ዜና

ሻይ ለጤና (ክፍል አንድ)

Views: 1387

በግራ የመቅመቆ ሻይ  በቀኝ የከርከዴ ሻይ

መግቢያ ስለ ሻይ

ሻይ የቱ ነው? ስንት ዓይነት ሻይ አለ? በእኛ አገር ብዙ ያልተወራለት መጠጥ ቢኖር ሻይ ነው፡፡ እስቲ የሻይን ጠቀሜታ እና ዓይነታቸውን እያነሳን እንማማር፡፡

ሻይ በተራ ትርጉም  በትኩስ ወይም በቀዝቃዛ የሚጠጣ ነው፡፡ ዋናው መገኛውም የሻይ ዛፍ ካሚሊያ ሴኔንሲስ  (Camellia sinensiis) ከሚባለው ዛፍ የሚገኘው ቅጠል በፋብሪካ ተቀናብሮ ታሽጎ የቀረበው እና በየሱቁ የሚሸጠው ነዋ፡፡ ቢባል ስህተት አይመስልም፡፡

ሻይ በስፋት ሲተነተን ጉዳዩ የትየለሌ ነው፡፡ ነገር ግን በአጭሩ እንዲህ እንመልከት፡፡ ሻይ የሚገኘው ከሻይ ዛፍ (ከካሚሊያ ሴኒንሲስ) ብቻ ሳይሆን ከብዙ የተክል ውጤቶች ነው፡፡ በጠቅላላው መደበኛ ሻይ እና የዕፀዋት ሻይ (Herbal tea)  ይባላሉ፡፡  በእኛ አገር ብዙ አልተሠራበትም፡፡  የአውሮፓ አገራት ከሌሎቹ ብዙ ጥሬ እቃ ገዝተው አቀናብረው መልሰው ለዓለም ገበያ ያቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ ሮቦስ የተባለ ምርጥ የዓለም ሻይ በጀርመን ይመረታል፡፡ ጥሬ ዕቃው እንደ ጭራሮ እንጨት ተሰብስቦ የተወሰደው ግን ከደቡብ አፍሪካ ነው፡፡

 ሻይዎች የአልኮል ይዘት የላቸውም፣ ነገር ግን ለጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ ማጣቀሻ አንድ

 • ለማነቃቃት ይጠቅማሉ፣
 • የበሽታ መከላከል አቅም ለማጎልበት፣
 • ለደም ዝውውር መስተካከል እና የደም ግፊት ለመቀነስ ይረዳሉ፣
 • ለልብ ፣ ለኩላሊት፣ ለጉበት፣ለጨጓራ፣ ለአንጀት ጤንነት ይጠቅማሉ፣
 • የስኳር በሽታ ለመቀነስ ይረዳሉ፡፡
 • የሰውነትን ጤና ለመጠበቅ እጅግ ይረዳሉ
 • ክብደት ለመቀነስ፣
 • አለርጂ ለመቀነስ
 • የምግብ ስልቀጣ ስርዓትን ለማገዘ
 • ለጥሩ እንቅልፍ
 • ለአአዕምሮ ጤና
 • ለምግብ ፍላጎት እና ለማህበራዊ ትሥሥር ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡

ሻይ ወደር የሌለው የዓለም መጠጥ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉም የሻይ ዓይነት ለሁሉም ሰው ይስማማል ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም ሻይ ከላይ የተነገሩትን የጤና በረከት ይኖሩታል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ መአዛማ ሻይ የሆኑት የተባለውን በበቂ መጠን ሲኖራቸው፤ ሌሎቹ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ አንዳንዱ ዓይነት ሻይ ከምግብ ጋር፣ ሌላው ከምግብ አርቆ መውሰድ ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ብዙ ጊዜ እንዲያነቃቃ ጠዋት ይጠጣል፣ ነገር ግን እንቅልፍ እንዲያስወስድ  በመኝታ ሰዓት የሚጠጡም አሉ፡፡ በእርግዝና ላይ ያሉት እና የሚያጠቡ እናቶች እንዳይጠጡ የሚከለከሉም ሻይዎችም አሉ፡፡

1/  በእኛ አገር ሻይ የት ይመረታል?

