ዜና

የኩላሊት ጠጠርን ሳይጠጥር ነው ማስወገድ!

Views: 1327

(ምሥል አንድ     በቀኝ ያለው ኩላሊት ጠጠር የጀመረው)

(ምሥል ሁለት በ 2.5 ኢንች ውስጥ የሚታዩ ከፍ ያሉ ጠጠሮች)

መግቢያ

ኩላሊቶች በሰውነት ውስጥ በጣም ጠቃሚ ሥራ አላቸው፡፡ ዋናው ሥራ ትርፍ ፈሳሽ እና ቆሻሻ ነገሮችን በሽንት መልክ ማስወገድ እና በሰውነት ውስጥ የኬሚካል ሚዛን እንዲጠበቅ መርዳት ነው፡፡ ማንም ያለ ኩላሊት በሕይወት መኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ የኩላሊትን ጤንነት መጠበቅ ለሕይወት ግዴታ ነው፡፡  ቢሆንም አሳዛኙ እውነት አብዛኛው የዘመናዊ ኑሮ ዘይቤ በክፉ ሁኔታ የኩላሊትን ጤና የሚፈታተን ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡

በዚህ የተነሳ በዚህ ዘመን የኩላሊት ሕመም፣ የኩላሊት ጠጠር፣ ስንት ፍዳ መከራ እያስከተለ እንዳለ ይታወቃል፡፡ የኩላሊት መዳከም፣ የኩላሊት መውደቅ፣ ኩላሊትን ማጠብ፣(ዲያሊስስ ሕክምና)፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላ፣ኩላሊት ልገሳ፣  ወዘተ የሚባሉ ጉዳዮች የዘወትር ዜና ሆነዋል፡፡

ብዙ ጊዜ ኩላሊት በአንድ ቀን እና በፍጥነት፣ አይደክምም፣ አይወድቅም፡፡ በጊዜ ሂደት የሚመጣ ችግር ነው፡፡ በጣም ብዙ ነገሮች በቤታችን ውስጥ እና በአመጋገባችን ማስተካከል የሚገቡን አሉ፡፡ ጠጠሮቹን እንዳይፈጠሩ መከላከል፣ ከተፈጠሩም አድቅቆ ማስወገድ፣የኩላሊት ችግር ሥር ሳይሰድ፣ ጠጠሩም ሳይጠጠር መከላከል ይበጃል፡፡

የበሽታው ምልክት፣

“የኩላሊት ወይም የፊኛ ጠጠር የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት ብዙውን ጊዜ በታችኛው የጀርባ ክፍል ላይ ወይንም በጐን ላይ ወይም ታችኛው የሆድ ክፍል ላይ አስጨናቂ እና አጣዳፊ ህመም ያስከትላል” ይላል ዴቪድ ዋርነር  ማጣቀሻ አንድ ብዙ የህመም ዓይነት ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ምልክት ያሳዩ ይሆናል፤ ስለሆነም  በምርመራ የኩላሊት ጠጠር መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

የኩላሊት ጠጠር እንዴት ይፈጠራል፣

የኩላሊት ጠጠር፣ በአመጋገብ፣ በሌሎች ብዙ ውስብስብ ችግሮች ጭምር ይፈጠራል፡፡ በዚህ በሽታ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች በርካታ አሉ፡፡ ለምሳሌ   በጥላሁን አለልኝ እና በየነ ጴጥሮስ የተደረገው የምርምር ውጤት በሪሰርች ጌት መረጃ መረብ ላይ ይገኛል፡፡ ማጣቀሻ ሁለት

የጠጠሮች ዓይነት እና የበሽታው ስፋት እንዲህ ተጠቅሷል፡፡

 1. የካልስየም ኦክሳሌት/ፎስፌት ጠጠሮች (Calcium Stones: Calcium Oxalate and Calcium Phosphate about 80%)
 2. የማግኒዝየም አሞኒየም ፎስፌት ጠጠሮች    (Magnesium Ammonium Phosphate Stones  10–15%)
 3. ዩሪክ አሲድ ጠጠሮች (Uric Acid Stones or Urate. 3–10% of all stone types)

