ሲኖዶስ፣ በቀሲስ በላይ ሊቋቋም በታሰበው የኦሮሚያ ቤተክህነት ጽ/ቤት አቋም ወሰደ

Views: 97

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በቀሲስ በላይ ሊቋቋም ለታሰበው ‹‹የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት ጽ/ቤት›› ጉዳይ ላይ መክሮ፣ ከአንድ አቋም ላይ መድረሱ ታወቀ፡፡ ነገ በይፋ ለህዝብ ይገለጣል ተብሏል፡፡

ቤተክርስቲያኒቱን በመከፋፈል በሂደት ሀገር ለመበትን የሚደረገውን ሩጫ አውግዟል፤ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከግለሰቦችና ቡድኖች ከፖለቲካ እና ከኢኮኖሚ ጥቅመኝነት እጅግ የላቀ መለኮታዊና መንፈሳዊ ሚና የተሸከመች፣ አቃፊና አካታች ሩቅ ተጓዥ የህዝበ-ክርስቲያን ቤት ናት ብሏል- ቅዱስ ሲኖዶስ፡፡

ቅድስት ቤተ-ክርስቲያን ለተደቀኑባት አካባቢያዊ፣ ክልላዊ እና ዓለማቀፋዊ ተግዳሮቶች ሌሎች ተጨማሪ ጥፋቶች እንዳይከሰት ግራ-ቀኙን በመቃኘት ከስሜት በራቀ መንገድ መንፈሳዊ መፍትሄዎችን እየሰጠች ችግሮችን እየተሻገረች መለኮታዊ ሚናዋን ትወጣለች ያሉን የቤተክህነት የዜና ምንጮች፣ በየጊዜው የሚነሱባትን ጊዜያዊ እክሎች፣ ችግሮች፣ መሠናክሎች፣ አሻጥሮች ሁሉ በእግዚአብሔር እርዳታ፣ በመንፈሳዊ እርምጃዋ እየተሻገረች ወደ ፊት ትራመዳለች ብለዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ትላንት ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓ.ም በወቅታዊ የቤተክርስቲያኒቱ ተግዳሮቶች እና ተጓዳኝ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ በአስቸኳይ ተሰብስቦ፣ በአንድ የመፍትሄ አቋም ላይ ከስምምነት ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዕለቱ በጉዳዩ ላይ ለብዙኃን መገናኛ ይሰጣል የተባለው ጋዜጣዊ መግለጫ ወደ ነገ የተሻገረ ሲሆን፣ ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በዝርዝር ይፋዊ መግለጫ ይሰጥበታል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዓርብ ነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም እነ ቀሲስ በላይ ከሲኖዶስ እውቅና ውጪ ቤተክርስቲያኒቱን ለመከፋፈል የኦሮሚያ ቤተክህነት ጽ/ቤት ለማቋቋም የሚያደርጉትን ከፋፋይ እኩይ ድርጊቱን መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆመው ጋዜጣዊ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com