ሀ) በፋብሪካ    በስፋት እና በብዛት የሚመረት ሆኖ፣ በአብዛኛው አሁን እየጠጣን ይገኛል፡፡

ለ) በአነስተኛ መጠን (በባልትና)     በጣም ጥቂት ድርጅቶች፣ በአነስተኛ መጠን የሚያቀርቡት ማዓዛማ ወይም ዕፀ ማዓዛ ሻይ ነው፡፡

ሐ) በየቤታችን አዘጋጅተን ወይም አልምተን    ይህ በየቤቱ ሰው ከአንዳንድ ተክሎች አዘጋጅቶ የሚጠቀመው ወይም ተክሎቹን አልምቶ የሚጠቀመው ነው፡፡

2/ መደበኛ ሻይ እና የዕፀዋት ሻይ በአጠቃላይ

ሀ/  ከምን ከምን ይመረታሉ? ዋናው ተክሎች ሲሆኑ፤ ለማስረዳት ያህል እንደዚህ ማጠቃለል ይቻላል፤

ሀ)ከዛፍ ቅጠላ ቅጠል       (tree leaves)

ለ) አትክልቶች              (vegetables)

ሐ) ከዕፀ መአዛ ተክሎች   (herbs and spices)

መ)ከአበቦች    (flowers)

ሠ) ከሥራሥር   (root crops)

ረ)ከፍራፍሬ   (fruits  )

ሰ)አረም ቅጠሎች  (weeds )

ሸ) ከጫካ ቅጠሎች  እና  (wild leaves)

ቀ) ከሌሎች

ለ/ ያላቸው ቃና (ጣዕም)፣ በመላው ዓለም በተለይም በቻይና፣ ህንድ እና ሲሪላንካ ከእራሱ ከሻይ ዛፍ (ካሚሊያ ሴኔንሲስ) ብቻ፣ ቀዩን ሻይ ሳይቀር በተለያየ ቃና ያመርታሉ፡፡ በእኛ አገር የተለመደው የቀዩ ሻይ ቃና በአመዛኙ ተመሳሳይ ሆኖ በስኳር እናጣፍጠዋለን፡፡  ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ ተክሎች እጅግ በብዙ ዓይነት ቃና ይመረታል፡፡

 ሐ/ጥፍጥናቸው  ስኳር ሳይጨመርበት በተፈጥሮው 

ሀ) ጣፋጭ  ለ) ጎምዛዛ  ሐ) ጣዕም የሌለው፣ መ) መራር ሊሆን ይችላል፡፡

 መ/ቀለማቸው፣  ደማቅ ቀይ፣ ቀይቡኒ፣ ቡና መልክ፣ ወይን ጠጅ፣ ደማቅ ቢጫ፣ ብርትኳናማ ቢጫ፣ ደማቅ አረንጓዴ፣ ሎሚ ከለር፣ ነጣ ያለ፣ ነጭ፣ ውሃ ቀለም፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡

ሠ/ የሻይ ደረጃዎች፣ በብዙ አገራት ሁሉም የየራሳቸው መስፈርት ይኖራቸዋል፡፡ በእኛ አገር የተሰጠው ደረጃ ይኖር እንደሆን ለጊዜው በመረጃ የተደገፈ ነገር የለም፡፡ የተወደደው እና ሰፊ ተቀባይነት ያለው ግን ቀዩ ሻይ ነው፡፡

 3/ ከላይ በፎቶ የተገለፁት

3.1 (በግራ የመቅመቆ ሻይ) የሚዘጋጀው መቅመቆ  Rumex abyssinicus   ከሚባል ዱር በቀል አረም ዓይነት እፀዋት ሥር ነው፡፡ በጎንደር እና በትግራይ ለቅመምነት በጣም ተፈላጊ ነው፡፡ መርካቶ ገበያ ላይ ምዕራብ ሆቴል አካባቢ ይሸጣል፡፡ ሥሩን ነቅለው አድርቀው ለገበያ ያቀርቡታል፡፡ ሥሩ ይታጠባል፣ ይወቀጣል፣ ዱቄቱ በትንሹ ከጦስኝ ጋር በፈላ ውሃ ላይ ተደርጎ በማር፣ በስኳር ወይም ብቻውን ይጠጣል፡፡  ለኩላሊት፣ ለደም ግፊት፣ ለደም ጥራት፣ ለሳል፣ ለጉንፋን በሻይ መልክ ይጠጣል፡፡

