ዜና

ሀገረሰባዊ እምነት በሰባት-ቤት ጉራጌ -፫-

Views: 878

ንፑአር / ንፖር

ቅድመ ዝግጅት

ከሳምንት በፊት

የንፑአር ክብረ በዓል ቅድመ ዝግጅት የሚጀመረው ከበዓሉ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ነው[1]፡፡ የንፑአር ወቅት መድረሱ የሚታወቀው የማጋዎች ንጉስ  በሰባት ቤት ጉራጌ በሚገኙ ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች ከጥጥ የተሰራ ነጭ ኮፍያ በማድረግ በሌሎች ማጋዎች በመታጀብ በገበያ ውስጥ በመዘዋወር “ጎተነ ተጎቸ” ሲሉ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን  ኮፍያውን  አድርገው  በገበያ ውስጥ የሚዘዋወሩት ለምን እንደሆነ ስለሚታወቅ “ጎተነ ተጎቸ” የሚለው የቃል መግለጫቸው ብቻ ቀርቷል፡፡

ነጩ ኮፍያ  ንፑአር ደርሷል ማለት በመሆኑ በገበያ ውስጥ በመዘዋወር ብቻ የንፑአር ወቅት መድረሱን ለሰዉ ያሳውቃሉ፡፡ ከእወጃው ቀጥሎ ባሉት ቀናት ማኅበረሰቡ ማድረግ ያለበትና የሌለበትን ነገር ስለሚያውቅ ራሱን ከተከለከሉ ነገሮች ይጠብቃል፡፡

One week before Nepwar arrives, the maga perambulate through out the market in their clan district, making pronouncement on behalf of Boza. These initial   prohibition against the cutting of wood, slaughtering animals, quarrelling or mediating in dispute as well as the loaming of animals, money or goods, the reclaiming which might lead to feuding. (Shack, 1976, 170)

ከላይ ከተገለፀው ሃሳብ የተለየ የሚመስለኝ በአሁኑ ወቅትም ሆነ ቀደም ባሉት ጊዜያት ንፑአር መድረሱን የሚገልፁት በየአካባቢው የሚገኙ ማጋዎች ሳይሆኑ፣ የማጋዎቹ ንጉስ ብቻ ናቸው፡፡ ነገር ግን በአካባቢው የሚገኙ ማጋዎች በጠቅላላ ንጉሱን ስለሚያጅቧቸው እወጃውን ያከናውናሉ ማለት አይደለም፡፡

ከእወጃው በኋላ፣ ክልክል የሆኑ ተግባራት አሉ፡፡ እነዚህም፡- ማንኛውም ሰው ዛፍ እንዲቆርጥ አይፈቀድለትም ፤ እንስሳትን ማረድ የተከለከለ ነው፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት  አበድሮ የነበረውን ብድር ካለ በንፑአር ሳምንት መጠየቅ አይችልም፡፡ መጨቃጨቅ፣ ሴቶችን  መማታት፣ ጉድጓድ መቆፈር፣ የቤት ክዳንን ሳር ማልበስ የተከለከለ ነው፡፡ ይህንን ድርጊት በንፑአር ሳምንት የሚፈፅም ሰው ቦዠ በሱና በንብረቱ ላይ መብረቅ በመጣል ይቀጣዋል ተብሎ ስለሚታመን፣ ከነዚህ ድርጊቶች ራሱን በተቻለ መጠን ይጠብቃል፡፡

በተጨማሪም፣ በቤት ውስጥ ሴቶች ሰኸር የተባለውን ባሕላዊ መጠጥ ያዘጋጃሉ፡፡ ወንዶች ደግሞ በንፑአር ቀን ለሚከፋፈሉት የቅርጫ በሬ መግዣ  የሚያገለግላቸውን  የገንዘብ ማሰባሰብ ያካሄዳሉ፡፡

ከበዓሉ አራት ቀናት በፊት፡-

ለበዓሉ አራት ቀናት ሲቀር በሰባት ቤት ጉራጌ የሚገኙ ማጋዎች በጠቅላላ ወደ እናንጋራ ይጓዛሉ፡፡ በጉዞውም እያንዳንዱ ማጋ ለጎይታኩየው የሚሰጠውን ገንዘብና ወይፈን ይይዛል፡፡ እንዲሁም እናንጋራ በሚደርስበት ዕለት  የሚያርድውን ከብት የሚይዝ ሲሆን፣ የማጋው ሚስት በበኩሏ የተነጠረ ቅቤና ለክትፎ ማዘጋጃ የሚሆን ቅመማ ቅመም በማዘጋጀት ወደ አካባቢው ይጓዛሉ፡፡