1.  የኩላሊት ጠጠር እና የምግብ ምርጫ

ማሳሰቢያ ቀጥሎ ያለው ምክር ስለ ምግብ ምርጫ ነው፡፡ ከሚሰጠው መደበኛ የሕክምና አገልግሎት እና ምርመራ ጋር ምክሩን ጎን ለጎን ማካሄድ እንጂ የምግብ ምርጫ ብቻውን ሕክምናውን አይተካም፡፡ ጠጠሮቹ ሙሉ በሙሉ ከተወገዱ በኋላ  በጥንቃቄ ወደ መደበኛው ምግብ መመለስ ይቻላል፡፡ የሚከለከሉት ምግቦች ሁሌም አይደለም፡፡

1.1 .  የኩላሊት ጠጠር እንዲፈጠር ወይም እንዲባባስ የሚያደርጉ ምግቦች

ኪድኒ ኦርግ የተባለው እንደሚከተለው ያስረዳል፡፡ ማጣቀሻ ሶስት

 • ኦክሳሌት (Oxalate) የተባለ ንጥረ ነገር በከፍተኛ መጠን የያዙ፣ እና
 • ሶዲየም እጅግ የበዛባቸው ምግቦች ሲሆኑ፣

ጉዳዩን እጅግ አስከፊ የሚያደርጉት ደግሞ ከእነዚህ በኦክሳሌት፣ እና በሶድየም ይዘት ከፍተኛ የሆኑ ምግቦች ጋር ተመጣጣኝ የሆነ

 • በካልስየም፣ በፕሮቲን እና በአሰር ይዘት የዳበሩ ምግቦች በበቂ መጠን አብሮ አለመመገብ እና በቂ ውሃ ወይም ፈሳሽ አለመጠጣት ናቸው፡፡

1.2. የኦክሳሌት ይዘታቸው የበዙቱ የትኞቹ ናቸው

የአትክልት አይነት ከሆኑት እነዚህ ይበልጥ በኦክሳሌት ይዘት ከፍተኛ ናቸው፡፡፣

ሩባርብ ዘንግና ቅጠል

እስፒናች ቅጠል

ቆስጣ ቅጠል

ቲማቲም ፍራፍሬ

 

 

የቀይ ሥር ቅጠሉ፣

ስኳር ድንች ሥር

ድንች ሥር፣

መደበኛው ቀይ ሻይ

ስኳር

ጎስቤሪ ፍራፍሬ፣

ካካዋ፣

ጥቁር ቤሪ፣

ሰሊጥ

የታሸጉ ጥራጥሬዎች፣

አቾሎኒ

ኦክራ

ቸኮላት

ሠንጠረዥ አንድ

2 . ቀድሞውኑ የኩላሊት ጠጠር እንዳይፈጠር የሚረዱ ነገሮች

 • ውሃን በበቂ መጠን መጠጣት፣
 • እነዚህን የኦክሳሌት ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑትን በመጠን መመገብ፣
 • ጨውና እና ስጋን በመጠን መመገብ፣
 • እስፒናች እና ቆስጣን እጅግ ከማብዛት ይልቅ ፣በማግኒዝየም የዳበሩ ነገር ግን ኦክሳሌት የሌላቸውን ተክሎች መመገብ እንደ ሰላጣ፣ ጎመን፣ የሳማ ቅጠል፣የዱባ ቅጠል፣ጥቅል ጎመን፣ አበባ ጎመን፣ ብሮኮሊ፣ እና የመሳሰሉትን ማዘውተር
 • ስኳር ድንች እና ድንች ከማብዛት፣ይልቅ ሌሎች ሥራሥር የሆኑ እንደ ካሮት፣ ቀይሥር፣ ጎደሬ፣ ካዛቫ፣ ሐረግ ቦዬ ወይም ዱባ፣ ዝኩኒ፣ ስኳሽ፣ቻዮቴን የመሳሰለትን ማዘውተር፣
 1. የኩላሊት ጠጠር መፈጠራቸው እንደታወቀ የሚረዱ ነገሮች

