ኮንዶሚኒየሞቹ ይጮኻሉ

Views: 198

በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነቡት የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተዳደር በሥርዓት የተዘረጋ አደረጃጀት እና አሰራር ባለመኖሩ፣ ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች ከተላለፉ በኋላ ያለው ሁኔታ ትኩረት አልተሰጠውም የሚለን የአዲስ ኦንላይን ጸሐፊ ሐብቴ ታደሰ፣ አንድ ወጥ የሆነ የአሰራር እና አደረጃጀት ሥርዓት ተዘርግቶላቸው ተገቢው ክትትል ካልተደረገላቸው፣ በቀጣይ የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶች ወደ ዘመናዊ የተጎሳቆሉ አካባቢዎች (Modern Slum Areas) የማይቀየሩበት ምንም ምክንያት የለም በማለት ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ የሚከተለውን አቅርቧል፡፡

በኢትዮጵያ ብዙም ያልተለመደው በጋራ ሕንፃ ላይ በጋራ የመኖር ልምድ በመስፋፋት ላይ ቢገኝም፣ ከከተማ እና ቤት ልማት ሚንስቴር መ/ቤት የተገኙ ሰነዶች፣ ከጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶች ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች፣ እሮሮዎች እና ስጋቶች አዘውትረው እንደሚሰሙ ይጠቁማል፡፡ በቀጣይ የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶች ጋር በተያያዘ፣ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሁሉ፣ እስካሁን ድረስ  ከተፈጠሩ ችግሮች ጋር በተያያዘ ደረጃ በደረጃ ግንዛቤ በመፍጠር በዘለቄታዊነት መፍትሄ መሻት ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው፣ በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶች በዋናነት ለተጠቃሚዎች የሚተላለፉት በዕጣ ነው፡፡ ቤቶች በዕጣ በሚተላለፉበት ወቅት ነዋሪዎች የሚደርሳቸው ቤት በእድል ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ በአንድ ሕንፃ ውስጥ ቤት የሚደርሳቸው ሰዎች የተለያየ ባህርይ እና የአኗኗር ዘይቤ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች ከተላለፉ በኋላ እያጋጠሙ ያሉ ችግርች በርካታ ናቸው፡፡

መንግስት፣ የተናጠል ብሎም የጋራ የሆኑ ችግሮችን ለመቆጣጠር እና ለማስወገድ በጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎችን መሰረት ያደረገ የጋራ ሕንፃ ቤት ባለቤትነት አዋጅ ቁጥር 370/1995 ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የጋራ ሕንፃ ቤት ባለቤቶች በማህበር ተደራጅተው ሕንፃቸውን እና አካባቢያቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ ቢደረግም፣ በሚፈለገው ደረጃ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንዳልቻሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከሚ/ር መስሪያ ቤት የተገኙ ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፣ በጋራ ሕንፃ መኖሪያ አካባቢዎች የፀጥታ፣ የፅዳት (በተለይ ከፍሳሽ ቆሻሻ ጋር የተያያዙ)፣ እና ከኢትዮጵያውያን ባህል ጋር የሚቃረኑ ተግባራትን ጨምሮ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ የሕንፃዎቹ የውጪ ግድግዳዎች እና አረንጓዴ ቦታዎች በዲሽ ተሞልተዋል፡፡ ለንግድ አገልግሎት የተከፈቱ ሱቆችም ቢሆኑ ከፍተኛ ጩኸት ይለቃሉ፡፡ ከኮሪደር አጠቃቀም፣ ከህንፃ እድሳት ወዘተ… ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አሁንም የነዋሪው ችግር ሆነው ቀጥለዋል፡፡