በአካባቢው እንደደረሱ ጐይታኩየው ወደ ሚገኝበት እልፍኝ ከመግባታቸው በፊት፣ ወደ ዋቅ ዘገር በመሄድ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ፤ ይሳለማሉ፡፡ በመቀጠልም፣ ለጐይታኩየ ያመጧቸውን የእንስሳት ስጦታዎች ያስረክባሉ፡፡ ከዚያም፣ ወደ ግምግምየ  በመሄድ ለማደሪያ የሚሆናቸውን ቦታ በማዘጋጀትና እንጨት በመሰበሰብ የምሽቱ መምጣት ይጠባበቃሉ፡፡ ጊዜው መጨላለም ሲጀምርም እሳት በማያያዝ እና ለእርድ ያመጧቸውን ከብቶች በማረድ ክትፎ ያዘጋጃሉ፡፡

ማንኛውም ከነቤተሰቡ እስከ በዓሉ ፍፃሜ ድረስ በወንዙ አካባቢ የሚያድሩ ሲሆን፣ ማጋው በቤት ውስጥ ካደረ ቦዠበንፑአር እለት ልመናቸውን ሰምቶ አይወጣም ተብሎ ይታመናል፡፡

on the eve of Nepwar, gewtakweya ‘s tribe takes several oxen, as ascends to yenangre, slaughters the oxen and stay therefore four days ( LESLAU, 1964, 55)

ማጋዎቹ ግምግምየ በሚያድሩባቸው ቀናት የእድግ ጎሣ አባላት የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አብረዋቸው በወንዙ አካባቢ ያድራሉ፡፡  ሌሊቱን  በእድሜ የገፉት ማጋዎች ስለቦዠ ታላቅነት ስላደረጋቸው ነገሮች በድራ[2] የተባለውን ጨዋታ ካሉበት ቦታ ሆነው በቅብብልና በክራር አጋዥነት በመጫወት ያሳልፋሉ፡፡ ህፃናት የሆኑት በበኩላቸው ካሉባቸው ቦታዎች ሆነው በተመሳሳይ በቅብብሎሽ አቢዮ[3] የተባለውን ጨዋታ  በመጫወት ሌሊቱን ያሳልፋሉ፡፡

ከንፑአር እለት ቀደም ብለው ባሉት አራት ቀናት በርቀት የሚገኙ ሰዎች የተለያዩ ስጦታዎችንና ስዕለቶችን በመያዝ ወደ እናንጋራ ይጓዛሉ፡፡ የሚያመጧቸው ነገሮች በአብዛኛው ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆኑ ጥላ፣ ማር፣ ብቅል፣ የእንሰት ችግኝ፣ ገንዘብና ወይፈን የተለመዱ ስጦታዎች ናቸው፡፡

አንድ አካባቢ ተሰባስበው የሚመጡ ወይንም በመንገድ ላይ ተገናኝተው በጋራ ወደ እናንጋራ የሚጓዙ ተጓዦች በመንገዳቸው ላይ በሚያልፉባቸው መንደሮች የቦዠ ኤቸሁ![4] በማለት የቦዠን ታላቅነት፣ መሃሪነት የሚገልፁና ልመናና ሙገሳ ያካተቱ ዘፈኖችን ይዘፍናሉ፡

ወደ እናንጋራ ሲደርሱ ከጀፎረ ጀምረው በእልልታ ቦዠን ያመሰግሉ፡፡ ወደ ጎይታኩየ እልፍኝ ከመግባታቸውና ያመጧቸውን ስጦታዎች ከመስጠታቸው በፊት ወደ ዋቅ ዘገር በመሄድ ምስጋናቸውን በዜማ ያቀርባሉ፡፡ ይሰግዳሉ፡፡ በመቀጠልም ወደጎይታኩየ በመሄድና በተመሳሳይ በመስገድና ለቦዠ ምስጋና በማቅረብ ያመጧቸውን ስጦታዎች ከየት እንደመጡ በመግለፅ ይሰጣሉ፡፡ ስዕለት የሚያቀርቡ ሰዎች ስዕለታቸውን በመንገርና ለጥቂት ጊዜያት በመጨፈር ወደየመጡበት ይመለሳሉ፡፡

