ዜና

ሀገረሰባዊ እምነት በሰባት-ቤት ጉራጌ -፪-

Views: 683

ዥምወድ

ስለዥምወድ ማንነት የተለያዩ አፈታሪኮች ይነገራሉ፡፡ ከየት እንደመጣች ወይም ቀደም ስላለው የቤተሰቦቿም ሆነ የሷ ታሪክ የሚተረከው ታሪክ  ሁለት አይነት  ነው፡፡ የመጀመሪያው ታሪክ የዥምወድ ቀደም ያለ ታሪክ አይታወቅም የሚለው ነው (ጎይታኩየ ሙሉ)፡፡ ሁለተኛው ታሪክ የቄስ ልጅ እንደሆነች የሚገልፀው ታሪክ ነው፡፡ በሁለቱም ተራኪዎች ዥምወድ ከባህር እንደወጣችና ከባህር ስትወጣም አረር (ቀይ ሸማ) ለብሳና አብሯት ሰው መውጣቱንና ያ ሰውም በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ማጋዎች አባት እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

ሁለተኛዎቹ ተራኪዎች በበኩላቸው የቄስ ልጅ  እንደነበረች ይገልፃሉ፡፡ ከመወለዷ በፊት ወደ ውሃ አካባቢ እንዳትደርስ በተነገረላት ትንቢት መሠረት፣ ቤተሰቦቿ ወደ ወንዝ እንዳትሄድ እየጠበቁ ያኖሯት ነበር፡፡ ከእለታት በአንዱ ቀን ቤት ውስጥ ሰው ያለመኖሩን ያየችው ዥምወድ ቤት ውስጥ ካለች አገልጋይ ጋር ወደ በር/ወንዝ ሄደች፡፡ ውሃው አካባቢ ስትደርስም ወንዙ ደፍቆ አሰመጣት፡፡

አብራት የነበረችው አገልጋይም የሆነውን ነገር ወደ ቤተሰቦቿ በመሄድ ስለሆነው ነገር ተናገረች፡፡ ቤተሰቦቿም ወደ አዋቂ ሄደው ምን ማድረግ እንዳለባቸው  ሲጠይቁ፣ ሰባት ቀን ወይፈን አርደው ወደ ውሃ እንዲጨምሩና ልጃቸውን ከዚያው ውስጥ  እንደሚያገኙ አዋቂው ነገራቸው፡፡

በተነገራቸው መሠረት ወይፈን አርደው ወደ ወንዙ መጨመር በጀመሩ፣ በአምስተኛው ቀን ቦዠ ዥምወድን ወደ ላይ አውጥቶ መልሶ አስገባት፡፡ በተከታዩ ቀንም ብቅ ጥልቅ እንድትል አደረጋት፡፡ በሰባተኛው ቀን አዋቂው እንዳለው ቦዠ ከውሃው አወጣት የሚለው ትረካ ነው፡፡ መልስ በፃፈው የመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ ፅሁፉ ወንዙ መገራር እንደሚባል ገልጿል (መልስ፣ 198ዐ፣7)

ከውሃው ፉጥረ እና ሙጥረ ከሚባሉ ሁለት ሰዎች ጋር እንደወጣች ይነገራል፡፡ ከዚያም ጌቨረ ወደ ተባለው የእዣ ዋቅ እንደሄዱ ይተረካል፡፡ እዚያ ሲደርሱም ጌቨረ ማነህ ቢሏቸው ሞህር ነኝ ደጅ ደጅ እሄዳለሁ ብለው ተናገሩ፡፡ በዚህም ከሞህር እንደመጣ በዚያ ታወቀ ይላሉ፡፡ ከዚያም ድርሻዬን ስጠኝ አለው፡፡ ጌቨረም በቤት ውስጥ  የሚወለደው ወይፈን ላንተ ይሁን አለው፡፡ ከዚያ ተነስቶ ትንንሽ ዋቆችን ትቶ ወደ ቸሃ አወቅ ወደ አወጌት ሄደ፡፡ አወጌት በአገሩ አልነበረም፡፡ (ወደ ሁሉም ዋቆች ቦዠ የሄደው ወተዋ በሚባለው የመኀር  ወቅት እንደነበር ይተረካል) ነገር ግን አሁን እኔ ጋር ብዙ የምስጥህ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን፣ ካለኝ የተላጠ ግንድ፣ ቅቤና እህል ሰጥቼሃለሁ አለው፡፡ አነሰኝ ሲልም በል በመጀመሪያ የተወለደን ወይፈን ውሰድ አለው፡፡ በየት በኩል ይግባ ሲለው በግምግምየ አለ በማለት የሚሰጠው፡፡

