ዜና

ከእረኝነት እስከ ፈጠራ ባለሟልነት

Views: 858

በደቡብ ክልል ሸካ ዞን ልዩ ቦታው ከላቻ የተባለ ሥፍራ የተወለደው መልካሙ ታደሰ የዘንድሮው ሶልቭ አይቲ የፈጠራ ሥራ ውድድር ባለ ሶስት አውታር ማተሚያ (3ዲ ፕሪንተር) በመፍጠር የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ከአርባ ደቂቃ በላይ በእግሩ ተጉዞ ፤ላሞችን አልቦ እና ከብቶቹን አሰማርቶ ወደ ትምህት ገበታው ይደርስ የነበረው መልካሙ ሁሌም ከክፍል በአንደኝነት ደረጃ እየወጣ ቤተሰቡንና አስተማሪዎቹን ያኮራ ነበር፡፡ በመጨረሻም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዓመት ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት በማዕረግ ተመርቋል፡፡

በአካባቢያቸው በቀላሉ ከሚገኙ ቁሳቁሶች ባለ ሶስት አውታር ፕሪንተር ከዩንቨርሲቲ ጓደኞቹ ጋር በመሆን የሰራው መልካሙ ቤተሰቦቹና ዩኒቨርሲቲ በሚማርበት ጊዜ አማካሪው የነበሩት አቶ ሔኖክ እገዛ እንዳደረጉላቸው ገልጿል።

ባለ ሶስት አውታር ፕሪንተር በገበያ ላይ ያለ ቢሆንም ዋጋው በጣም ውድ ስለሆነ እነደልብ አይገኝም የሚለው ወጣቱ ይህን የ3ዲ ፕሪንተር ለመፍጠር ያሰበው በተማረበት ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ቴክኖሎጂው ባለመኖሩ ተማሪዎች ፕሮጀክታቸውን ለመስራት ሲቸገሩ በማየቱ እንደሆነ ለቢቢሲ አስረድቷል፡፡

ማሽኑ በተለይም የህንፃ ዲዛይን በሶስቱም ማዕዘን ቁልጭ አድርጎ ለማሳየት እንደሚረዳም ተናግሯል፡፡

መልካሙ ይህን የፈጠራ ስራ ለማዳበር ከዩኒቨርሲቲ ጓደኞቹ መንበሩ ዘለቀ እና መልካሙ ፍቃዱ ጋር በመሆን አጎልብተውት፤ በመጨረሻም በሶልቭ አይቲ ፋውንዴሽን ሥልጠናዎችንና ልምዶችን ለመቅሰም እድል አግኝተው በውድድር ከነበሩ 63 ስራዎች መካከልም የእነሱ ፈጠራ የአንደኝነት ደረጃን አግኝቷል፡፡

አንደኛ ስለወጡም በአይኮ ግላብ ድርጅት የ100 ሺህ ብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ወደፊት ከሃገር ውስጥና ከውጭ አገር ያሉ ባለሃብቶች ጋር በመገናኘት የፈጠራ ሥራቸውን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰሩ መልካሙ ታደሰ ገልፆልናል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com