ከንፑአር አንድ ቀን በፊት፡-

ከንፑአር አንድ  ቀን ቀድሞ የሚገኘው እለት “የቆሎ ንፑአር” በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ እለት ሴቶች ቆሎ በመቁላትና ከቤት ውጪ ቡና በማፍላት ያከብሩታል፡፡ ይኸ ሥርዓት በአሁኑ ጊዜ እየቀረ የመጣ ሲሆን፣ አልፎ አልፎ በጥቂት ሰዎች ብቻ ይከበራል፡፡ እለቱን ግን በአብዛኛው የቆሎ ንፑአር በማለት ይጠሩታል፡፡

የንፑአር ቀን፡-

የንፑአር በዓል ዓመት መጥ ክብረበዓል ሲሆን፣ በጥር ወር ይከበራል፡፡[5] የንፑአር በዓል አከባበር  የሚጀመረው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ጎይታከየ በጠዋት በመነሳት ወደ ዋቅ ዘገር ይገባሉ፡፡ ወደ ዋቅ ዘገር ከመግባታቸው በፊት፣ እሳቸውም ሆነ ዋናው ማጋቸው ምግብ የማይቀምሱ ሲሆን፣ ቦዠ እስኪወጣ ድረስ ምንም አይነት ምግብ አይቀምሱም፡፡ ወደ ዋቅ ዘገር ሲገቡ በራሳቸው ላይ አረር የተባለውን ጨርቅ የሚያስሩ ሲሆን፣ በአካባቢው በዓሉን ለማክበር የሚመጡ ማጋዎችም በተመሳሳይ አረሩን በአናታቸው ላይ ያስራሉ፤ አሊያም ይለብሱታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የእድግ ጎሣ አባላት የሆኑ ወጣቶችም ልክ እን ደማጋዎቹ  አረር የሚለብሱ ሲሆን፣ ይህ ግን ትክክል ያለመሆኑን አዛውንቶች ይገልፃሉ፡፡

ወደ ዋቅ ዘገር ከገቡ በኋላ፣ የእርድ ሥነስርዓት ይከናወናል፡፡ እርዱን የሚያከናውነው ዋናው ማጋ ሲሆን፣ ከእርዱ የሚወጡ የተለያዩ ሞራዎች ወደ እሳት ይጨመራሉ፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በስዕለት  የመጡላቸውን ወይፈኖች በጠቅላላ የሚያርዱና ላመጣው ሰው ምርቃትና ልመናን ያቀርቡ ነበር፡፡

ከታረደው ስጋም ላመጣው ሰው እንደ ፍላጎቱ ከድርሻው እንዲወስድ ይደረጋል፡፡ በአብዛኛው አምጪዎቹ ድርሻቸውን እዚያው ትተው ተመርቀው ብቻ ይሄዳሉ፡፡ ከስጋው ግማሽ በአካባቢው ለሚገኙ አራሶች/የወለዱ ሴቶች ተካፍሎ የመስጠት ሁኔታ ቢኖርም፣ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የሚገኙት ጠቅላላ የእስልምና አሊያም የክርስትና እምነት ተከታዮች በመሆናቸው ምክንያት፣ ይህ ሥርዓት ቀርቷል፡፡

ከዚያም፣ በእለቱ ከተለያዩ አካባቢዎች ተጉዘው የሚመጡ ሰዎች ስዕለታቸውን ለጐይታኩየ በመናገር፤ አሊያም፣ ምን ተስለው/ጠይቀው እንደሞላላቸው በመናገር፣ ያመጡትን ያስረክባሉ፡፡ ጎይታኩየው በበኩላቸው ምርቃት በመስጠትና ስዕለታቸው እንዲሞላላቸው በመመኘት፣ የሚመጡትን ስጦታዎች ይቀበላሉ፡፡

በተጨማሪም፣ በስዕለት መልክ ያመጧቸውን ሳንቲሞች ወደ ዋቅ ዘገሩ ጣሪያ ላይ በመበተን ቦዠ ከዓመት ዓመት እንዲያደርሳቸው ይማፀናሉ፡፡ ለዚያ እለት ስላደረሳቸው ምስጋናቸውንም ያቀርባሉ፡፡ የሚበትኗቸው ሳንቲሞች በአብዛኛው በዓመት ውስጥ ያጠራቀሟቸው ሲሆኑ፣ ለዚያን ዕለት ቦዠ ስላደረሳቸው የሚያቀርቡት የምስጋና ስጦታ ነው፡፡

