ዜና

መላ የወባ ትንኞች እንዳይናደፉ

Views: 638
መልካሙ ዜና እንደዚህ ይላል፡- ማጣቀሻ አንድ

ኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ፋና ብሮድካስቲግ ኮርፖሬት፤ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ስለ ወባ በሽታ ጉዳይ “በኢትዮጵያ ከወባ በሽታ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱም ታውቋል፡፡”  ብሎ ነበር፡፡

“ባለፉት 5 ዓመታት

1ኛ/ የወባ ትንኝ መራባትን የመቆጣጠር ሥራ፣

2ኛ፣ የቤት ለቤት የኬሚካል ርጭት፣

3ኛ/ የአጎበር ሥርጭት፣

4ኛ/ የህክምና አገልግሎት አቅርቦትን የማጠናከር ሥራዎች

“በመከናወናቸው በወባ የሚጠቁና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ መቀነሱን የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይገልጻል፡፡”

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ  ትንበያ  ማጣቀሻ ሁለት

በአጠቃላይ በመጭው ክረምት 2019 የተመረጡ ‹‹አናሎግ›› አመታት የዝናብ፣ ሙቀትና ምዛና የአየር እርጥበትን እና በመ/ቤቱ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ የዝናብ ትንበያን መሠረት በማድረግ ለወባ መፈጠር ምቹ የአየር ሁኔታ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቁት አካባቢዎች

 • አብዛኛው የክረምት ተጠቃሚ ዝቅተኛና መካከ ቦታ ያላቸው የሀገሪቱ ክፍሎች እንዱሁም
 • የወባ በሽታ ተጋላጭ ቦታዎችን ጨምሮ ትም ምዕራብ ትግራይ፣ ምዕራብና ምስራቅ አማራ፣ ምዕራብና ቡብ አፋር፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ጋምቤሊ አካባቢዎች፣

በመጭው ክረምት 2019 ለወባ መፈጠር አመች የአየር ሁኔታ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ከመስከረም ወር በኋላ ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት የወባ በሽታ አምጭ ትንኝ የመቆየት እድል ከፍተኛ ሊሆን ይችላል፡፡

በመልካሙ ዜናም ሳንፈነድቅ፣ በስጋት ዜናም ሳንርበተበት ማድረግ የሚገባንን በትጋት መወጣት ግድ ይላል፡፡ እውነት ነው፤ አገራችን የተሰጣት ዕውቅና እና ሽልማት ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ በዚህ በተባለው ደረጃ ለመቆየት የሁሉም ጥረት ያስፈልጋል፡፡ የምናደርገው ጥረት በሁላችንም ዘንድ የቻልነውን ያህል መሆን አለበት፡፡ ይህ በሽታ የሚተላለፈው በትንኝ ነው፡፡ እንዴት ትንኝን ታህል ትንሽ እንስሳ መከላከል ያቅተናል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት 4 ዋና ዋና የመከላከያ ጉዳዮችን ማጠናከር እንዳለ ሆኖ ሌሎችም ተጨማሪ ደጋፊ ዘዴዎችን እንመልከታለን፡፡

መነሻ ጉዳይ፡-

በዓለም ደረጃም ሆነ በአገራችን ትንኞች ሰውን በመናደፍ አስቸጋሪ ናቸው፡፡ በምድራችን ላይ ከፍተኛ ገዳይ እንስሳት ትንኞች ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በጣም ጎጂ የሆኑት የወባ ትንኞች አደገኛ የበሽታ ዓይነት አስተላላፊ ናቸው፡፡ በጥቅሉ ሲነገር የወባ ትንኞች

 • የወባ በሽታ (malaria)
 • ቢጫ ወባ (yellow fever)
 • የደንጊ በሽታ Dengue fever (DF) mosquito born viral
 • ቺኩን ጉንያ ቫይረስ (Chikungunya virus) ፣ እና ሌሎችንም የበሽታ ዓይነት አስተላላፊ  ናቸው፡፡

ወባ ለብዙ ዘመናት ሲያሰቃየን የኖረ ሲሆን፣ ቺኩንጉንያ የተባለው ደግሞ በቅርቡ ድሬዳዋ ከተማ ተከሰተ የተባለው፣ ትኩሳት ያለው እና መገጣጠሚያን የሚያሳምም ዓይነት በሽታ ነው፡፡ ቀደም ብሎም በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች የደንጊ በሽታ እና ቺኩን ጉንያ መከሰቱ ይታወሳል፡፡