በጋራ መኖሪያ ሕንፃ አካባቢ የተሠሩት የጋራ መጠቀሚያ ሕንፃዎች የነዋሪዎች ባህላዊ ፍላጐቶችን ለማስተናገድ ያለሙ ናቸው። የጋራ መጠቀሚያ ቤቶቹ ጥቅም ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤት ላይ ለማከናወን የሚከብዱ ባህላዊ ሥራዎችን ማለትም እንደ እርድ፣ የልብስ ማጠብ፣ እንዲሁም ብዛት ያላቸው ምግቦችን ማብሰል፣ ዕድር እና የመሳሰሉ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ የሚጠቅም ነው። ሕንፃዎቹ በአይነታቸው ራሳቸውን ችለው የቆሙ በጋራ ሕንፃ አካባቢ በሚገኙ ክፍት ቦታዎች ላይ የተገነቡ ናቸው። ምንም እንኳን የጋራ መጠቀሚያ ቤቶቹ የአሰራር ሁኔታ በደንብ የታሰበበት ቢሆንም፣ ነዋሪዎቹ ከሰፈሩ በኋላ፣ እነዚህን የጋራ መጠቀሚያ ቤቶች የማስተዳደር ሥራ አስቸጋሪ መሆኑ፣ የጋራ መጠቀሚያ ሕንፃ አጠቃቀም በተመለከተ የተቀናጀ ሥራ አለመኖሩን ያመለክታል፡፡ አንዳንድ የጋራ መጠቀሚያ ሕንፃዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለሌላ አገልግሎት ተከራይተዋል፡፡

በነዚህ አካባቢዎች፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና አገልግሎትን የሚያስተባብረውም ሆነ ወጪውን የሚሸፍነው የከተማው አስተዳደር ነው። የመሰረተ ልማቱ መንገድ፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያ፣ የእግረኛ መንገድ እና አረንጓዴ ቦታዎችን ያካተተ ሲሆን፣ አገልግሎቱም የውኃ፣ ኤሌክትሪክ፣ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ቤት የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የፍሳሽ ማስወገጃን የሚያጠቃለል ነው። ለቅድመ ግንባታም ሆነ ድህረ ግንባታ የሚያስፈልገው መሠረተ ልማት በሚመለከታቸው የመሠረተ ልማት ዘርፍ መ/ቤቶች እንዲቀርብ የተደረገ ቢሆንም፣ በተቀናጀ ሁኔታ በማቅረብ ረገድ እጥረቶች ይታያሉ፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ በቅድሚያ የተፈተሸው፣ የሰላም፤ ፀጥታ እና ደህንነት ሁኔታ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው፣ ሰላም እና ጸጥታ ለሰው ልጅ ኑሮ ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ በቀዳሚነት ይመደባሉ፡፡ በተለይ ብዙ ህዝብ በአንድ ላይ ተሰብስቦ በሚኖርበት እንደ የጋራ ሕንፃ መኖሪያዎች አካባቢ ያለው ሰላም እና ፀጥታ እጅግ በጣም አስተማማኝ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ በተጨባጭ እንደሚታየው በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ከሰላም እና ፀጥታ ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

ከዚህ በመነሳት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ በአትኩረት ቡድን አማካይነት በተደረገ ውይይት ወቅት ከተነሱት ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፡- ዝርፊያ እና በአንዳንድ ሳይቶች ህይወት እስከ ማጥፋት የደረሰ የጸጥታ እና ደህንነት ችግር ተከስቷል፡፡ ወጣት ሴቶች በቡድን በመከራየት አላስፈላጊ ስራዎችን ያከናውናሉ፣ ቤቶችን በመከራየት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ከማከናወን ጀምሮ፣ ለህጻናት፣ ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች ደህንነት ጥበቃ የሚደረግበት አሰራርም የሌለ በመሆኑ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

በየሳይቱ በርካታ የንግድ ቤቶች በመኖራቸው፣ በእነዚህ ንግድ ቤቶች ውስጥ የመጠጥ ቤት፣ የምሽት ጭፈራ ቤቶች፣ ህገወጥ ጫት ቤቶች ይገኙባቸዋል፤ በመሆኑም ያለምንም ገደብ መብራት ቢጠፋ እንኳን ጀኔሬተር በመጠቀም ለሊቱን ሙሉ ሲጨፈር ያድራል፤ በዚህም ነዋሪው በከፍተኛ ደረጃ ዕረፍት የማጣት እና የመረበሽ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ ችሏል፡፡