ማጋ እና የእንቴዘራ ጎሣ አባል የሆኑ ወንዶች በበኩላቸው ከግምግምየም ሆነ ካሉበት አካባቢ በዕለቱ ወደ ዋቅ ዘገር ሲመጡ፣ የተላጠ የፅድ እንጨት ይዘው ነው፡፡ ይህም ለቦዠ በዋቆቻቸው አማካይነት የተገባ ቃል መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የፅድ እንጨቱ በአሁኑ ጊዜ በሌሎች እንጨቶች የተተካ ሲሆን፣ ጎይታኩየ ዓመቱን ሙሉ ለሚያቀርቧቸው መስዋዕቶች ማቃጠያነት ይገለገሉባቸዋል፡፡

በእለቱ ከተለያየ ቦታ የሚመጡ ሰዎች በሕብረትና በአንድነት ስለ ቦዠ ኃያልነት ሙገሣና ልመና የተቀላቀለባቸው ዜማዎችን በማዜም ወደ አካባቢው የሚመጡ ሲሆን፣ በእጃቸው የሾላ ዝንጣፊ ይይዛሉ፡፡ የሾላ ዝንጣፊ የሚይዙበት ምክንያትም ቦዠ በየአካባቢው ባሉ አዋቅ ቤቶች ሲያርፍ የተቀመጠው የሾላ ዛፍ ላይ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡

ዋቅ ዘገሩ ያለበት ጀፎረ ጋር ሲደርሱ፣ ጀፎረው መሐከል ወደ ሚገኘው የዝግባ ዛፍ ሦስት ጊዜ ደርሰው ይመለሳሉ፡፡ ከላይ ወደ ታች ሦስት ጊዜ ሲመላለሱም በሶምሶማ ሩጫ ሲሆን፣ የቦዠ ኤቸሁ! በማለት ዜማዎችን ያዜማሉ፡፡ በመጨረሻም አዋቅ ዘገሩ ዙሪያ ቆመው በማዜምና ሦስት ጊዜ ኤቸሁ! በማለት እና መሬቱን በመሳለም ያመጧቸውን ስጦታዎች ለጐይታኩየው ያስረክባሉ፡፡ በሌላ በኩል በጋራ በፈረስ ራቅ ካሉ አካባቢዎች የሚመጡ ተጓዦች ከቁባ መስጊድ፣ ከጀፎረው የወዲያኛ ጫፍ (መጀመሪያ) እስከ አዋቅ ዘገሩ ድረስ ሽምጥ በመጋለብ የፈረስ እሽቅድድም ያካሄዳሉ፡፡ ይህም ከዓመት ዓመት እንደ ስዕለት የሚፈፅሙት ክዋኔ መሆኑን ይገልፃል፡፡

ከፈረስ እሽቅድድሙ በኋላ፣ በዋቅ ዘገሩ አካባቢ በእለቱ ወደ ሚመሰረቱት ገበያዎች በመሄድ በቡድን በመሆን ዋቅ እስኪወጣ ድረስ በአካባቢው ይቀመጣሉ፡፡ የእድግ ጎሳ አባላት የሆኑና ማጋዎች በበኩላቸው በአካባቢው በሚገኘው የግምግምየ ወንዝና በጀፎረው አካባቢ በመሰብሰብ፣ የተለያዩ ዜማዎችን በማዜም የቦዠን የመውጫ ሰዓት ይጠባበቃሉ፡፡

ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ሲሆን፣ ማጋዎች በጠቅላላ ከያሉበት በመሰባሰብ ወደ ግምግምየ ይሄዳሉ፡፡ በወንዙ ዙሪያ በመቆም ቦዥ በእለቱ እንዲወጣ ልመናን ያቀርባሉ፡፡ በዚያ የሚያካሂዱትን የልመና ሥርዓት በቦታው የተገኙ ታላላቅ ማጋዎችና የእድግ ጎሣ አዛውንቶች የሚመሩት ሲሆን፣ ቦዠን” ና! ውጣ! ካለሁበት በፍጥነት ስምተኸን ውረድ!” የሚል ተማፅኖን የያዘ ነው፡፡

