መንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር

Views: 348

እምብዛም የማይደፈረውን፣ በቅጡ ያልመረመርነውን፤ እንደው በነሲብ ስንከተለው የኖርንበትንና አንዱን ጌታ ሌላውን ጭሰኛ ያደረገን ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ከመቶ ዓመት በፊት በቅጡ ለመመርመር እና ለመጋፈጥ የደፈረ አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ ብላቴና ነበር::

ይህ ብላቴና ገና በወጣትነት የዕድሜ ክልል ላይ ሆኖ፤ ለአገሩ እና ለወገኖቹ ብሩኅ ጭንቅላቱን ተጠቅሞ ብዙ ሊያበረክት ሲታትር፣ በውል ባልታወቀ አጨቃጫቂ ምክንያት ህይወቱ አለፈ::

በህይወት እያለም፤ ከሞተ በኋላም ያላደመጠችው አገር፣ ይኸው ሳትሞት በቁሟ እያጣጣረች አለች:: ልጆቿ በርኃብ፣ በሥደት እና በሥራ አጥነት አዙሪት ውስጥ ተተብትበው ዛሬም ከዓለም አገራት ህዝቦች የመጨረሻ የሚባለውን ደረጃ ይኖራሉ፡፡ መኖር ከተባለ!

“An Economist should have a cool mind and warm heart”

ፕ/ሮ እሸቱ ጮሌ

ያ ብላቴና ነጋድራስ ገ/ህይወት ባይከዳኝ አልሰማውም እንጂ ይህን ብሎ ነበር

‹‹የሚበላውንና የሚለብሰውንም ያጣ ድኻ የተወለደበትን አገር

የሚወድበትን ምክንያት ያጣልና የአገሩ መንግሥት ቢበረታ

ወይም ቢጠፋ ግድ የለውም፤ ስለዚህም መንግሥት የሚጠቀምበት

የአገሩ ኃብት በጥቂቶች ሰዎች እጅ ሲሰበሰብ አይደለም:: የአገሩ ኃብት

በመላው ሕዝብ ሲከፋፈለው ነው እንጂ ::›› 

ይህ ከተባላ መቶ ዓመት በኋላ በዚህች አገር ሠማይ ሥር የመንግሥት ሥርዓት እና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦች ተደርገዋል ፤ ያውም ባሸበረቁ ቃላት ተውበው ፖሊሲዎች ተጽፈው ለተግባራዊነታቸው ጠብ እርግፍ ተብሏል:: ዜጎች በድህነት እና ርኃብ ረገፉ እንጂ ለሠፊው ደኃ ሕዝብ ጠብ ያለ ነገር የለም::

ይህንንም ብሎ ነበር ወጣቱ አሳቢ ያን ግዜ …

‹‹አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ሥራት የለውም:: ሥራት የሌለው ሕዝብም

የደለደለ ኃይል የለውም:: የኃይል ምንጭ ሥራት ነው እንጂ የሠራዊት

ብዛት አይደለም:: ሥራት ከሌለው ሠፊ መንግሥት ይልቅ በሕግ የምትኖር

ትንሽ ከተማ ሞያ ትሠራለች፡፡››

ወጣቱ አዋቂ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ከመቶ ዓመት በፊት ስለ ሥርዓት እና ሠላም እንዲሁም በልጽጎ ለመኖር የሕግን አስፈላጊነት እና ቀጥተኛ ግንኙነታቸው ሰብኳል:: የዛሬዎቹ አዋቂዎች በሥርዓት አልበኛ ደጋፊዎቻቸው ብዛት እውቀታቸውን ይለካሉ:: ዘመን ወደ ፊት እውቀት ወደኋላ ኋላ፤ ይኸው ነው ያለንበት ዕውነት::

ፕሮፈሠር እሸቱ ጮሌ (መሬቱ ይቅለለውና) በአንድ ወቅት የተናገረውን ከላይ ያስቀመጥኩት ያለ ነገር አይደለም፤ የተረጋጋ አዕምሮ እና ሞቅ ያለ ልብ (ለወገኑ የሚገደው) የሌለው ኢኮኖሚስት (የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁር) በፈረሠ አገር ላይ ገበያውን እንደሸረሪት ድር ያደራል:: የተረጋጉ አሳብያን ለወገን የሚገዳቸው ተመራማሪዎች የሌሉበት አገር ከከብት በረት በምንም እንደማይሻል ያለንበት ሁኔታ ማሳያ ነው:: አልሰማንምና ቅጣቱ አይገባንም የምንልበት አንደበት አይኖረንም::