3.2 (በቀኝ የከርከዴ ሻይ)፣የሚዘጋጀው ከርከዴ  Hibiscus sabdariffa  ከሚባል አነስተኛ ቆጥቋጦ ዛፍ ላይ በሚገኝ አበባ ነው፡፡ አበባው ተለቅሞ በጥንቃቄ ይደርቃል፣ ይፈጫል፣ ለሻይ ይሆናል፡፡ በቤንሻጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ በገበያ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡

የከርከዴ ሻይ ብዙ የጤና ጥቅሞች አሉት፡፡  አንቲኦክሲደንት አለው፣ የደም ግፊት ይቀንሳል፣ የደም ቅባት ይቀንሳል፣ የጉበት ጤናን ይረዳል፣ክብደት ለመቀነስ ይውላል፣ ካንሰርን ለመዋጋት የሚረዱ ንጥረ ነገሮች አሉት እንዲሁም ባክቴሪያን ይዋጋል፡፡ማጣቀሻ ሁለት

4/ የሻይ ምርት በዓለም እና በእኛ፣

ዓለም ስንት ጥበብ ተራቆበታል፣ሻይ በዓለም ላይ ህልቆ መሳፈርት በሌለው ዓይነት ቀርቦ ይገኛል፡፡ በእኛ አገር በጣም የታወቀው ቀይ ሻይ ብቻ ነው፡፡ ከተመሳሳይ ተክል ተዘጋጅቶ በአመራረት እና በቀለም የሚለየው ለጤና ተመራጭ የሆነው፣ አረንጓዴው ሻይ እንኳን ብዙ እውቅና የለውም፡፡ ገበያ ላይም በቀላሉ ለማግኘት አይቻልም፡፡

አሁን ለመነሻ ያህል በአገራችን እና በተለያዩ አገራት ለሻይ ምርት ጥቅም ላይ ከሚገኙት ተክሎች ጥቂት ምሳሌ በተለያየ መጠሪያ እንመልከት፡፡ ይህ የተወሰደው ከዕፀዋት መጠሪያ መጽሐፍ ነው፡፡ ማጣቀሻ ሶስት

4/ በሚቀጥሉት ክፍሎች በዝርዝር የምናየው፡

የተመረጡ የሻይ ዓይነታትን በምን ዓይነት እንጠቀም? ምን የጤና ጠቀሜታ እናገኝባቸዋለን? ብለን በሰፊው እንማማራለን፡፡ በተለይም

1/ በአገራችን የሚገኙት የሻይ ፋብሪካዎችስ ምን ምን ዓይነት አቅርበውልናል?

2/ ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ገበያ ላይ ስለሚገኙት፣

3/ የበለጠ ቀጠሜታ ያላቸው እና ከውጪ ወደ አገር ውስጥ ቢያስመጡ የምንላቸውን፣

4/ በቤታችን ውስጥ ሊመረቱ ስለሚችሉ የሻይ ምርት ዓይነቶች ልማቱን ጭምር ትምህርት ቢሰጥበት

 በአገራችን በጣም ብዙ የሻይ አይነት ሁላችንም ማምረት እንችላለን በሚል እምነት፡፡

5/ በአገር ውስጥ የሌሉትን ዓይነታት ባለእርሻዎች አምጥተው እንዲያለሙ ምክር እና

የመሳሰሉትን እናቀርባለን፡፡      በማንበብ ተከታተሉን፡፡

 

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ አንድ  Drinking tea may improve your health             https://www.today.com/series/one-small-thing/top-10-health-benefits-
ማጣቀሻ ሁለት፣ Benefits of Hibiscus Tea https://www.healthline.com/nutrition/hibiscus-tea-benefits

ማጣቀሻ ሶስት፣  በቀለች ቶላ፣  2ዐዐ9 ዓ.ም  Glossary of Plant ‘s Name  in Scientific, Amharic and Others

የዕፀዋት መጠሪያ  በሳይንሳዊ   አማርኛ እና ሌሎችም፣ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com