የልመና ሥነ ስርዓቱ ሲጠናቀቅም፤ ከግምግምየ ጀመረው የዋቅ ዘገሩ እስከሚገኝበት ጀፎር ድረስ እየጨፈሩና ለቦዠ ምስጋና እያቀረቡ ይመጣሉ፡፡ የዋቅ ዘገሩ ከሚገኝበት ፊት ለፊት  የሚገኝ የዝግባ ዛፍ ጋር ሲደርሱም የማጋዎች ንጉሥ በሚመራው ልመና ቦዠ እንዲወጣ ለሁለተኛ ጊዜ ልመና ይካሄዳል፡፡

ልመናው ከተጠናቀቀ በኋላም፤ ከጀፎረው ጫፍ እስከ ዝግባው በሦሥተኛ ዙር ከሮጡ በኋላ፣ ወደ ዋቅ ዘገሩ በሩጫ በመግባት በዋቅ ዘገሩ ውስጥ ይሰበሳበሉ፡፡ በዋቅ ዘገሩ ውስጥ የሚሰበሰቡት የእድግ ጎሣ አባላት እና ማጋዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከነሱ ውጪ ሌላ ሰው ቢገባ ቦዠ እሺ ብሎ አይወጣም ተብሎ ስለሚታመን  የሚገባ የለም፡፡

በዋቅ ዘገሩ ከተሰበሰቡ በኋላ፣ በሦስት አቅጣጫ በመሆን “የኧ የኧ”(ና!ና!) በማለት ቦዠ እንዲወጣና  በጎይታኩየው ላይ እንዲያርፍ ልመናቸውን ያቀርባሉ፡፡ ከዘገሩ ውጪ የተሰበሰበው ህዝብም በተመሳሳይ በጭብጨባና በእልልታ ቦዠ እንዲወጣ ይለምናል፡፡

ቦዠ መውረዱ የሚታወቀውም በማጋዎቹ ንጉሥና በዋናው ማጋ ጎይታኩየው ከዋቅ ዘገሩ እስከ መግቢያው ሦስት ጊዜ ከላይ ወደታች በአረር እንደተሸፈኑ ሲመላለሱ ነው፡፡  የተሰበሰው ህዝብ በሕብረት በመሆን በቦዠ በመውረዱ የተሰማውን ደስታ በእልልታና በጭብጨባ ይገልፃል፡፡

ጎይታኩየው፣ በአረር እንደተሸፈኑ ወደ ዋቅ ዘገራቸው ሲገቡ፣ ማጋዎች በበኩላቸው ከየአካባቢያቸው ከመጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች ጋር በመሆን ለቦዠ ምስጋናን፣ ለሚቀጥለው ዓመት እንዲያደርሳቸው ልመናን በማቅረብ ወደ የቀያቸው በሠላም እንዲገቡ ምርቃትን አቅርበው የበዓሉ ፍፃሜ ይሆናል፡፡

የበዓሉ አክባሪዎች ወደ የመንደራቸው ከተመለሱ በኋላ፣ በቤት ውስጥ የሚፈፅሟቸው ሥነ ሥርዓቶች አሉ፡፡ አባወራው ከጐረቤቶቹ ጋር በሕብረት የገዛውን ከብት በማረድ ሲከፋፈል እማወራዋ በበኩሏ የታረደው የከብት ሥጋ እስኪመጣና ለበዓሉ የሚሆነውን ክትፎ እስክታዘጋጅ ድረስ ቆጮ በመጋገርና ቅቤ በማዘጋጀት ትጠባበቃለች፡፡

ለክትፎ የሚሆነው ስጋ ከመጣ በኋላ፣ ክትፎውን አዘጋጅታ በጣባ በማድረግና ቀደም ብላ የጠመቀችውን ሰኸር በእቃ በማድረግ ቤት ውስጥ በሚገኙ ልጆች አማካይነት ወደ ጓሮ ለባሏ በመላክ በቤት ውስጥ ተቀምጣ ትጠባበቃለች፡፡ አባወራው ወደ ጓሮው የተላከለትን ክትፎ ግማሽ ከልጆቹ ጋር በመሆን ከተመገበ በኋላ፣ ቀሪውን ለባለቤቱ በማስተረፍ በእንሰቱ መሐል ከተላከለት ቆጮ እና ክትፎ ግማሹን በእንሰት ውስጥ ይረጫል፡፡