ባላሞ ወደተባለና እንሞር/እኖር ወደሚገኝ ዋቅ ቦዠ ሲሄድ የምትሄድበት ቦታ ከሌለህ በኔ ገራራ ኑር አለው፡፡ ከዚያ የሚፈልገውን እንደሌሎቹ ድርሻውን ተቀብሎ ሄደ፡፡ ወታወ ገራራ ቦዠ ገርፋር አወጣቸው፡፡ ወታወ ገራራ[1] አሣድሩን አሉ፣ ግቡ ተባሉና እዚያው አደሩ፡፡ ተኝተው ሳለ የሰውየው ሚስት በመደቡ ላይ ሆና ወደ እንግዶቹ ስታይ ዥምወድ የተኛችበት ቦታ በእሳት ተከቦ ስታይ ዳዎ ዳዎ[2] ሴትየዋ የተኛችበት ቦታ እሳት እየነደደ ነው አለቻቸው፡፡ ሰይጣንም ይሁን ሰው  ጠዋት ይለያልና ዝም ብለሽ ተኚ አሏት፡፡ ጠዋት መርቀው ወጡ፡፡ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ፈልገው ወደ ላይ ሲወጡ ተመልሰው የነበሩበት ቦታ ሲመሽ ሌላ አዋቂ ቤት የደረሱ መስሏቸው አሣድሩን አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የቤቱ ባለቤት ሂጂ ከዚህ ማታ እዚህ ቤት አይደል ያደርሽው እቤትሽ ሄደሽ ለባልሽ ጐመን አትቀቅይም፣ ቆጮ አትጋግሪም  ብለው ተቆጧቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቦዠ ወይ በለኝ የምኖርበት ቦታ ስጠኝ ብለው ዥምወድ አለቀሱ፡፡ በዚህም ጊዜ የገረፋርን አዋቅ በንፋስ እና በዝናብ ውሽንፍር የት እንዳደረሳቸው አይታወቅም፡፡ ከዚያም የወታወን ገራር ከገረፋር አዋቅ ወደ ዥምውድ ቀየረላቸው፡፡ በዚህም በወታዋ ገራር ገብተው መኖር ጀመሩ፡፡

በዥምወድ አማካይነት ቦዠ ሞህር አካባቢ መቆርቆር  ከሚባል ወንዝ ሲወጣ ለዠምወድ፣ ለሙትሬ እና ለፉጥሬ አስይዞ ያወጣቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ እነዚህም ጎንደር[3]፣ አረር፣ እርቅር[4]፣ አስታረ[5] እና ጐመን ናቸው የሚሉ ሰዎች ሲኖሩ ቅቤና ወይፈን የሚጨምሩ ተራኪዎች አሉ፡፡

በጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዓመታዊ መጽሔት “ቦዠ” በሚል ርዕስ በእልፍኝ መጽሔት ላይ በወጣው መጣጥፍ፣ ከሁለቱም ታሪኮች የተደባለቀ ታሪክ ተፅፎ ይገኛል፡፡

እንደ ፀሐፊ ቦዠ ከመነሻው መጣ ተብሎ የሚታመነው ሞህር ከተባለ ቦታ ነው፡፡ ሞህር ውስጥ ከዋቅ ጋር በተያያዘ የሚተመንበት ቆጥራ ተብሎ የሚጠራ በጣም ጥልቅ የሆነ ወንዝ ነበር፡፡ በዚህ ወንዝ የአካባቢውን ህዝብ ያስቸገረ መንፈስ ነበር፡፡ አንድ ቀን አቡነ ዜና ማርቆስ ለመሻገር ሲሞክሩ መንፈሱ አላሻግር ብሎ አስቸገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን በማውጣት ዳዊት በመድገም ላይ ሳሉ መንፈሱ ከወንዙ ወጥቶ ተቀመጠ፡፡