የወባ ትንኞች በሽታን ወይም የበሽታን ተውሳክ በንድፈት (ንክሻ) ከአንዱ ወደ ሌላው ያስተላልፋሉ፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ትንኞች በሽታ አስተላላፊም ባይሆኑ ንክሻቸው ወይም ሲናደፉ ያሳምማሉ፣ የሰውነት መቆጣት ያስከትላሉ፣  ሰዉን ይረብሻሉ፣ እንቅልፋ ይነሳሉ፣ ቆዳችን ይቀላል ወይም ያጉረበርባል፣  ወዘተ፡፡

ስለሆነም በተቻለ መጠን አቅም በፈቀደ ሁኔታ፣ ፀባያቸውን መሠረት አድርገን እንዴት ትንኝን ማባረር እንደምንችል እነሆ ጥቂት መላ መላ፡፡

1/ የተለመዱትን የመከላከያ ዘዴዎች ምንጊዜም አስተውሉ

የወባ ትንኝ ድሮ ድሮ “በሞቃት አካባቢ ትራባለች፣ ትገኛለች ይባል”  ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ሙቀት ያልጨመረ አካባቢ የለም፡፡ ስለሆነም፣ በሐሩር ቆላ፣  በቆላ፣ በወይናደጋ፣ በደጋ፣ ወይም በገጠር፣ በከተማ ሁሉ ልትገኝ ትችላለች፡፡ ስለሆነም፣

 • የታቆረ ቆሻሻ ውሃ ማፋሰስ እና ማስወገድ፣
 • የሚረጨውን መድኃኒት ማስረጨት፣
 • በፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል የተነከረ መከላከያ አጎበር በአግባብ መጠቀም፣
 • የበሽታ ምልክት እንደታየ ሕክምና ማድረግ፤
 • ሌሎችም በየጊዜው የሚነገሩትን ምክሮች መከታተል፣
 • ትንኝ ለመከላከል የሚሆኑትን ማንኛውንም ዘዴዎች መጠቀም እና
 • የሚቀቡ ዘይታማ ቅባትን ወይም ክሬሞችን አስቀድሞ አለርጂ ያስከትሉ እንደሆን ማጣራት እና ተስማሚ ከሆኑ በተለይም ለወባ ትንኝ ንክሻ ተጋላጭ የሆኑትን ፊትን፣ እጅን፣ አንገት እና እግር መቀባባት እና ማለዳ መታጠብ ያስፈልጋል፡፡
 • በቀንም በትንኝ መነደፍ እየተከሰተ ስለመጣ፣ በፀሐይ ብርሃን ውስጥ ቅባታማ ነገር ከመቀባት ይልቅ የተፈጥሮ ቅጠሉን መጠቀም ይሻላል፡፡
 • ዘይታማ ቅባት ምንጊዜም ከሌላ ተስማሚ ዘይት ወይም ቅባት ጋር በመጠን ይቀየጣል እንጂ ብቻውን አይቀባም፡፡

2/ ትንኞች በጣም የሚወዷቸውን ነገሮች ለዩ፤ ማጣቀሻ ሶስት

አዴስ አጂፕቲ Aedes aegypti   የምትባለውን የወባ ትንኝ ዝርያ ዓይነት በተለይ

 • የሰው ላበት ይስባታል
 • ነጣ ካለው ይልቅ ጥቁር ወይም ጠቆር ያለ ልብስ ይማርካታል፣
 • የውሃ ላይ እንቦጭ፣ የውሃ ላይ አረም፣ ወተር ሊሊ እና ወተር ሌትዩስ የሚባሉ የውሃ ላይ ተክሎችን በጣም ትወዳለች፣
 • ፓፒረስ የሚባለውን በሐይቅ ደርቻ የሚበቅል ወፍራም ቄጠማ የሳር ዓይነት ይወዳሉ፣
 • በፖታስየም የዳበሩ ምግቦች (ሙዝ፣ ድንች፣ ፕሩነስ፣ ሊማ ቢን፣ አቮካዶ፣ እስፒናች እና የመሳሰሉት) እነዚህን ምግቦች ተመግበን በላበት ውስጥ ላክቲክ አሲድ (Lactic acid ) ስለሚመነጭ ይህ ለሷ “ውስጧ” ነው፡፡
 • ጨው የበዛው ምግብ የተመገበ ሰው ላበት ለሷ “ነፍሷ” ነው፣
 • ከቀጭን ሰው ወፍራም ሰዎችን፤ ከሁሉ ሴቶች እርጉዝ ሴቶችን ትመርጣለች፣
 • ከብርሀን ጨለም ያለ ቦታ ትመርጣለች፣
 • ከማትወደው ሽታ (ጠረን)፣ ጣዕም፣ ጭስ፣ ትርቃለች፣
 • ሴቷ የወባ ትንኝ ለመራቢያ የሰው ደም ለመምጠጥ ስትፈልግ በሰው ትንፋሽ የሚወጣውን ካርቦንዳዮክሳይድ፣ ወይም ከሰው ላበት የሚወጣውን ላክቲክ አሲድ ትወዳለች፤ ይህንንም ጠረን እስከ 3ዐ ሜትር ርቀት ላይ ትለያለች፣

