የዐራተኛው ፓትርያርክ በዓለ ሲመት ነገ በድምቀት ይከበራል

Views: 98

– መንፈሳዊያን እንግዶች ተጋብዘዋል
– ታሪካዊነቱ ይጎላል ተብሏል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዐራተኛው ፓትርያርክ የሆኑት የአቡነ መርቆሪዮስ በዓለ ሲመት፣ ነገ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ በቤተክህነት ጊቢ በድምቀት ይከበራል ተባለ፡፡

የፓትርያርኩ በዓለ ሲመት ከ29 ዓመት በኋላ በመንበራቸው ሲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሆን ነው የቤተክህነት ምንጮች ለኢትዮ-ኦንላይን ያስታወቁት፡፡

የዐራተኛው ፓትርያርክ የአቡነ መርቆሪዮስ 31ኛው የበዓለ ሲመታቸው ቀን እጅግ ታሪካዊ እንደሚሆን፤ መንፈሳዊያን እንግዶች መጋበዛቸውን የገለጹት የኢትዮ-ኦንላይን የቤተክህነት ምንጮች፤ በዓለ ሲመታቸው በደርግ መንግሥት የመጨረሻዎቹ ጊዜያት በይፋ ለመጨረሻ ጊዜ እንደተከበረ ገልጸው፤ ሆኖም፣ በህወሓት/ኢህአዴግ ፖለቲካዊ አሻጥርና ጣልቃ ገብነት ከዚያ በኋላ በብጹእ አባቶች ታስቦ እንጂ ተከብሮ እንደማያውቅ ነው የገለጹልን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዐራተኛው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዮስ እና ተሰዳጁ ሲኖዶስ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በመሩት እርቀ ሠላም ከሥደት ከተመለሱ ከአንድ ዓመት በኋላ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በድምቀት ይከበራል ተብሏል፡፡

ባለፈው ዓመት በብጹእ አባቶች እና በተወሰኑ ምዕመናን በፓትርያርኩ መኖሪያ ቅጽር ጊቢ በዓለ ሲመታቸው ታስቦ መዋሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቃል-ዓዋዲ (ዶግማ) መሠረት፣ ፓትርያርክ በሕይወት ካላለፈ በቀር አይሻርም፤ ሌላ ፓትርያርክም አይሾምም፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com