ይህ እየተከናወነ ባለበት ወቅት ዥምወድ የተባለች ልጃቸው ውሃ ለመቅዳት ወደ ወንዙ አካባቢ መጣች፡፡ ከዚያ መንፈሱ ዥምውድን ወደ ወንዙ ይዟት ገባ፡፡ በዚህ ወንዝ ለሦስት ዓመታት ካቆያት በኋላ፣ ከእሷ ጋር ሌሎች አራት ሰዎችን በመጨመር ልብስ አልብሷቸው በእያንዳንዳቸው እጅ ላይ ሦስት ሦስት አምባሮች በማድረግ፤ ቃጭል አሲዟቸው ወጡ፡፡ ይዘው የወጧቸው ነገሮች ነጭ አስታራ፣ እንሰት እና የወተት ከብት ናቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ዥምውድና አራቱ ሰዎች ከሞህር በመነሣት ወደ ተለያዩ የጉራጌ ክፍሎች ከተዟዟሩ በኋላ፣ በስተመጨረሻ እናንጋራ የተባለው ቦታ ሲደርሱ መቀመጫቸው እዚያው አደረጉ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚሁ ስፍራ ቦዠ መከበር ጀመረ ይላል፡፡ (እልፍኝ፣ 2ዐዐ2፣7)

ጎይታኩየ

ጎይታኩየ ወይም ጌታኩየ የሚለው ቃል ከሁለት የጉራጌኛ ቃላት ጥምረት ማለትም “ጌታ” እና “ኩየ” ከሚሉት የተገኘ ሲሆን፣ እነዚህ ሁለት ቃላት ወደ አማርኛ ሲመለሱ “አምላክ” እና “እንደ” ማለት ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም ጎይታኩየ ማለት “እንደ አምላክ ማለት” ነው፡፡ ስለዚህ ጎይታኩየ ማለት እንደ አምላክ የሚታይ ማለት ነው፡፡ በሰባት ቤት ጉራጌ ህዝብ ዘንድ የቦዠ አምላክ መንፈስ ያለበት  ሰው መጠሪያ ነው፡፡ ንግሥናውን የሚያመለክት አምባር (ጎንደር) በእጁ ላይ ያጠልቃል፡፡ ይህ አምባር የንግስናው ምልክት ሲሆን ከንግስናው ጋር ከልጅ ልጅ  በዘር የሚተላለፍ የስልጣን ምልክት ነው፡፡

እስከ አሁን ድረስ የነገሱት ጎይታኩየዎች 17 ናቸው፡፡ ለጎይታኩየነት የሚሾሙትም ከአባት ወደ በኩር ልጅ በሚተላለፍ የዘር ቆጠራ መሠረት ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጅነት ዋናውና የመጀመሪያው መስፈርት ቢሆንም፣ የሚነግሰው በበኩር ልጅነት ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች መስፈርቶችም ከብኩርናው እኩል ዋጋ አላቸው፡፡ እነዚህም በማኅበረሰቡ የተከበረ፣ አዋቂና አስታራቂ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ለንግሥና ከማያበቁ እና በኅብረተሰቡ ከሚጠሉ ድርጊቶች መካከል ለምሳሌ ሌባ ከሆነ ለንግሥና አይታጭም፡፡

ለንግሥና የሚታጨውን ሰው የመምረጥና የመወሰን ትልቅ ሥልጣን ያላቸው የማጋዎች ንጉሥ፣ ማጋዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ናቸው፡፡

ዥምወድና ሙጭረ ከየት እንደመጡ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎችን አግብተው መኖር ጀመሩ፡፡ በጉርብትና ሲኖሩ የየራሳቸው ወይፈን/ ከብት ያረቡ ነበር፡፡ ከእለታት አንድ ቀን የሙጭረና የዥምወድ ወይፈኖች ይጣላሉ፡፡ የዥምወድ ወይፈን የሙጭረን ወይፈን ወደ ገደል ከቶ ይገድለዋል፡፡