አኖፊሊስ ጋምቢየ   (Anopheles gambiae)    የምትባለው የወባ ትንኝ ዝርያ በተለይ የሰው እግር ጣቶች መሐል ያለው ሽታ ይስባታል፡፡

3/ ትንኝ አባራሪ ተክሎችን አልሙ

ትንኞች በጣም አደገኛ ነፍሳት ናቸው፡፡ ዓይነታቸው በተለይም ሰውን የሚነድፉት ብቻ ከ 1ዐዐ የዝርያ ዓይነት በላይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን “ትንኝ አባራሪ ነገሮች አሉ” ቢባልም ሙሉ በሙሉ ይሠራል ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ለአብዛኛው ይሠራል ስለሚባል መጠቀሙ አይከፋም ለማለት ነው፡፡ ማጣቀሻ አራት

በተፈጥሮ አንዳንድ ተክሎች ባላቸው ወይም በሚያመነጩት ጠረን ወይም ሽታ ብዙዎቹ የትንኝ ዓይነቶች የሸሻሉ፡፡ ስለሆነም፣ ትንኞቹ የማይወዷቸውን ተክሎች በጊቢአችሁ አልሙት እና እንደአስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ አውሉ፡፡  ብዙ ዘዴዎችን አጣምሮ መጠቀም ደግሞ የተሻለ ብልሃት ነው፡፡

ሀ. ጠጅ ሳር፣ ናርዶስ ሳር፣ ሎሚ ሳር ወይም ቬቲቨር ሳር

እነዚህ የሳር ቤተሰቦች ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ የምታገኙትን  አልሙ፡፡

 • ሊንቀሳቀስ በሚችል ዕቃ የተተከለ ከሆነ ተክሉን ማታ ወደ በር ዘንድ ማምጣት
 • እርጥብ ሣሩን በበር አካባቢ መጎዝጎዝ ፣
 • እርጥብ ወይም ደረቅ ሳሩን በመቀቀል እቤት ውስጥ ማትነን፣ ወይም በፍም ላይ ማጨስ
 • ከእነዚህ የሣር ተክሎች መዓዛማ ዘይት አምራቹ በሚነግረው መርህ መጠቀም፤

ጠጅ ሳር እና አጁባን በአንድ ላይ ለመጎዝጎዝ ይቻላል፡፡

በቀኝ ሎሚ ሳር በግራ ቬቲቨር ሳር

 ለ. ነጭ ሽንኩርት

 ጥቂት ፍንካች ጥሬ ነጭ ሽንኩርት ማታ መመገብ፤ በላበት የሚወጣው ሽታ አባራሪዋ እንዲሆን ይረዳል፤

 • በር አካባቢ እና በሚተኙበት አካባቢ መክተፍ እና መበተን፣
 • ነጭ ሽንኩርት መፍጨት፣ በውሃ በጥብጦ አስፈላጊ በሆነ ቦታ መርጨት፤

 ሐ. ናና፣ ፔፐርሚንት ወይም ሌሎች መሰሎቹ

ናና  (ነአነአ)፣  የተፈላ ሻይ ላይ ጣል የሚደረግ ቅጠል በመሆኑ፣ እውቅና አለው፡፡ ፔፐርሚንት እንጨቱ ጠቆር ያለ እና ጠረኑ ከነአነአ ይበልጥ ይጠነክራል፡፡

 • ናና ወይም ፔፐርሚንት ቅጠል የወባ ትንኝ አባራሪ ናቸው፡፡
 • ተክሉን ማታ ወደ በር ዘንድ ማምጣት ወይም እርጥብ ቅጠሉ ማታ መጎዝጎዝ፣
 • ከሌሎች ወይም ብቻውን በመቀቀል እንፋሎቱን በቤት ውስጥ ማትነን፤
 • ከናና እና ሌሎች የናና መሰሎች የተገኘውን መዓዛማ ዘይት በሚነግረው መርህ መጠቀም፣
 • መዓዛማ ዘይቱን ከሌሎች ቅባት ወይም ሎሽን ጋር ቀይጦ መቀባባት፣
 • ቅጠሉን ፊት፣ አንገት፣ እጅ እና እግር ላይ ማሸት ትንኝን ለማራቅ ይረዳል

