“የተማረ ሰው ይዋሻል”፣ እና ስለ ቻርልስ ዳርዊን ‘ ሰርቫይቫል ኦፍ ዘ ፊተስት’

Views: 314

በአዱሊስ ቲዩብ (Adulis tube) ሰለተላለፈ ንግግር የተሰጠ አስተያየት

በቅርቡ አንድ በዩቱብ ቪዲዮ የተላለፈን የአዱሊስ ቲዩብ (Adulis tube) ዝግጅት ስሰማ ተናጋሪው ወጣት ለተሰብሳቢው እና ለአዳማጩ ከተናገራቸው ዐረፍተ ነገሮች መካከል ሁለት መስተካከል የሚገባቸው መልእክቶች ስላገኘሁ ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀትና በዚያ ስብሰባ ላይ ለነበሩም ሆነ ለሌሎች ግንዛቤ ይረዳል በሚል ወደ እናንተ ዘንድ ልኬዋለሁ። ከዚህ ጊዜ ቀደም ብሎ (እኤአ March 1999 ) ኢኢዲኤን (E.E.D.N: Ethiopian Electronic Distribution Network) በተባለ የኤሌክትሮኒክ መድረክ በተለይ ሰለ ቻርልስ ዳርዊን ሰርቫይቫል ኦፍ ዘ ፊተስት ተነስቶ ውይይት ተደርጎ ነበር ።

ማጠንጠኛ ሀሳቡም “Survival of the Fittest might be the most misused concept by non-biologists” የሚል ሲሆን፣ አንዱ ተሳታፊም የሚከተለውን ሀሳብ ሰንዝሮ ነበር “To me ‘Survival of the Fittest’ is not to be understood without grasping the concept of natural selection” ። ይህ ተሳታፊ ያለው ትክክል በመሆኑ በዚህ ርዕስ ዙሪያ መወያየት ለሚሹ፣ ጽሁፍ ለሚያዘጋጁ፣ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ንግግር ለሚያደርጉ ሁሉ በቅድሚያ ሰለርዕሱ ስለተጻፈው እንዲያነቡ እና እንዲረዱት አሳስባለሁ። ዝግጅቱን በሚከተለው አድራሻ ያገኙታል። ተናጋሪው ስሙ ስላልተጠቀሰ እዚህ ልጠቅሰው አልቻልኩም።

(Published on Jul 6, 2019)

መስተካከል የሚገባቸው ሁለቱ አረፍተ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፤

፩ኛ በተማርን ቁጥር እንዋሻለን፣ የተማረ ሰው ይዋሻል፣ ዲግሪ ካለው ማስተር ያለው ውሸታም ነው፡ ሁለተኛ ሀይማኖት (religion is a power) …
፪ኛ ስለ ቻርልስ ዳርዊን ሰርቫይቫል ኦፍ ዘፊተስት፣ የተናገራቸውን … በ፰፡ ፴፰ ኛው ደቂቃ (8: 38 minutes) ጀምሮ ያለውን ያድምጡ፣ “የተማረ ሰው እንደሚዋሽ ማሳያው አንደኛ አማኝ ነው፣ ይዋሻል” ይላል።

ይህንን አስተያየት እንዴት አብራራው? የተናገረውን እጠቅሳለሁ፣ “በነገራችን ላይ በዘመናዊ ትምህርት ( one person cannot be both a believer and a scientist ) ምክንያቱም የዘመናዊው ዓለም ነቢያት አንደኛ ቻርልስ ዳርዊን ሰርቫይቫል ኦፍ ዘፊተስት ሲል እርስ በርስ ተዋግተህ በሳይዝ ምልከታ በዳርዊን ትውስት ዛሬ መባላታችን ትክክል ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ያሸነፈ ይኑር ። ተፈጥሮ ራሷን ባላንስ የምታደርገው እያባላች ነው፣ የማልቱሲያን ቲዎሪ ሀሳብ ወ.ዘ.ተ.”
አስተያየት ቶማስ ማልተስ (Thomas Malthus) ለምን እዚህ ላይ እንደገባ ባላውቅም ስለዚህ ሰው አስተዋጽዖ በጥቂቱ ከታች አብራራለሁ።