ገጽ 77 ላይ ደሞ ይህ ኃሳብ ሠፍሮ እናገኛለን:-

‹‹ሰው የተፈጠረ የዓለም ጌታ ሊሆን ነው፤ አርነት ካልሆነ

የተፈጠረለትንም ነገር ሁሉ ለማግኘት እንደ ባልንጀራው በትክክል

ደንብ ካልተበጀለት የምድር ጌታ ሆኖ በዓለም ሊኖር አይችልም::

ሰው ደግሞ ሲፈጠር ጌታ እና ደኃ ሆኖ አልተፈጠረም:: ድህነትና

ጌትነት የተለየ በሰው እውቀት ነው:: ስለዚህ፣ ዜጎቹን ለማስተካከል

የሚጥር መንግሥት ሁሉ የሕዝቡን ኃብት እንዲያበዛ የታወቀ ነው::››

ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ሩቅ አሳቢ በሆነ እና ጥልቅ መርማሪ በሆነው አዕምሮው እዚህ መጽሐፉ ላይ ዘመን ተሻጋሪ እና ትውልድን ቀያሪ የሆኑ ኃሳቦችን ሠንዝሯል:: ገጽ 93 ላይ ደግሞ ይህን ይለናል:-

‹‹ … ስለዚህም ያገራችን መሬት የዝኆን ጥርስ፣ ዝባድ፣ ቆዳ፣ ቡና፣ እኽል፣ በሬ፣ ላም፣ ፈረስ፣ አህያ፣ በቅሎ እየሆነ በያመቱ ወደ ውጭ አገር ቢሄድ አሁን ለጊዜው ለኛ ባይሰማን የኢትዮጵያ ሕዝብ በዝቶ መሬት እየጠበበ ሲሄድ ጉዳቱን ያገኘዋል:: ሕዝቡ በሥራ ሠልጥኖ ሥራውንም ሁሉ እንደመጠኑ ተከፋፍሎ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ባገሩ ለመበጀት ቢችል ግን ፍጉ ይቀርለት ነበር:: ስለዚህም፣ ዕውቀት ያነሰው ሕዝብ ዕውቀታቸው ከፍ ካሉ ሕዝቦች ጋር ሲገበያይ መዠመሪያ ትርፍ ድካም ይሰጣቸዋል:: ሁለተኛ መሬቱ ወደ እነሱ እየተጓዘ ይሄዳል:: እንደዚህ ያለውም ዕውቀት ያነሰው ሕዝብ ሲበዛ መሬቱ የሚሠጠው ፍሬ አይበቃውም:: ስለዚህም በግዜ ብዛት ሠርቼ እበላለሁ ሲል መሬቱ ወደ ሄደበት አገር ተከትሎ ዕውቀት ወዳላቸው ሕዝቦች አገር ይሰደዳል:: በአገሩም የቀሩ ሕዝቦች ወንድሞቹ ከረኃብና ከበሽታ ጋር እየታገሉ ዕረፍት ሳያገኙ ጊዜ ሞታቸው ይደርስና ይሄዳሉ ::››

ይህን መራራ እውነት ከመቶ ዓመት በፊት የነገረን ኢትዮጵያዊ ወጣት ምሁር መኖሩን ማወቅ፤ አውቆም ማሰብ እንዴት ክፉኛ ያማል?! በአገራችን ሠርተን የምንበለጽግበትን ሥርዓት ዘርግተን የሁላችን ሕይወት ይቃና ዘንድ መሥራት አልቻልንምና ዛሬ የተሰደዱት ሥጋቸውን አድነው መንፈሳቸውን ሲያደርቁ አገራቸው ያሉ ዜጎች ደሞ በሁለቱም ተጎድተው ይታያሉ:: ይህ ትንቢት ቀመስ ትንታኔ ኢትዮጵያዊውን ሊቅ ደግመን ደጋግመን እንድናከብረው የሚያስገድድ ሆኖ እናገኘዋለን::

ሌላኛው ጥልቅ ተመልካችነቱን እና መርማሪ ልቦና እንደነበረው የሚመሠክርለት ኃሳቡን ከመጽሐፉ ገጽ 105 እንዋሰው:-

‹‹… በዚህ አገር ውስጥ ወዳሉት ከተማዎች ወይም ትልልቅ መንደሮች ብንዞር

ሕዝቡ የተመቸ ኑሮ እንደ ለመደ ጌትነቱም እየበዛ እንደ ሄደ እናያለን፤ ግን አይሠራም::