በአንዳንድ ሳይቶች አካባቢ ከሚገኙ ፋብሪካዎች የሚወጡ ኬሚካሎች፣ በግቢው ውስጥ ካሉ የብረት እና እንጨት ሥራ ድርጅቶች የሚወጡ ድምፆች፣ ከቀለም ጋር የተቀላቀሉ ኬሚካሎች፣ ከብሎኬት ምርት እና ከአሸዋ ሽያጭ ሥራዎች ጋር በተያያዘ የሚወጡ ብናኞች፣ በግቢው ውስጥ ከሚያልፉ መኪኖች እና ሌሎች የንግድ ቤቶች የሚወጡ ድምፆች የሚረብሹ ናቸው፡፡

ዕቃን ከመጫን እና ከማውረድ ጋር ተያይዞ በአካባቢው የሚኖሩ ወጣቶች የግድ መጫንም ሆነ መውረድም ያለበት በእኛ ብቻ ነው በሚል ከፍተኛ ገንዘብ የመጠየቅ ሁኔታ የሚስተዋልባቸው ቦታዎችም አሉ፤ በአንዳንድ ሳይቶች ለምሳሌ በሰሚት የአካባቢው ገበሬዎች ከብቶችን ወደ ግቢው በማሰማራታቸው የተነሳ  ግጭት የተፈጠረበት ጊዜ ነበር፡፡

የአንዳንድ ኮንዶሚኒየም ሳይት ግቢው አጥር ስለሌለው ጅቦች እያስቸገሩ ናቸው፤ አብዛኞቹ የኮንደምኒየም ሳይቶች ሰፊ ቢሆኑም፣ ይህንኑ ያገናዘበ የፖሊስ ሰራዊት አልተመደበም፤ የየሳይቱ ጥበቃዎች አብዛኛዎቹ ስልጠና ያልወሰዱ እና ደካማ በመሆናቸው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም፣ እንዲያውም ለጥበቃው ሌላ ጥበቃ የሚያስፈልገው ግቢ መኖሩ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከፅዳት ሁኔታ ጋር በተገናኘ ደግሞ፣ በአንድ የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶች ላይ በአማካይ ከ25 ያላነሱ አባውራዎች/እማውራዎች ይኖራሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተገነቡት እና እየተገነቡ ያሉት የጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶች ሳይቶች አንድ መቶ እና ከዚያ በላይ ሕንፃዎችን ያካተቱ ናቸው፡፡ ስለሆነም በአንድ ሳይት ላይ ከ2 ሺህ 500 በላይ አባውራ/እማውራ የሚኖር ሲሆን፣ በአማካይ አንድ ቤተሰብ አምስት አባላት ይኖረዋል ተብሎ ቢታሰብ እንኳ፣ በጥቅሉ 12 ሺህ 500 ነዋሪዎች በአንድ ሳይት ላይ እንደሚኖሩ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህም በየቀኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ደረቅ እና ፍሳሽ ቆሻሻ እንደሚመነጭ ያመለክታል፡፡

