“ቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄያችንን ባይቀበለውም ሂደታችንና ጥያቄያችን አይቆምም!” ቀሲስ በላይ መኮንን (ሊቀ አእላፍ)

Views: 120

– ሀገር እያፈረስን ሳይሆን እየገነባን ነው!

በቅርቡ ‹‹የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት ጽ/ቤት››ን እናቋቁማለን በሚል በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ቀሲስ በላይ መኮንን (ሊቀ አእላፍ)፣ ‹‹ድርጊታችንን የሚቃወም የቤተክርስቲያን ጠላት ብቻ ነው፤ ለአስተዳደራዊ ሥራ ያልተማከለ ሥርዓት ነው ለማስፈን እሞከርን ያለነው›› ሲሉ ለኢት-ኦንላይን ገለጹ፡፡ የተናጠል ጽ/ቤት ለማቋቋም የሚያደርጉት ሂደት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር እያወዛገባቸው ነው፡፡

‹‹ጥያቄያችንን ቅዱስ ሲኖዶስ ባይቀበለውም፣ ጥያቄያችንን እና የምስረታ ሂደታችንን አናቆምም›› ሲሉ ለዘጋቢያችን በስልክ የገለጹት ቀሲስ በላይ መኮንን፤ ‹‹ሲኖዶሱ ይህን ካልተቀበለ ቤተክርስቲያንም የለችም፤ እኛም የለንም ማለት ነው፤ አስተዳደራዊ በደሉ ካልተፈታ ይቺ ቤተክርስቲያን የለችም›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ በምዕራቡ የሀገራችን ክፍል በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ 85 እና 90 በመቶ ምዕመኗን በአስተዳደር በደል የተነሳ በሌሎች ሃይማኖቶች ተነጥቃለች የሚሉት ቀሲስ በላይ፤ ብዙው ምዕመን በአስተዳደር በደል ከቤተክርስቲያን እንዲርቁ ተደርገዋል፤ ብዙ አብያተ-ቤተክርስቲያናት ተዘግተዋል፤ የእኛ እቅድ ይሄን መልሶ ለመክፈትና ህዝባችንን ለመመለስ ነው እንጂ ሰዎች እንደሚያወሩት ሀገር ለማፍረስ ሳይሆን፣ ሀገር ለመገንባት ነው ብለዋል፡፡

ጉዳዩንም የጀመርነው ዛሬ ሳይሆን፣ ከአሥራ አምስት እና አሥራ ስድስት ዓመት አካባቢ ነው፡፡ ይሄ እንቅስቃሴ በውስጣችን ያለውን የአስተዳደር በደል የሚፈታ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት ያልተማከለ የቤተክህነት ጽ/ቤት ድሮ ትግራይ ጠቅላይ ግዛት በነበረበት ወቅት፣ የትግራይ ሀገረ ስብከት የሚል ነበር ያሉት ቀሲስ በላይ፤ ያኔ ኦሮሚያ እና አማራ ጠቅላይ ግዛት ያልተባለበት ምክንያት፣ በጣም ሰፊ ግዛት ስለሆኑ ጎጃም ክፍለ ሃገር፣ ባሌ ክፍለ ሃገር፣ ጎንደር ክፍለ ሃገር፣ ወለጋ ክፍለ ሃገር እየተባለ የሚሄድ አስተዳደር ነበር ብለዋል፡፡

አሁንም ትግራይም መቀሌ ላይ፣ በዐማራም ባህርዳር ላይ ቢቋቋም እና ደቡብም እንዲሁ በተለያዩ ቦታዎች ቢመሰረት ለአስተዳደራዊ በደል ፍቱን መፍትሄ ነው፤ ይህ ተግባር ቤተክርስቲያንን ማዳን ነው ብለዋል፡፡

የቤተክርስቲያኒቱ ዶግማ እና ቀኖና (ሕገ-ቤተክርስቲያን) እንከን የለሽ ነው፤ ቃል-ዓዋዲው ይሻሻል ከተባለ የሚሻሻሉ ነገሮች አሉ፤ በአጠቃላይ ግን በጣም ጥሩ እና የምንወደው ነው፤ ከዛ አንወጣም፤ አስተዳደሩ ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አፍርሷታል፤ ወደፊት ኦሮሚያ ብቻ አይደለም፣ ደቡብም፣ ጋምቤላም፣ ቤኒሻንጉል ይከተላል ሲሉ ለዘጋቢያችን አስረድተዋል፡፡

ይሄን እንቅስቃሴ ስንጀምርም የቤተክርስቲያኒቱን ሕግ ተከትለን ነው፣ መጀመሪያ ቤተክርስቲያን ስትመሠረት ሃዋርያት ከክርስቶስ ተልዕኮ ወስደው ሲሰማሩ የህዝቡን ቋንቋ፣ የህዝቡን አሰፋፈር ተከትለው፣ ህዝቡን እንዲያስተምሩ፣ አብያተ-ክርስቲያናትን እንዲያስፋፉና እንዲያንጹ ነው፤ ይሄን ነው እያደረግን ያለነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሀገራችንም የህዝቡን አሰፋፈር እና የመንግሥትን አወቃቀር ተከትላ ነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተመሠረተችው፤ ቀደም ሲል አንድ ጠቅላይ ግዛት በነበረበት ጊዜ አንድ መንበረ ጵጵስና ናት፤ አንዱ ለአራት በተከፈለ ጊዜ ደግሞ አራት ጽ/ቤት አላት፤ ለምን ቢባል እዛ ካለው መሠረት ጋር እኩል አቻ ሆና እንድትሄድና ክብሯን፣ መብቷን ለማስከበር፣ ችግር ለመፍታት፣ የህዝቡንም ጥያቄ ይዛ መንግሥት ህዝቡን የሚጎዳ ሥራ እንዳይሰራ ትጸልይለት ዘንድ፤ ትመክር ዘንድ እንዲቻላት ነው ብለዋል- ለዘጋቢያችን፡፡
(ከቀሲስ በላይ መኮንን ጋር ያደረግነውን የስልክ ቃለ-መጠይቅ፣ በነገው ዕለት ሙሉውን የምናቀርብ ይሆናል)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com