በዚህ የተናደደው ሙጭረ እንዴት የሴት ወይፈን ያሸንፋል በማለት የዥምወድን ወይፈን በጦር ወግቶ ይገድለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ዥምወድ ሙጭረን ለመበቀል አቅም ስላነሳት ትራገማለች፡፡ እርግማኑም፣  የአዙሪት በሽታ ይፈጠር፤ ከኔ በኋላ ሥልጣን በወንድ ልጅ እጅ ይግባ! በማለቷ የዥምወድን እርግማን የሰማው ቦዠ የንግስናውን ሥልጣን እድግ ለተባለው የዥምወድ የበኩር ልጅ እንደሰጠው ይነገራል፡፡

የቦዠ አምላክ ወታወ ገራራ ለብዙ ዓመታት ከቆየ በኋላ እናንጋራ ወደሚባል ግዛት ይመጣል፡፡ እንደመጣ በገራራው ይኖር የነበሩትን የቁስያ ጎሳዎች አለቃ የሚፈልግውን ሁሉ እንዲሰጠው ጠየቀ፡፡ ለቦዠ ጥያቄ የጎሳው መሪ ምላሽ እንቢታ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ የቦዠ አምላክ የጎሳውን አለቃና አባላቱን በጠቅላላ አጥፍቶ እናንጋራ ላይ በማረፍ የጉራጌ ህዝብ የንፑአር በዓሉን እዛ እንዲያከብርለትና ግብሩን ይዞለት እንዲመጣ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በእናንጋራ የንፑአር በዓል መከበር ጀመረ፡፡

ማጋ

ማጋ በጉራጌ ብሄረሰብ ከእንቴዘራ ጎሣ የሚገኙ ናቸው፡፡ የእንቴዘራ ጎሣ በሰባት ቤት ጉራጌ በየትኛውም አካባቢ ሄዶ የመኖር መብት ያላቸው ጎሳዎች ናቸው፡፡ማጋዎች በሰባት ቤት ማኅበረሰብ የቦዠ መንፈስ እንዳደረባቸው ስለሚታመን በማኅበረሰቡ የተከበሩ ናቸው፡፡

ማጋ ከዥምወድ ጋር ከወጡት የሙጭረ ተወላጆች ሲሆኑ የጎይታኩየውን ሥራ ጎይታኩየውን ወክለው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚፈፅሙ ተወካዮች ናቸው፡፡ ያላቸው ሥልጣን ከጎይታኩየው እኩል ሲሆን፣ እንደ ቦዠ  ሥራ አስፈፃሚዎች ወይንም ተላላኪዎች ይቆጠራሉ፡፡

በማኅበረሰቡ ማጋዎች አረርና ሸነ ከመትከል ጀምሮ የተለያዩ ግልጋሎቶችን ይሰጣሉ፡፡ ሸነ እና አረር የተተከለባቸውን ንብረቶች የሰረቀ ወይንም ያቃጠለ ሰው፣ ቦዠ በመብረቅ እንደሚቀጣው ይታመናል፡፡ በዚህ ምክንያትም  ቤቱ ወይም የተከለው እንሰት በመብረቅ የተቃጠለበት ሰው ጥፋቱን ካልተናገረና የበደለውን ካልካሰ ተጨማሪ ቅጣት ቦዠ ይጥልበታል ስለሚባል በርቸ[6] ላለማስቀመጥ የሚፈፅማቸው ሥርዓቶች አሉ፡፡

አንድ  ሰው ቤቱ በመብረቅ ቢመታ/ቢቃጠል ማጋው ካለበት ተጠርቶ እስኪመጣ ድረስ ምንም ዓይነት ንብረት ከቤቱ አያወጣም፡፡ እቃ አሊያም ከብቶች በቤት ውስጥ ቢኖሩ እንኳን፣ ለማትረፍ አይሞክርም፡፡ ነገር ግን፣ ማጋው መጥቶ በአፉ ማር በመያዝ ምሰሶው ላይ ወጥቶ ማሩን በሚቃጠለው ቤት ላይ በአፉ እስኪያፈስ ድረስ ይርር/እልል እያለ በመለመን ንብረቱ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንዳይስፋፋ ቦዠን በማሞገስ ይለምናል፡፡