ፍሳሽ ቆሻሻ ብዙውን ጊዜ፣ ንፁህ ውኃ ለተወሰነ አገልግሎት ሲውል የሚፈጠር ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ አገልግሎት ላይ ከሚውለው ውኃ ከ70 እስከ 80 በመቶ ያህሉ ወደ ፍሳሽ ቆሻሻነት ይለወጣል፡፡ ይህም በመሆኑ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ አገልግሎትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ አገልግሎቱ ከማህበረሰብ ጤና ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ስለሆነ  ፍሻስ ቆሻሻን ስርዓት ባለው መንገድ መሰብሰብ፣ ማጓጓዝ፣ ማጣራት፣ መልሶ መጠቀም የሚያስፈልግ ሲሆን፣ የማይፈለገውን ደግሞ አካባቢውን በማይበክል መልኩ ማስወገድ፣ በዚህም የማህበረሰቡን ጤና እና ደህንነት ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ይህ በከፍተኛ መጠን የሚመነጭ ቆሻሻ የሚወገድበት ሥርዓት ካልተዘረጋ ለነዋሪዎቹም ሆነ ለአካባቢው ህብረተሰብ ከፍተኛ ችግር ይፈጥራል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተደረገው ውይይት የሚከተሉት ዋና ዋና ችግሮች ተነስተዋል፡- የፍሳሽ ማጠራቀሚያ ሴፕቲክ ታንኮች ቶሎ ቶሎ መሙላት፣ የመፈንዳት እና አካባቢውን የመበከል፣ ለማስመጠጥ ወረፋ መብዛቱ ተጠቅሷል፡፡ አንዳንድ ሳይቶች ላይ ደግሞ ለምሳሌ የገላን ሳይት ሴፕቲክን በተመለከተ ታንኩ ሲበላሽ ከተለመደው የተለየ ክህሎት ስለሚጠይቅ በቀላሉ አይጠገንም፤ ሲሞላም ለመምጠጥ ስለሚያስቸግር ይደፈናል ይህ ደግሞ በመገንፈል ችግር እየፈጠረ ነው፡፡

በሌላም ከፍሳሽ ማጠራቀሚያ የመሙላት እና የመፈንዳት ባህርይ ከሚያጋጥም ሁኔታ ጋር በተያያዘ፣ ከፍተኛ የሆነ ሽታ ስላለው ነዋሪዎቹ በተለይም ከፍሳሽ ማጠራቀሚያው አካባቢ ያሉት ለመተንፈሻ አካል በሽታ እየተዳረጉ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ሳይቶች፣ መስኮትም ከፍተው መቀመጥ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

የጎርፍ ብሎም የዝናብ ውኃ መሰብሰቢያ እና ማስወገጃ መስመሮች በአግባቡ ስለማይያዙ በየጊዜው ይደፈናሉ፣  ከዚህም የተነሳ የአካባቢ ብክለት ይከሰታል፤ በተጨማሪም የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን በተመለከተ በአንዳንድ ሳይቶች ቆሻሻ ለመሰብሰብ የተደራጁ ማህበራት በሳምንት አንድ ቀን፣ ሁለት ቀን እንዲሁም በየ15 ቀኑ እንደሚሰበስቡ የተገለጸ ቢሆንም፣ ማህበራቱ ፕሮግራማቸውን ጠብቅው ስለማይመጡ፣ አንዳንድ ጊዜ ቆሻሻ አላግባብ በመከማቸት ሽታ እና ተባዮችን በማፍራት በተለይም ልጆች ሲጫወቱ ጤናቸው እየታወከ መሆኑ ተብራርቷል፣ የደረቅ ቆሻሻ አሰባሰቡ ዘመናዊ ካለመሆኑ የተነሳ ቆሻሻ በገንዳዎች ዙሪያ እና በቱቦዎች አካባቢ ተዝረክርከው ይገኛሉ፣ ከዚያም በላይ አንዳንድ ነዋሪዎች ቆሻሻ አላግባብ በመስኮት ይጥላሉ ይህም በተለይም ታችኛው ወለል ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ ብክለትን እየፈጠረ መሆኑ ተስተውሏል፡፡፣

የአረንጓዴ፣ መዝናኛ እና መኪና ማቆሚያ ቦታዎች ልማት በተመለከተ ሰነዱ ሲያብራራ፣ የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎች ሲገነቡ በተናጠል ከሚያዙት ቤቶች በተጨማሪ፣ ለአረንጓዴ ልማት እና ለአደባባይ የሚውሉ ቦታዎች አሏቸው፡፡ በመሆኑም ለአረንጓዴ ልማት እና መሰል አገልግሎት የሚውሉ ቦታዎችን በተገቢው መንገድ ማልማት እና መጠቀም፣ የአካባቢ ደህንነትንም ሆነ ጤንነትን ከመጠበቅ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው፡፡

