ስድስተኛው ፓትሪያርክ አሳሰቡ

Views: 179
  • “ከመለያየት ጉዳት ይተርፋል፤ ከአንድነት በረከት ይገኛል”

ከብዙ ዓመታት መለያየት በኋላ አንድ የሆነችውን ቤተክርስቲያን ዳግም የሚለያይ አጀንዳ መከሰቱ እንዳሳዘናቸው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ፡፡

በዐራተኛው ፓትሪያርክ ብፁህ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በዓለ-ሲመት ላይ የተገኙት አቡነ ማትያስ እንደተናገሩት፣  ከብዙ ዓመታት መለያየት በኋላ ሲኖዶስ አንድ በመሆኑ ሁሉም ህዝበ ክርስቲያን ተደስቶ ባለበት ወቅት፣ ቤተክርስቲያንን የሚከፋፍል ሌላ አጀንዳ ማምጣቱ አሳዝኖኛል ብለዋል፡፡

ቤተክርስቲያን አንድ ሆነች ብለን በተደሰትንበት፣ በአንፃሩ ሀገራችንም ባለችበት አስቸጋሪ ወቅት ይህን ጥያቄ ያነሱት ሰዎች ለቤተክርስቲያን አንድነትና ለሀገራችን ሠላምና አንድነት ሲሉ በአግባቡ ሊያስቡበት ይገባል ብለዋል፡፡

ይህ የበዓለ-ሲመት ዝግጅት፣ የአንድነት በዓል ነው ያሉት አቡነ ማትያስ ሁሉም ህዝብ እንደ መልካም አርዓያነት ወስዶት፣ ከመከፋፈል ይልቅ አንድነትን የሚመርጥበት መሆን አለበት ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ከመለያያት የሚገኘው ጉዳት እንጂ ጥቅም አይደለም፤ መርገምት እንጂ በረከት አይኖርም በማለት በአጽንዖት የተናገሩት ፓትሪያርኩ፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን ሰላሟንና አንድነቷን ጠብቃ ስትኖር ነው በበረከት የምትጎበኘው ሲሉ ብፁህነታቸው ገልጸዋል፡፡

በሀገራችን የተፈጠረው ችግር እንዲቆም፣ ሁላችንም በአንድ ልብ ሆነን በፍቅር መፀለይ ይኖርብናል፤ ፈጣሪም ፀሎታችንን የሚሰማው አንድ ላይ ሆነን በፍቅር ስንለምነው ነው እንጂ ተጠላልተን እና ተከፋፍለን የምንፀልየው ፀሎት ተቀባይነት የለውም በማለት ገስጸዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com