በአጋጣሚ ማጋው በአካባቢው ካልተገኘ የሱ ወንድ ልጅ አሊያም ያላገባች ሴት ልጁ በተመሣሣይ በማጋው ቦታ በመሆን ማሩን እንዲያፈሱ ይደረጋል፡፡ እነዚህ ሁሉ በአካባቢው ከሌሉ የምታጠባ ሴት  ልጇን እንዳቀፈች ማሩን በቤቱ ማገር ላይ እንድታፈስ ይደረጋል፡፡ ቦዠም ማር ሲያገኝ ከቁጣው   ይታገሣል ተብሎ ይታመናል፡፡

ቤቱ የተቃጠለበት ሰው፣ ማጋው ከመጣና ንብረቱን ከቤቱ ካወጣ በኋላ ለሌሎች ሥርዓተ- ክዋኔዎች ቀጠሮ በመያዝ ይለያያሉ፡፡ ማጋው የሚያዘው ትዕዛዝ አለ፡፡ ይህም፣  ቤትህ እንዴትና በምን ምክንያት ሊቃጠል እንደቻለ አዋቂ ጠይቀህ ጠብቀኝ ብሎ፤ ለዚያም የአንድ ወር ቀነ ቀጠሮ በመስጠት ይሄዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ቤቱ የተቃጠለበት ሰው አንድ አዛውንት ከአካባቢው በመያዝ ወደ ሦስት አዋቂ ቤቶች በመሄድ የቃጠሎውን ምክንያት ይጠይቃል፡፡

ቦዠ አንድን ቤት የሚያቃጥለው በሁለት ምክንያት ነው ተብሎ በማኅበረሰቡ ይታመናል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የቤቱ ባለቤት ሸነ ወይም አረር ያለበት ንብረት ላይ ጉዳት በማድረሱ፤ አሊያም ቦዠን የሚያንቋሽሽ ንግግር በመናገሩ ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ቦዠ ሰይጣንን ሲያባርር ሰይጣኑ ቤት ውስጥ በመግባቱ ምክንያት ሰይጣኑን ለማቃጠል ቤቱንም አብሮ እንዳሚያቃጥለው  ይታመናል፡፡ ከሁለቱም ምክንያቶች በመጀመሪያው ማለትም ሸነ ወይም አረር በተሰቀለበት ንብረት ላይ ሥርቆት/ጥፋት በማድረሱ ቤቱ ከተቃጠለ  በአዋቂው ይህ ይነገረዋል፡፡

ይህንንም በሽማግሌዎች ፊት በመናገርና የበደለውን ሰው በመካስ፣ በርቸውን አውጥቶ ቤቱ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡ ማጋው ቤቱን እንዲሰራ እስካልፈቀደና መፈፀም ያለበትን ሥርዓት እስካልፈፀመ ድረስ ግን፣  ቤቱን መስራት አይችልም፡፡ ከማጋው ፈቃድ ውጪ አሊያም በርቸውን ሳይጨርስ ቤቱን ቢሰራ በድጋሚ ቤቱን ቦዠ እንደሚያቃጥልበት ይታመናል፡፡

[1] በየጎሳው ሃገረሰባዊ እምነት ሥነሥርዓት መፈፀሚያ ቤተ መቅደሶች የሚገኙባቸው ጫካዎች መጠሪያ

[2] የየጎሳው ሃገረሰባዊ እምነት መሪዎች መጠሪያ  ስያሜ

[3] አምባር

[4] ቃጭል

[5] ለመድሃኒትነት ጥቅም ላይ የሚውል የእንሰት ዓይነት

[6] ከተፈፀመ በቆየ ኃጢአት ምክንያት፣ ዘግይቶ የሚመጣ የአምላክ ቅጣት፤

 

ሳምንት ይቀጥላል

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com