ከላይ የተነገሩትን ነገሮች በጣም ማስተዋል፣ (ደጋግሞ ላለመፃፍ)፤ 

የተፈጠሩትን ጠጠሮች በምርመራ መለየት፣ (ለምሳሌ በአልትራሳወንድ ምርመራ) ከላይ በምስል ሁለት ላይ እንደሚታየው፣ ጥቂት ትልልቅ ጠጠሮች ወይስ ብዙ ደቃቅ፤ ምን እንደሆኑ ማወቅ፡፡ እና በአግባቡ መታከም፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ጠጠሮቹ እስኪወገዱ ድረስ፤

 • የኦክሳሌት ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑትን ከምግብ ውስጥ ማስወገድ፤
 • በፎስፈረስ እና በፖታስየም ንጥረ ምግብ የበለፀጉ ምግቦችን መተው፣እንደ ስጋ ምግቦች፣ የዶሮ ስጋ፣ ጥራጥሬዎች፣ ጓንጉሌ     (እንደ አቾሎኒ)፣ የዱባ ፍሬ፣ የፈረንጅ ሱፍ፣ ያሉትን ማለት ነው፡፡
 • ጨው እና በጨው የተቀናበሩ ምግቦችን መተው፣
 • ስኳር፣ቀይ ሻይ፣ ቡና፣ አልኮል፣ ከምግብ ማስቀረት፣
 • የተፈቀዱትን የአትክልት ዓይነት አብስሎ፣ በጁስ ወይም በሻይ መልክ በደንብ መመገብ፣
 1. የኩላሊት ጠጠሮቹን ሊያሟሙ የሚችሉ ነገሮች

ከቀረቡት አማራጮች የቻሉትን ይጠቀሙ፡፡ ጠጠሮቹ ተሰባብረው እየወጡ እንደሆነ ሽንት ላይ ተከታትሎ ማየት ነው፡፡ መልካም እድል ጠጠር ለማስወገድ፡፡

 • በሶቢላ ቅጠል አሲቲክ አሲድ ይዟል፤ ይህም የኩላሊት ጠጠርን ለመሰባበር ይረዳል፡፡ በሶቢላ በጣም ጠቃሚ ንጥረ ምግብ ይዘትም አለው፡፡ ለኩላሊት ጤና በጣም ጥሩ ነው፡፡ ጁሱን ለማዘጋጀት 3ዐ ግራም ያህል ቅጠሉን መሸምጠጥ እና በጁስ ማሽን ወይም በሙቀጫ መውቀጥ ነው፡፡ ከዚያም በውሃ መበጥበጥ እና ማጥለል እና በማር ወይም እንዲሁ መጠጣት ነው፡፡ እስከ አንድ ወር በተከታታይ መጠጣት፡፡ ማጣቀሻ አራት
 • አፕል ሲደር ቪኒገር (ከአፕል የተዘጋጀ አቺቶ ማለት ነው)፡፡ አሲቲክ አሲድ አለው፡፡ ይህ ጠጠሩን ሊያሟሟ ዘንድ ይረዳል፡፡ ሁለት የሾርባ ማንኪያ አቺቶ በሁለት ሊትር ውሃ ማዋሃድ እና ቀኑን ሙሉ ጠጥቶ መጨረስ፡፡ እስከ ሁለት ሳምንት በቂ ይሆናል፡፡
 • ሎሚም አሲቲክ አሲድ አለው፡፡ ማለዳ ከአንድ እስከ ሶስት ሎሚ ጭማቂ በውሃ ላይ እያደረጉ ማር አክሎ ለሳምንታት መጠጣት፡፡

ኩላሊት መሳይ አደንጓሬ፣ የፍሬው ማቀፊያ ቅርፊት ደርቆ፣ ተሸክሽኮ፣ አንድ የቡና ስኒ በሶስት ሊትር ውሃ ለሰስ ባለ ሙቀት እስከ 5 ሰዓት መቀቀል፡፡ አንድ ሊትር የተክሉ ሻይ ይገኛል፡፡ ይህን አንድ ብርጭቆ በየ 6 ሰዓቱ መጠጣት፡፡ ለሳምንታት እንዲሁ መቀጠል፡፡