አንደኛ በጅምላ መፈረጅ ትክክል አይሆንም፣ ተቀባይነት አይኖረውም። አንድ ሰው አማኝም ኢአማኝም (የማያምንም) ሊሆን አይችልም አለ ተናጋሪው። አንድ ሰው ከተማረ አማኝ አይሆንም የሚል አመለካከት ነው። ይህ ጉልህ ስህተት የያዘ አስተያየት ነው። ለስህተቱ በቂ ማስረጃ ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ሀኪሞችን ከማየት ወይ ከመጠየቅ ይገኛል። ብዙዎች የቀዶ ጥገና ሀኪሞች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ትንሽ ጸሎት ያደርጋሉ፣ አምነው ነው ወይስ ሳያምኑበት? መልሱን ከእነርሱ ታገኛላችሁ።

አንዳንድ ሀኪሞች በእነርሱ ስር ሆነው የሕክምና ትምህርት የሚከታተሉትን ተማራዎቻቸውን ሲያሰለጥኑ የአእምሮ ወይም የአካል ጉድለት ስላለባቸው ሕሙማን ከሚነግሯቸው የመጀመሪያ ዐረፍተ ነገር መካከል የሚጠቀሰው “እኛ ዕድለኞች ነን ፈጣሪያችን እንደነርሱ አድርጎ ሊፈጥረን ይችል ነበር” የሚል ይገኝበታል። ይህ የማመን አዝማሚያ ይመስላል፣ ባይሆንም እንኳ ሌላ ገንቢ የሆነ የትምህርት ገጽታን አመልካች ነው።
፪ኛ ስለ ቻርልስ ዳርዊን ሰርቫይቫል ኦፍ ዘ ፊተስት (Survival of the Fittest)፣ የተናገረውን አያይዘን እስቲ በዚህ ርዕስ ዙሩያ የተጻፉትን በሰፊው እንያቸው።
ሰርቫይቫል ኦፍ ዘ ፊተስት የሚለውን ሐረግ የፈጠረው ኸርበርት ስፔንሰር (Herbert Spencer) በ1864 በታተመ መጽሐፉ እንጂ ቻርልስ ዳርዊን አልነበረም። ይህንን ሐረግ በመጀመሪያው የዳርዊን መጽሀፍ (1859 በታተመው) ላይ የለም። ኸርበርት ስፔንሰር ይህንን ሐረግ ከፈጠረ በኋላ ጽሁፉን ለሂስና ለትችት ወደ ዳርዊን የላከው አልፍሬድ ዋላስ (Alfred Wallace) ነበር። ለማስረጃ የሚከተለውን ከኸርበርት ስፔንሰር መጽሐፍ የተገኘ ጥቅስ ይመልከቱ።

Principles of Biology (volume 1, 1864, page 444): this survival of the fittest, which I have here sought to express in mechanical terms, is that which Mr. Darwin has called ‘natural selection’ or the preservation of favored races in the struggle for life.

አዎን ኸርበርት ስፔንሰር ከአካል ግዝፈትና ከጥንካሬ ጋር አያይዞ ሰለጻፈ በጊዜው የነበሩ የፓለቲካ ቡድኖች እና ግለሰቦች በሕዝቦች መካከል የሚታዩ ልዩነቶችን ለማስፋፊያ እና ሕዝቦችን ለመከፋፈያ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል። ከዚያም በዃላ የሰውን ዘር ለማሻሻል በሚል ስሜት ተነሳስተው ኢውጀኒክስ (Eugenics – the self-direction of human evolution) የሚባል መስክ የፈጠሩና ጥሩውን የሰው ዘር መጥፎ ብለው ከፈረጁት በመለየት በሰዎች ላይ ብዙ ዘግናኝ
የሆኑ ምርምሮችን ያደረጉ ሰዎችም ነበሩ።

የተፈጥሮ መረጣ (Natural Selection) ወይም ተፈጥሮ ለአካባቢያቸው ምቹ የሆኑትን የወደፊት ዝርያዎችን ትመርጣለች የሚለውን አስተሳሰብ ለሰዎች ግራ አጋቢ ሆኖ በመገኘቱ ቻርልስ ዳርዊን ማብራሪያ እንዲያደርግ ያሳሰበው በተመሳሳይ ሁኔታ እና ጊዜ፣ ነገር ግን ሌላ ቦታ ሆኖ ፤ ምርምር ያደርግ የነበረው ሌላው የሳይንስ ሊቅ አልፍሬድ ዋላስ (Alfred Wallace) ነበር። ይህንን አስተያየት ተመርኩዞ ዳርዊን የሚከተለውን ፃፈ፤ ከአራት አመት በዃላ (1868). ቻርልስ ዳርዊን በሚከተለው ርዕስ (The Variation of Animals and Plants under Domestication, page 6, 1 st edition, 1868) ከጻፈው ውስጥ የተወሰደውን ለንፅፅር ይመልከቱ።

This preservation, during the battle for life, of varieties , which possess any advantage in structure, constitution, or instinct, I have called Natural Selection; and Mr. Herbert Spencer has well expressed the same idea by the Survival of the Fittest. The term “natural selection” is in some respects a bad one , as it seems to imply conscious choice; but this will be disregarded after a little familiarity.