ከዚህ አንፃር ነዋሪዎች እና የቤት ባለቤቶች ማህበራት ተቀናጅተው በማልማት ረገድ ምን እየተሰራ እንደሆነ እና ምን አይነት ችግር እንዳጋጠመ በተደረገው ውይይት የሚከተሉት ዋና ዋና ሃሳቦች ተነስተዋል፡- የኮንዶሚኒየም ሳይቶች ፕላን እና ካርታ ስለሌላቸው ትክክለኛ ወሰኑን ለማወቅ እና ለማልማት አስቸጋሪ ሁኔታዎች አጋጥመዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የወረዳ አመራሮች ሳይቀሩ፣ የኮንዶሚኒየም ሳይት ክልል ውስጥ ያሉ ቦታዎችን ለሥራ ዕድል ፈጠራ በሚል ሰበብ ለመውሰድ እና ነዋሪው የመኖሪያ ቤቱ ሕንፃ ካረፈበት ቦታ ውጭ መብት እንደሌለው አድርጎ የመቁጠር ሁኔታዎች እየተለመዱ ናቸው፡፡

በሌላም በኩል ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ የምልስ አፈር እና ሌሎች ተረፈ ምርቶች ያለመነሳታቸው አካባቢውን ለማጽዳትም ሆነ ለማልማት አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጥር ችሏል፤ ለአረንጓዴ ልማት የተለዩ ቦታዎች የመኪና ማቆሚያ ሆነዋል፡፡ ለመኪና ማቆሚያ ተብሎ በስርዓቱ የተዘጋጀ ቦታ ካለመኖሩ የተነሳ መኪኖች፣ የእግረኛ እና የመኪና መተላለፊያ መንገዶችን ጨምሮ  በየቦታው ይቆማሉ፣ የሚቆጣጣራቸውም የለም፡፡ በሁሉም ሳይቶች የህጻናት መጫወቻ ቦታዎች አልተዘጋጁም፤ ይህ ደግሞ በተተከሉ ሣሮች እና ችግኞች ላይ ችግር መፈጠሩ ተመልክቷል፡፡

በመጨረሻም የህንጻ ደህንነት፣ ዕድሳት እና ጥገና ሁኔታ ጋር በተገናኘ ደግሞ ሰነዱ ላይ እንደሰፈረው፣ የጋራ ሕንፃ ነዋሪዎች ተረጋግተው ያለስጋት ለመኖር ሕንፃው ጥራት ያለው እና ደረጃውን የጠበቀ መሆን ያለበት ቢሆንም፣ የህንፃውን ደህንነት ተቀናጅቶ በታቀደ መልኩ መጠበቅ እና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መጠቀም ግድ ይላል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተደረገው ውይይት የሚከተሉት ጉዳዮች ተነስተዋል፡- የሕንፃዎቹ ግንባታ የጥራት ችግር ያለባቸው በመሆኑ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ከዋናው የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ጋር ያለመገናኘት፣ የዝናብ ውኃ ማውረጃ ጎረንዳዮዎች ቶሎ መበላሸት እና የዝናብ ውኃው በህንፃው ላይ መፍሰስ፣ የጣራ ማፍሰስ፣ ለመታጠቢያ ቤት እና ለማዕድ ቤት የሚገጠሙ ዕቃዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆን፣ የተዘረጉት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኮንድዩቶች የኤሌክትሪክ ገመድ የላቸውም፡፡

የቤቱን ውስጥ ለማስዋብ እና ለማስፋፋት በሚል ክፍሎች ይቀላቀላሉ፣ በሮች ይቀየራሉ በዚህም ህንፃው ለጉዳት የሚዳረግበት ሁኔታ ያለ ሲሆን፣ በአንዳንድ ሳይቶች በሕንፃው ላይ ዲሽ ለመስቀል፣ የልብስ ማስጫ ለመዘርጋት እና ለመሳሰሉት ሲባል ህንፃውን የመብሳት ሁኔታ መኖሩ ተስተውሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፣ ግድግዳን እየበሱ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመርን በውጪ በኩል ማድረግ፤ የተዘረጉት የውኃ መስመሮች በአግባቡ ያልተገጠሙ መሆን፣ የጋራ መጠቀሚያዎች በሚፈለገው መጠን ያለመገንባት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡

በአንዳንድ ሳይቶች ለምሳሌ በገላን እና ኮሜት ሳይቶች ላይ ከባድ የጭነት መኪኖች ስለሚያልፉ የህንፃውን መሰረት ሊያዛቡት እንደሚችሉ ተገልጿል፣ በተለይ ኮሜት ጀርባ የድንጋይ ማውጫ ካባ በመኖሩ ድማሚት ሲፈነዳ ህንፃዎቹ አልፎ አልፎ የመንቀጥቀጥ ሁኔታ እንደሚያጋጥማቸው በሰነዱ ተጠቁሟል፡፡

አንዳንዴ ሕንፃው ላይ የመውቀጥ፣ የመከትከት እና የመሳሰሉት ህገ-ወጥ ተግባራት ይከናወናሉ በመሆኑም ህንፃው ለጉዳት ይዳረጋል፣ በመንግስት ያልተላላፉ ቤቶች በህገ ወጥ መንገድ ይሰበራሉ፣ ይከራያሉ፣ ሕንፃዎችን የሚጠግን አካል ማን እንደሆነ በግልፅ አለመታወቁ በዋናነት ከተጠቀሱት መካከል ይገኙበታል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንፃ ግንባታ ሂደት፣ ለከተሞች እድገት እና ህዝብን እርስ በርስ ከማቀራረብ አንጻር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንፃ ግንባታ በስፋት እየተካሄደ ነው፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የቤት ባለቤት ሆነዋል፡፡ በአንድ መንደር በመሰባሰባቸው አካላዊ ቅርርባቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የአንዱ ቤት ከአንዱ ቤት አይርቅም፡፡ በአንድ ሕንፃ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ በአንድ ወለል ላይ የሚገኙ፣ በአንድ መወጣጫ ወይም አሳንሰር የሚጠቀሙ፣ ሲወጡ እና ሲገቡ የሚገናኙ ሰዎች ናቸው፡፡

የማህበራዊ አደረጃጀት እና ትስስር/ግንኙነት ሁኔታን በተመለከተ ደግሞ ሰነዱ እንዲህ ያትታል፡፡ የጋራ  መኖሪያ ቤቶች ሕንፃ የመቀራረብን ጸጋ ይዞ መምጣቱ መልካም ነገር ቢሆንም፣ በተቀራረቡት ነዋሪዎች መካከል ያለው የመተሳሰብ ወይም የመተዋወቅ ርቀት ግን መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመለክቶ በአዲስ አበባ በተለያዩ ሳይቶች በተደረገው ውይይት በርካታ ችግሮች ተነስተዋል፡፡ ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ ያህል፡- ሁሉም የራሱን በር ዘግቶ ስለሚኖር ነዋሪው እርስ በርሱ አይተዋወቅም፤ በጋራ ችግሮቹ ላይ አይነጋገርም፡፡ አንዱ የአንዱን የቤተሰብ፣ የሥራ፣ የመሳሰሉትን ሁኔታዎች አያውቅም፣ ለማወቅም አይጥርም፤ በሀዘንም ሆነ በደስታ አይደራረስም፣ በተለይ ይህ ችግር በወንዶች በብዛት ይስተዋላል፡፡ አንዱ ስለሌላው አይጨነቅም፤ ለዚህም መገለጫው የጋራ መተላለፊያ ስፍራን መዝጋት፣ የራሱን ቆሻሻ ጠርጎ በጎረቤቱ ደጃፍ ላይ ማስቀመጥ/መጣል፣ ከመጠን በላይ የሆነ የሙዚቃ፣ የመዝመሩ/መንዙማ፣ የሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን ድምጽ ማሰማት እና  አብሮ መጮህ፣ ፎቅ ላይ ቡና መውቀጥ፣ ከባድ ድምጽ ያላቸውን ነገሮች ወለል ላይ መጎተት… ወዘተ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያውያን ባህል የሆኑት እንደ እድር፣ ዕቁብ፣ ማህበር/ሰንበቴ የመሳሰሉት ማህበራዊ መድረኮች እየተመናመኑ ናቸው፣ አንዳንድ ሳይቶች ላይ ጨርሶውኑ ጠፍተዋል፡፡ በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤቶች ሰፈር ውስጥ ባሉት ነዋሪዎች መካከል ያለውን ማህበራዊ እና ሥነ-ልቡናዊ ርቀት ሌቦች እና ሌሎች ህገ ወጦች በደንብ ያውቁታል፡፡ በዚህም የተነሳ የተቆለፈውን በር በገሃድ እየፈለቀቁ ነዋሪውን ይዘርፉታል፡፡