ኩላሊት መሳይ አደንጓሬ ተክል

 • ለአንድ ጊዜ አንድ የሾርባ ማንኪያ የአብሽ ዱቄት በግማሽ ሊትር ንፁህ ውሃ ላይ መነስነስ፤ እስከ 4 ሰዓት ማቆየት፣ ከዚያም አብሹን በማሽን ወይም በእጅ በደንብ መምታት ንፁህ የእርድ ዱቄት 1 የሻይ ማንኪያ እና 1 ሾርባ ማንኪያ ማር ጨምሮ መጠጣት፡፡ አብሽን  በተለመደው ዓይነት ጠዋት ብቻ ሳይሆን፤ በቀን እስከ ሶስት ጊዜ፣  ለሳምንታት መጠጣት፣ ማጣቀሻ አምስት

የኩላሊት ጠጠሮቹ እንዲሟሙ በሶቢላ ቅጠል፣ አፕል ሲደር አቺቶ፣ የሎሚ ጭማቂ፣የአደንጓሬ ቅርፊት ወይም አብሽ በሚጠጣበት  ጊዜ በቀን እስከ ሶስት ሊትር ንፁህ ውሃ በመጠጣት የሟሟው ወይም የደቀቀው ጠጠር በሽንት እንዲወገድ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 1. ኩላሊትን የሚያፀዱ መጠጦች

ጠጠሮቹን የማድቀቅ ፕሮግራም ላይ እያሉ እና ጠጠሮቹ ከተወገዱም  በኋላ  እነዚህን ኩላሊትን የሚያፀዱ መርሆች መከተል ጠቃሚ ነው፡፡

ጁስ መጠጦች

የአናናስ ጁስ፤

የጥሬ  ቀይ ሥር ጁስ፣

የሃብሃብ (ወተርሜሎን) ጁስ፣

የወይን ፍሬ ጁስ፣

የዝንጅብል ጁስ፣

የሴለሪ ቅጠል እና አንጓ ጁስ፣

የእሬት ጄል በማር ጁስ፣

የሮማን ፍራፍሬ ጁስ

ሠንጠረዥ ሁለት

ሻይ መጠጦች

እንደሻይ እየተፈሉ የሚጠጡ እና ኩላሊትን የሚያፀዱ ናቸው፡፡ እነዚህ የሻይ መጠጦች ደምንም የሚያጠሩ ናቸው፡፡

የእንስላል ተክል

የመቅመቆ ሥር ዱቄት

የሳማ ቅጠል

የሴለሪ ቅጠል

የልት ሥር፣

የከርከዴ ሻይ፣

የእንስላል ሙሉ ተክል የሎሚ ሳር፣

የናርዶስ ሳር፣

የዳንደሊዮን  ሥር፣

አረንጓዴ ሻይ

ሠንጠረዥ ሶስት

 1. ማዓዛማ ዘይት (essential oils)

መዓዛማ ዘይቶችን በጥንቃቄ መጠቀም ነው፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ዓይነት መዓዛማ ዘይቶች አሉ፡፡ በአገራችን ሁሉንም ማግኘት ባይቻልም እንኳ ያሉትን በአግባብ መጠቀም ነው፡፡ ለኩላሊት አንዲት ጠብታ አንድ ዓይነት መዓዛማ ዘይት ከሌላ ዘይት ጋር አደባልቆ ከላይ መቀባት ነው፡፡ ይህ የሕመሙን ጫና ይቀንሳል፣ ጠጠሮቹንም ለማድቀቅ ድጋፍ ይሆናል፡፡ እጅግ በብዙ ጥንቃቄ የኩላሊትን ጠጠር ለማድቀቅ በውሃ ላይ ተደርገው የሚጠጡም አሉ፡፡ ለጊዜው ከላይ ለመቀባት የሚውሉትን ጥቂት ምሳሌ ተመልከቱ፡፡

በውጪ አካል ላይ ለመቀባት የሚሆን መዓዛማ ዘይት  ማጣቀሻ አምስት

የሎሚ መዓዛማ ዘይት

 • ከሎሚ የተሠራውን መዓዛማ ዘይት አንድ ጠብታ፣ በአንድ ማንኪያ ወይራ ዘይት ላይ አደባልቆ በኩላሊት አቅጣጫ ከላይ በስስ መቀባት፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ መታጠብ፡