ወደ አገር ቤትም ብንሄድ ባላገሩ ከድኽነት ጋር ሲታገል እናገኘዋለን:: ባንድ ፊት በየከተማው ሥራ ፈትተው የሚኖሩትን ሠዎች እመግባለኹ ሲል ይደክማል:: ባንድ ፊትም የሚመጣበት ገበያ ሩቅ ስለሆነ ባገሩ ቢሠራ ባንድ ጊዜ ያለ ብዙ ድካም ሊያገኘው የነበረውን ጨርቅና የቤት መሣሪያ እገዛለሁ ሲል ስምንት ግዜ ይደክምበታል፤ በዚሁም ጉልበቱ ይባክናል:: በመጨረሻም መሬቱ በዕዳ ተይዞ ወደ ሌላ እጅ ያልፋል:: ወይም ደሞ ለአንድ ትንሽ እርዳታ ሲል መሬቱን ላንድ ሹም አውርሶ ይሞታል:: ልጆቹም የሚቀመጡበት ቦታ አጥተው ቦታም ቢያገኙ የባላገሩን መከራ ጠልተው ወደ ከተማው ይሄዳሉ:: ሳይሠሩ የሚበሉትንም ሠዎች ቁጥር ማሳደጊያ ይሆናሉ::

ወይም የአንዱ ፈረንጅ አሽከር ሁነው ለራሳቸውም ለአገራቸውም ጥቅም
ሳይሆኑ ዕድሜያቸውን ሙሉ በከንቱ ያሳልፉታል:: እንግዲህም አራሹ
እያነሰ ባራሹ ድካም የሚመገቡ እየበዙ ይሄዳሉ:: በሥርዓት ተከፋፍሎ
የነበረውም መሬት በዕዳም በውርስም ሄዶ በጥቂቶች እጅ ይገባል::
የመንግሥትንም ሥራ በእጃቸው የጨበጡ እነዚህ ጥቂቶች ሰዎች
ስለሆኑ በግብር የሚጫናቸው የለም፡፡››

ትላንትም ዛሬም በተለያዩ ሥርዓቶች እና ሁኔታዎች ውስጥ ሆነን ኃብት እና ሥልጣን የጥቂቶች መሆኑን ስንገነዘብ እንደገና ቁጭት እና የባከነ ዘመን እንደ አገር እንዳሳለፍን ከመስማማት ውጭ አማራጭ ያለን አይመስልም:: ነጋድራስ ገ/ሕይወት ከመቶ ዓመት በፊት አዝማሚያውን ታዝቦ ያመላከተንን አቅጣጫ ‹‹አባከና›› ስላላልነው እዚህ ደርሰናል:: አስቀያሚ አዙሪት የእኛነታችን መገለጫ ይመስላል::

ነጋድራስ ገ/ሕይወት ‹‹አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› እንዲሁም ዛሬ በወፍ በረር ዳሰሳ ያየነው ‹‹መንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር›› የተባሉ ሁለት ሥራዎችን ትቶልን የዛሬ መቶ ዓመት ገደማ በ1911 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል:: አስተሳሰቦቹ እና ጥልቅ ምልከታዎቹ ግን ዛሬም ድረስ አብረውን አሉ:: በተለይ እንደኛ ዓይነት ‹‹ታሪክ ራሱን መድገም….›› ብቻ ሳይሆን፣ ታሪክ በማይቀየርበት አገር፤ የትላንቱ እንቅፋት የዛሬውም ነውና በትላንት መነጽር አገርን መገምገም ታሪክ ግምገማ አይሆንም::

የዜጎችን ሕይወት መለወጥ እና አገርን ማበልጸግ ያልቻለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ፤ ስለምን ከአንጋፋዎቹ የአገር አዋቂዎች እንደነ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ ያሉቱን ኃሳብ አይመረምርም? በቂ ውይይት አድርገንበት ይሆን ‹‹መንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር›› የተባለውን ይህን ሥራቸውን? ስለ ሠላም ጥቅም፣ ስለ ልማት ዋጋ፣ ስለ ሕግ የበላይነት አስፈላጊነት፣ ስለ መንግሥት ጽናት አስፈላጊነት፣ ስለ ግብር አሰባሰብ ዘዴ እና አስፈላጊነት፣ ስለ ማኅበረሰብ ብልጽግና፣ ስለ ዓለም ታሪክ እና አስተዳድራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተሞክሮ ብሎም ስለ ነገ እጣፈንታችን ወጣቱ ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ በዚህ የበኩር ሥራው አስተምሮናል፣ መክሮናል እናም አስጠንቅቆናል::

እንደተለመደው ሁሉ እንኳን ትላንት ዛሬም ለመስማት፣ በጥሞና ለመወያየት፣ የብልህ እርምጃ ለመውሰድ እንዲሁም ባጠቃላይ አገራችንን በጋራ ልንበለጽግባት በቀናነት አንነሳም:: እናም ደጋግመን እንወድቃለን!!! ይህንን ነው ብላቴናው ያለን!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com