ዳርዊን “preservation … of varieties , …” እንጂ “preservation of species (ዘር) አላለም። በዘር ውስጥ ብዙ ዓይነት ዝርያዎች (በቆዳ ቀለም፣ በቁመት፣ በሰውነት ስፋት፣ በሰውነት ቅርጽ፣ ወ.ዘ.ተ. የሚገለጹ) አሉ።

ዳርዊን ለምን “ a bad one ” አለ?
ይህንን (በ1868) የጻፈው አልፍሬድ ዋላስ የሌሎች ሊቆችን ትችት (የዳርዊን መጽሃፍ ከታተመበት ከ1859 እስከ 1868 ያሉትን) ሰምቶ ዳርዊን እንዲያብራራው ካሳሰበው በኋላ ነበር።

Survival of the Fittest: ይህን ሐረግንስ በሚመለከት የቻርልስ ዳርዊን አስተሳሰብ ምን ነበር?
ዳርዊን ያለው ‘ የሚቀጥለውን ትውልድ የሚመርጠው ሰው ሳይሆን ተፈጥሮ ነው’ የሚል ነው፣ በተለይም ለእንስሳት እና ለዕፀዋት። ለአንድ እንስሳ አካባቢዉ ምቹ ካልሆነ ያለው ምርጫ ቦታ መቀየር ነው፣ ይህንን ካላደረገ እርሱም ዘሩም ይጠፋል። ለምሳሌ የዓለም ማያው ሀይቅ ሲደርቅ ውሃው ውስጥ የነበሩ አሳዎች እና ሌሎች እንስሳት የት ሄዱ? መልሱ ግልፅ ይመስለኛል። የሰው ዝርያን በተመለከተ ደግሞ በቀላሉ ለመረዳት ያህል የሚከተለውን ምሳሌ ማየት እና ማሰላሰል
በቂ ይሆናል።

አንድ ቤተሰብ፣ ማለትም ባልና ሚስት፣ አንድ ልጅ ብቻ ቢኖራቸው፣ ጎረቤታቸው ያለ ሌላ ቤተሰብ አስር ልጆች ቢወልዱና ሁሉም ለአቅመ አዳም ደርሰው ልጆች ቢወልዱ፣ ከሁለት ወይም ከሶስት ትውልድ፣ ማለትም ከዛሬ አርባ ወይም ስልሳ ዓመት በኳላ፣ ብዙ የሕዋሳት አይነቶችን እና በራሂዎችን (genes) ለትውልድ በብዛት
ያሚያስተላለፈው ባለ አስሩ ቤተሰብ ነው የሚሆነው እንጂ አንድ ልጅ ብቻ የወለዱት አይሆንም የሚል ነው። ስለዚህ ፊትነስ (fitness) የሚለው ቃል ሪፕሮዳክቲቭ ፊትነስ (reproductive fitness) በሚለው ገላጭ በሆነው መልኩ ነው መረዳትም ሆነ መተርጎም ያለበት። ቻርልስ ዳርዊን ‘Survival of the Fittest’ ሲል
ይህንን ነው የምንገነዘበው።

ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንይ፣ በባክቴሪያ ምርምር ላይ የተሰማሩ ሀኪሞችም ሆኑ ሌሎች ተመራማሪዎች በየጊዜው የሚያስገነዝቡን አንድ ምክርና ትምህርት አለ። ለአንድ በባክቴርያ ለተጠቃ በሽተኛ ይህንን መድሃኒት ሳታቋርጥ ወይም ሳታቋርጪ ጠዋትና ማታ በቀን ሁለቴ ለአስር ቀን ውሰድ ወይም ውሰጂ ይላሉ። ምክንያት አላቸው። አንዳንድ ሰው መድሃኒቱን ለሶስት ወይም ለአራት ቀን ከወሰደ በኋላ የመሻል ምልክት ሲያይ ወይም ሲሰማው መድሃኒቱን መውሰድ ያቆማል። ነገር ግን ከጊዜ በኋላ በድጋሚ ከታመመ ሀኪሞቹ ያንኑ መድሃኒት መልሰው ላያዙለት ይችላሉ፣ መድሃኒቱን ለታቀደው አስር ቀናት ሳይወስድ ቀርቶ ሊሆን ይችላል ብሎ ሀኪሙ ሊገምት ይችላል፣ በሽተኛው በትክክል ባይናገርም፣ ምክንያቱም መድሃኒቱ በቤተ ሙከራ ጥናት ያንን ባክቴርያ በአስር ቀናት ውስጥ ጨርሶ እንደሚያጠፋው ሀኪሙ ስለሚያውቅ ነው። በተለምዶ የበሽተኛው ሰውነት በሽታውን ተላምዶት ነው ይባላል፣ ወይም በተመሳሳይ ሁኔታ ይገለጻል። ነገር ግን የሆነው ባክቴርያው ፀባዩን ቀይሮ መገኘቱና በሌላ መልክ ወይም በተጠናከረ ሁኔታ ከበሽተኛው ሕዋሳት መኖሪያውን እና ምግቡን ለማግኘት መቻሉ ነው።

በሽተኛው ከወሰደው መድሂኒት ጥቃት ያመለጡት ባክቴሪያዎች ተለይተው መባዛት ሲጀምሩ ነው የዳርዊን የ’Survival of the Fittest’ አስተሳሰብ ትክክል መሆኑ የሚረጋገጠው። ይህም በቤተ ሙከራ ጥናት በብዙ እንስሳት እና ባክቴርያዎች ላይ ተሞክሯል።

ሰለዝግመተ-ለውጥ (Evolution)
ዝግመተ-ለውጥን (Evolution) በትምህርት እና በንባብ ማወቅ፣ ለውጡን እና የለውጡን ሂደት ማወቅ ይሆናል፣ መቀበል ወይም አለመቀበል ሊሆንም ይችላል። ማወቅም፣ መቀበልም፣ አንዱን ወይም ሁለቱንም ሊሆንም ይችላል። ስለ ዝግመተ ለውጥ ማወቅ ማመን አይደለም፣ አይሆንምም። ስለዝግመተ-ለውጥ በቃል በሚገለጽበት ጊዜ ወይም በጽሁፍ ሲገለጽ የተደረሰበትን ድምዳሜ እና የቀረቡት መረጃዎች/ማስረጃዎች በበቂ ሁኔታ ክስተቱን ይገልጻሉ ወይስ አይገልጹም የሚል ጥያቄ ተነስቶ ይህ በበቂ ሁኔታ መመለስ አለበት። የቀረቡት መረጃዎች ተቀባይነት የሚወሰነው ለክስተቱ እና ለአስተምሮው ቅርበት ሲኖር ነው።

ቶማስ ማልተስ ማን ነበር ስሙስ ከቻርልስ ዳርዊን ጋር አብሮ ለምን ተነሳ?
ቶማስ ማልተስ የእንግሊዝ ዜጋ ነበር፤ በወቅቱ በነበሩ ምሁራን ዘንድ ሊታወቅ ከበቃበት ምክንያቶች አንዱ በሕዝብ ዕድገት እና በምጣኔ ሀብት መካከል ስላለው ቁርኝት እኤአ በ፲፯፻፺፰ (1798) (An Essay on the Principle of Population) የተሰኘ መጽሀፍ በመጻፉና በልዩ ልዩ ቦታዎችና አጋጣሚዎች በተደረጉ ውይይቶች፣ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጋቸው ክርክሮች፣ እና በሰጠው አስተያየቶች ነበር። ከእነዚህ አስተያየቶች ውስጥ የህዝብ ቁጥር ያለገደብ መጨመር አይችልም፣ ገደብ ይኖረዋል የሚለው ሲሆን፣ የገደቡ መንስዔ የሰዎች በረሀብ እና በበሽታ መጠቃት ነው ሲል ጽፏል። ሌላው በእንግሊዝ መንግሥት ደሆችን ለመርዳት የወጣው የ(Poor Laws) ሕግ ከምጣኔ ሀብት አኳያ ሲታይ የገንዘብ ግሽበትን ያስከትላል እንጂ ለደሀው ሕዝብ መፍትሄ አያመጣም ሲል ይከራከር የነበረው ነው። እንደእርሱ ከሆነ መፍትሄው የነፍስ ወከፍ ፍጆታን መቀነስ እና በኑሮአችን ላይ ግብረገባዊነት (ፈሪሃ እግዚአብሔር) ተጨምሮበት በመተሳሰብ ስንኖር ነው የሚል ነበር።

