ኢትዮጵያውያን ህፃናት ከእስራኤላውያን እኩዮቻቸው ጋር በአንድ ክፍል እንዳይማሩ ተደረገ

Views: 154

ኢትዮጵያውያን የመዋዕለ ህፃናት ተማሪዎች በእስራኤል ኪሪያት ጋት ከተማ ከእስራኤላውያን የእድሜ እኩዮቻቸው ጋር በአንድ ክፍል እንዳይማሩ እየተደረገ መሆኑ በጥቁር ወላጆች ዘንድ ቁጣ አስነስቷል ተባለ፡፡

ሴፊ ቢሊለን የሚባሉ ወላጅ እንደተናገሩት፣ የሦስት ዓመት ልጃቸውን መዋዕለ ህፃናት ት/ቤት ወስደው ካስመዘገቡ በኋላ፣ የተመዘገቡ ተማሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ስሟን ስላላገኙት ጉዳዩን ለመጠየቅ ወደ ትምህርት ቤቱ ሲሄዱ፣ ኢትዮጵያዊ ህፃናት ለብቻቸው ክፍል እንዳላቸውና ለብቻቸው እንደሚማሩ ባዩበት ወቅት አይናቸውን ማመን እንዳቃታቸው ተናግረዋል፡፡

የልጄ ስም በዝርዝሩ ውስጥ የለም ብለው ሲጠይቁ፣ ወደ ሌላኛው የህንፃ ክፍል እንዲሄዱና እዛ እንዲያዩ በተነገራቸው መሠረት ሲሄዱ የጠበቃቸው የነጮቹ ተማሪዎች ክፍል ሌላ ሲሆን ለኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች ደግሞ ሌላ መማሪያ ክፍል ሆኖ አግኝተውታል፡፡

“እነዚህ ታዳጊ ህፃናት በህይወታቸው ምንም መጥፎ ነገር አላደረጉም፤ ሊያደርጉም አይችሉም፤ በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ግን ከሌሎች እኩዮቻቸው ጋር አንድ ላይ እንዲሆኑ አልተፈቀደላቸውም” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

እኚህ ወላጅ የትምህርት ቤቱን ሁኔታ እንዳዩ ወዲያውኑ ልጃቸውን  ይዘው እንደወጡና  ወደ ከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ቅሬታ ለማቅረብ እንደሄዱም ተናግረዋል፡፡

“ማንም ሰው ልጆቻችንን ማግለል አይችልም፤ ጉዳዩንም በፀጥታ አናልፈውም ምክንያቱም ልጆቻችን በራሳቸው ተማምነው በቆዳቸው ቀለም ሳይሳቀቁ ማደግ ስላለባቸው ነው” ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያ የሆኑት ታማኖ ሻታም የመዋዕለ ህፃናቱን  አጸያፊ ተግባር በኃይል አውግዘው ኢትዮጵያውያን ህፃናት ከየትኛውም እስራኤላዊ ህፃን የሚለዩ አይደለም፤ የሀገሪቷ ትምህርት ሚኒስትርም በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያካሄደ እንደሆነ ገልጸው፤ ችግሩንም በአፋጣኝ እንደሚፈታም  ተናግረዋል፡፡

የከተማው ማዘጋጃ ቤት የህፃናቱ መማሪያ ክፍል ምደባ የተደረገው በኮምፒውተር ሲስተም ሲሆን ከአንድ አካባቢ የመጡ ተማሪዎችን በአንድ ላይ በማድረጉና በወላጆች ጥያቄ መሠረትም እንደሆነም ገልጿል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com