ከዚያም ቦዠን በመለመን ቤተሰቡን እንዲጠብቅለት፣ ከዓመት አመት እንዲያደርሰው እንዲሁም የተለያዩ ልመናዎችን ያቀርባል፡፡ ይህንን ሥርዓት አከናውኖ እስኪያጠናቅቅ ድረስ እማወራዋ ወደ ደጅ የማትወጣ ሲሆን፣ የተላከላትንም ምግብ የምትመግበው ቤቷ ውስጥ በመሆን ነው፡፡ ይህ በእንሰት ውስጥ የሚፈፀመው ሥርዓት በአብዛኛው የሰባት ቤት ጉራጌ ክፍል እየቀረ የመጣና እለቱን በማሰብ ብቻ በቤት ውስጥ ክትፎ አዘጋጅቶ ወደ መመገብ እየተቀየረ መጥቷል፡፡

ተምሳሌት አንድ ነገር ለአንድ ነገር ውክልና ሲውል ነው፡፡ በሁለት ነገሮች መካከል ያለው ዝምድና የመወራረስ፣ የመተካካት ሊሆን ይችላል፡፡ ውክልናው በአብዛኛው በማኅበረሰቡ መካከል ባለ ስምምነት የሚወሰን ነው፡፡

የምስል ውክልና፡-

በተለያየ የዓለም ክፍል የመብረቅ አምላክ እንደ ማኅበረሰቡ ባህላዊና ማህበራዊ እሴት እንዲሁም የአኗኗር ሥርዓት የሚወከልባቸው ምስሎችም ይለያያሉ፡፡ እነዚህ ምስሎች  በአማልክቱ የማምለኪያ ሥፍራዎች በብዛት በቅርፅና በስዕል ይቀመጣሉ፡፡ በተጨማሪ በዚያ ማኅበረሰብ በምስል በማምለኪያ ሥፍራዎቹ የተቀመጡት እንስሳት የተከበሩ ናቸው፡፡ የአማልክቱ መንፈስ እንደሚያድርባቸው ስለሚታንም ከጥቃት የተጠበቁ፣ እንክብካቤ የሚደረግላቸውና የተፈሩ ናቸው፡፡

Outside Israel however, it was usual to represent the thunder by various visual images, such as a bird a dragon, sharp arrows, or a pronged spear (Davidson, 1965, 2) (Eells, 1989, 329)

በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ደግሞ የመብረቅ አምላክ በንስር ይመስላል፡፡ (montelius, 1910, 62) ለምሳሌ፡-በግሪክ ‹ሚት› የመብረቅ አምላክ እንደሆነ የሚታመነው ዚየስ ከሚመስልባቸው ነገሮች መካከል ንስር አንዱ ነው፡፡

በተመሣሣይ በሰባት ቤት ጉራጌ ቦዠ ምን ይመስላል? ለሚለው ጥያቄ የሚገኘው መልስ ቀይ ዶሮ እንደሆነ በትረካዎቻቸው ይገልፃሉ፡፡ ቦዠን አይተነዋል፤ እሱን ባየነው ቅፅበትም ቤት ተቃጥሏል፤ አሊያም፣ እንሰት በመብረቅ ተመትቶ ወድቋል፤ ብለው የሚተርኩ ሰዎች፣ በቅድሚያ የተመለከቱት ቀይ ዶሮ እንደሆነ ይተርካሉ፡፡ ያጠፉ ሰዎች ለመቅጣት ሲመጣም በመጀመሪያ የሚቀመጠው በቤት ምሰሶ ላይ እንደሆነ ይተረካል፡፡

 

[1]  ሳምንት ከሰባት ቀን ሲቀረው እንደሚጀመር የገለፁ አዛውንቶች ይገኛሉ፡፡

[2] ግጥማዊ የሆነ  በቃል በረጅሙ  የሚቀርብ እና ስለአማልክቶቻቸው አመጣጥ፣ ታላቅነት፣ ኃያልነት፣ አዳኝነት ወዘተ… የሚገልፅ የትረካ ዓይነት ነው፡፡

[3]  እንቆቅልሽ የሚመስልና በአብዛኛው መሰዳደብ የሚበዛበት ጨዋታ፤

[4]  ክብር ለቦዠ ይገባል የሚል ተቀራራቢ  የአማርኛ ትርጉም አለው፡፡

[5] በጉራጌ ማዝያ/ሚያዝያ 27 ቀን ይውላል/የጉራጌ ብሄረሰብ የራሱ የሆነ የቀን አቆጣጠር ሥርዓት አለው፤

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com