የጋራ መጠቀሚያዎች አጠቃቀም እና አስተዳደር ሁኔታ

በጋራ ሕንፃ ቤት ባለቤትነት አዋጅ ቁጥር 370/1995 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ እንደተገለጸው፣ የጋራ መጠቀሚያ ማለት በተናጠል ከተያዙት ቤቶች ውጭ ማናቸውም የሕንፃው አካል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማንኛውም የጋራ መኖሪያ ሳይቶች ላይ ከህንፃው አካል ውጭም ማብሰያ/ማጠቢያ፣ ማረጃ፣ የመኪና ማቆሚያ እና የመሳሰሉት የጋራ መጠቀሚያዎች ይገኛሉ፡፡ በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 9 ንኡስ አንቀፅ 2 ላይ በጋራ መጠቀሚያዎች የመጠቀም መብት የማይከፋፈል እና ከእያንዳንዱ ቤት የባለቤትነት መብት ጋር የማይነጣጠል መሆኑ ተደንግጓል፡፡

በዚህም መሰረት አሁን ያለው የጋራ መጠቀሚያዎች የአስተዳደር እና አጠቃቀም ሁኔታ ምን እንደሚመስል ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በዋናነት የሚከተሉት ጉዳዮች ተነስተዋል፡- አብዛኞቹ የጋራ መጠቀሚያ ሕንፃዎች ከዓላማቸው ውጪ (ምሳሌ ለትምህርት ቤት፣ ለክሊኒክ፣ ለፋርማሲ፣ ለሱቅ……ወዘተ) ለሌላ ወገን እንዲከራዩ ተደርጓል፤ የጋራ መተላለፊያ ኮሪደሮችን መዝጋት፤  የጋራ የሆኑ ክፍት ቦታዎችን፣ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን እና አረንጓዴ ቦታዎችን በግል አጥሮ መያዝ፤ የጋራ ወጪዎችን ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆን፤ መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ አለመጠቀም፤ ለምሳሌ የውኃ መስመሮችን መዝጋት ወይም ማበላሸት፣ የፍሻሽ ማስወገጃ ቱቦዎችን መዝጋት ወዘተ ናቸው፤ የጋራ መጠቀሚያ ሕንፃዎችን የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያበቁ/ያረጁ ዕቃዎች ማከማቻ ማድረግ፣ ሕንፃዎቹ ሲበላሹ አለመጠገን በዋነኝነት ከተጠቀሱት መካከል ይገኙበታል፡፡

ማጠቃለያ

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንፃን አስመልክቶ የሚታዩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ከቤት ባለቤቶች ማህበራት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመቀነስ እና በመቅረፍ፣ የመኖሪያ ቤት ባለቤቶች ማህበራትን  ፍትሐዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ውጤታማ እና ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ለማገዝ እና ለማጠናከር ይቻል ዘንድ፣ ወጥ የሆነ የጋራ ሕንፃ ቤቶች አስተዳደር እና አጠቃቀም ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ የቤት ባለቤቶች ማህበር የአደረጃጀት ሁኔታ ወጥ በሆነ መንገድ የኗሪዎቹን ቁጥር  መሰረት አድርጎ ተደራሽ በሚሆንበት መንገድ የሚደራጅበት ሁኔታን መፍጠር፣ በተላለፉ ቤቶች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ በተለያዩ ዘርፎች ለማደራጀት እና የቤት ባለቤቶች ማህበራትን ለማቋቋም እና ለማጠናከር የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያካተተ ስቲሪንግ ኮሚቴ የሚቋቋምበት ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com