የሎሚ ሳር መዓዛማ ዘይት

 • ከሎሚ ሳር የተሠራውን ማዓዛማ ዘይት አንድ ጠብታ አንድ ሾርባ ማንኪያ ወይራ ዘይት ላይ መቀየጥ፣ ትንሽ ለብ አድርጎ መቀባት ነው፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ መታጠብ፡፡
 1. ሕክምና ላይ የደረሱት ማጣቀሻ አራት

ኩላሊት በጠጠር ወይም በሌላም ሕመም ከተጎዳ በኋላ እና ሕክምና ላይ የደረሱት እንዚህን እንዳይወስዱ ይመክራሉ፡፡

ጥቁር ኮለ መጠጦች

ለስላሳ መጠጦች

አቮካዶ

ሙዝ

የብርቱካን ጭማቂ

አፕሪኮት (የፍራፍሬ ዓይነት)

ቡናማ ሩዝ

የወተት ተዋጽኦ

የተቀነባበረ ስጋ

የታሸጉ ምግቦች (ጨው ሊበዛባቸው ስለሚችል)

ከስንዴ እህል የተሰሩ ምግቦች

ሠንጠረዥ አራት

መቸም ቢሆን ተስፋ መቁረጥ አይገባም፡፡ ሕክምናውን እየተከታተሉ የሚከለከሉትን (ሠንጠረዥ አንድ እና አራት) ምግብና መጠጥ መተው!! ነገር ግን የሚመቹትን ምግቦች እና መጠጦች  (ሠንጠረዥ ሁለት እና ሶስት)  መውሰድ ነው፡፡ “ኩላሊትህ ደከመ፣ ብቃቷቿ ከምንትስ ከመቶ በታች ነው”  የተባልክ ቀን እንኳን የራስህን እንክብካቤ ጀምር እንጂ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ፡፡

ማጠቃለያ

ይህ ምክር ለሕመሙ ታካሚ ብቻ ሳይሆን፣ ለአስታማሚዎች፣ ለቤተሰቦች፣ ወይም ለጠያቂዎች ጠቃሚ ነው፡፡ አንዳንድ ጠያቂ ምግብ አዘጋጅቶ ይሄዳል፡፡ ሙዝ እና አቮካዶ ይገዛል፡፡ በጠርሙስ

የታሸጉ ሶዳ መጠጥ፣ ወይም ስኳር የበዛባቸውን ይወስዳል፡፡

የራሳችሁን፣ የልጆቻችሁን፣ የቤተሰባችሁን፣ የሁሉንም የኩላሊት ጤንነት ጠብቁ፣ንፁህ ውሃ አብዝታችሁ ጠጡ፡፡

ማጣቀሻ
Image one     source  courtesy to   Rachna Pande What do you know about kidney stones, The New Times Rwanda 2007 – 2019 https://www.newtimes.co.rw/lifestyle

Images two    source  courtesy  to    Newsletter  ,   Medical News   How do you get kidney stones?

https:// www.medicalnewstoday.com/articles/154193.php

ማጣቀሻ አንድ .David Werner with Carol Thuman and Jane Maxwell. (2002). WHERE

THERE IS NO DOCTOR, A village health care handbook New Revised Edition, United States of America,

ማጣቀሻ ሁለት Tilahun Alelign and  Beyene Petros    Kidney Stone Disease: An Update on

Current Concepts https://www.researchgate.net/publication/322935596_Kidney_Stone_Disease_

ማጣቀሻ ሶስት https://www.kidney.org/atoz/content/kidneystones_prevent
ማጣቀሻ አራት Home Remedies for Kidney Stones: What Works? https://www.healthline.com/health/kidney-health/home-remedies-for-kidney-stones

ማጣቀሻ አምስት    በቀለች ቶላ፣ 2ዐዐ9 ዓ.ም ሕክምና በቤታችን፣ የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና

በተፈጥሮ  መድኃኒት፣ 5ኛ እትም፣ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ፣

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com