የእርሱን ታሪክ ትቼ ከዳርዊን ስራ ጋር እንዴት ስሙ አብሮ እንደሚነሳ በጥቂቱ እገልጻለሁ። ማልተስ እኤአ በ1766 ተወልዶ በ1834 ሞተ። ቻርልስ ዳርዊን ከእርሱ በኋላ እኤአ በ1809 ተወልዶ በ1882 ሞተ። ይህ ማለት ዳርዊን ገና የአስራ አምስት አመት ልጅ ሆኖ ነበር ማልተስ የሞተው። ስለዚህ የመተዋወቅም ሆነ በሕዝብ ጉዳይ ላይ ወይም ዝግመተ ለውጥን በተመለከተ በአንድነት ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም፣ ሊኖርም አይችልም። የሆነው ግን ዳርዊን አድጎ፣ ምርምር በማድረግ ላይ እያለ የማልተስን መጽሐፍ ያነባል። በምርምር ሥራው አሳሳቢ ስለነበረ አንድ ጉዳይ ከማልተስ መጽሐፍ ውስጥ አመላካች የሆነ ሀሳብ ያገኛል ፤ በጊዜ ሂደት ያንን ሀሳብ ከሌላ መጽሐፍ ውስጥ ካገኘው ሌላ ሀሳብ ጋር በማዛመድ ሲያሰላስል ስለነበረው የዝግመተ ለውጥ ሂደት ፍንጭ የሚሰጥ እና ዝግመተ ለውጥ እውን ነው ብሎ ያሰበውን ያሳካለት ስለነበር ነው። የሚከተለው መጽሃፍ በቅርቡ ለሕትመት በቅቷል፣ ሰለ ዝግመተ ለውጥ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል፣ ገዝተው ያንቡ።
ከየት ወደ የት የሰው ዘር ዝግመተ ለውጥ እና ማህበራዊ እድገት ያለማቋረጥ ይጓዛል፣ ሽብሩ ተድላ 2011 ዓ.ም

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. ጹሑፉን ለማንበብ በቅቻለሁ፡፡ ይህን ዓይነት ሰህተት በብዛት በብዙ አካባቢዎች ይከሰታል፡፡ በተቻለ መጠን ይህን ዓይነት ስህተት ማረም፣ ብሎም ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲዳብር መጣር ፣ የሁላችንም አላፊነት ነው፡፡ የእኔ አስተዋጽዖ አነሆ፡፡

    ‘Survival of the fittest’ ስለሚለው ሐረግ በቅድሚያ መገንዘብ ያለብን ድርጊቱ የጉልበት ጉዳይ አለመሆኑን ነው፣ ሁኔታን በተገቢ/ በሚያዋጣ መንገድ መጋፈጥ የመቻል አቅምን ማዳበር እንጂ፡፡ በበራሂ መዋቅር የተመሰረተ ከችግር ማምለጫ ዘዴ ነው፡፡ ለአካባቢ ተስማሚ አቅምን ማጎልበት ነው፡፡ የተከሰተ ሀኔታን መቋቋም የሚችሉ ናቸው ሕያው ሆነው ዘር የሚተኩ፡፡ ለምሳሌ በአይጥ ዓለም፣ በትንሽ ጠለላ መደበቅ ከማይችሉ ግዙፍ አይጦች (በጉልበት ከትናንሽ አይጦች የሚልቁ)፣ በትንሽ ጠለላ ሊደበቁ የሚችሉ፣ ከአይጥ-በል ንስር የመሰወር፤ብሎም
    ሕያው ሆኖ የመዝለቅ እድል አላቸው፡፡ በተጨማሪ ‘Survival of the fittest’ ማለት ችግሮችን አሸንፎ መዝለቅ እንደ ማለት ይታያል፣ በራሂዎች ባበረከቱት አቅም ከብዙ ውድመትን ሊያስከትሉ ከሚችሉ ሁኔታዎች ዘሎ፣ሾልኮ፣ ማምለጥ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡
    ሽብሩ

This site is protected by wp-copyrightpro.com