መ. በሶቢላ ፣ አጁባን፣ እና መሰሎቹ መዓዛማ ተክሎች

የበሶቢላ ቤተሰብ የሆኑት ብዙ አሉ፡፡ ለምሳሌ በአገር ውስጥ በብዛት የሚገኘው በሶቢላ፣ የዱር በቀል የፍየል ዝቃቅቤ፣ የፈረንጅ በሶብላ፣ አጁባን እና ዳማከሴ ትከሉ፡፡

 • በተንቀሳቃሽ እቃ ብትተክሉት ማታ ወደ በር አካበቢ ማስቀመጥ፡፡
 • ቅጠሉን በርና መስኮት ላይ ማንጠልጠል፣ ወይም መጎዝጎዝ፣
 • ማታ እና ንጋት ላይ በመቀቀል በቤት ውስጥ እንፋሎቱን እንዲያውድ ማድረግ፣
 • ፊት ላይ፣ አንገት ላይ፣ እጅ እና እግር ላይ ቅጠሉን ማሸት ይረዳል፣

ከእነዚህ የተገኘ መዓዛማ ዘይት አምራቹ በሚነግረው መርህ መጠቀም፤

በግራ አጁባን በቀኝ ቢጫ ታጌታስ (ሜክሲኮ ሜሪጎልድ)

ሠ. ታጌታስ (ሜክሲኮ ሜሪጐልድ)

የሜክሲኮ ሜሪጐልድ በየጊቢው እና አልፎ አልፎ ዱር በቀል ይገኛል፡፡ ቢጫ ወይም ደማቅ ቀይ አበባ ያብባል፤ ሃይለኛ ጠረን አለው፡፡ ብዙ የተባይ ዓይነትን በተለያየ ዘዴ ተከላካይ ነው፡፡

 • ትንኝ አባሪራ ስለሆነ በር አካባቢ መትከል፣ ወይም ቅጠሉን መጎዝጎዝ
 • በእቃ የተተከለ ከሆነ ባስፈለገ ጊዜ ወደ በር ማስጠጋት፣

ረ. ላቬንደር

ላቬንደር ተክል ችግኙን ወይም ግንጣዩን መትከል ይቻላል፡፡ (በዚሁ መረጃ መረብ ላይ ፀጉርን እንዲህ ተንከባከቡ) የሚለው ርዕስ ሥር ስለ ልማቱ ማንበብ ይቻላል፡፡

 • እርጥቡን የላቬንደር ቅጠል ቀንም ሆነ ማታ በመቀቀል እንፋሎቱን ማትነን፣
 • ደረቁ የላቬንደር ቅጠል በጥጥ ጨርቅ ተደርጎ ትራስ ሥር ሲደረግ ለጥሩ እንቅልፍ ይረዳል፤ ትንኝን ግን ያባርራል፣
 • ማታ ሊተኙ ሲሉ በሻይ መልክ መጠጣት ጥሩ ነው፤
 • መዓዛማ ዘይቱን በማትነኛ ውሃ ላይ ጠብ አድርጎ ቤትን ማወድ፣
 • አምራቹ በሚሠጠው መመሪያ መሠረት መዓዛማ ዘይቱን ከሌሎች ቅባት ጋር ቀይጦ መቀባባት ይቻላል፡፡

ሰ. ሮዝመሪ፣ ሴጅ፣ ሌመን ባልም፣ ካትኒፕ

 • እነዚህን ተክሎች ከላይ ለሌሎቹ እንደተነገረው ማልማት እና መጠቀም ጥሩ ነው፡፡
 • ከነሱ የተገኘውን መዓዛማ ዘይት ከሌሎች ቀይጦ መጠቀም፣

ትንኝ አባሪራ ስለሆኑ  በር አካባቢ መትከል፣

በግራ ላቬንደር በቀኝ የሴጅ ተክል

4/ መዓዛማ ዘይት

የሽቶ ባሕርዛፍ፣ የላቬንደር፣ የቲትሪ፣ የሲትሮኔላ፣  የአኩሪ አተር፣ የጦስኝ፣ የቀረፋ፣ የኒም፣ እና የሌሎችን መዓዛማ ዘይት በጥንቃቄ መጠቀም፡፡ በአምራቹ የተገለፁትን መመሪያዎች ማንበብ እና በአግባብ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የወባን ትንኝ ለማባረር ማዓዛማ ዘይቶችን

 • ከሌሎች ተስማሚ ቅባት ወይም ዘይት ጋር መጥኖ አስማምቶ ለትንኝ የተጋለጡ የአካል ክፍሎችን (በተለይ ፊት፣ አንገት፣ እጅ፣ እና እግር) መቀባት፣
 • በፈላ ውሃ ላይ ጠብ አድርጎ በማትነን እና ቤትን በማወድ፣
 • ልብስ ላይ በማበስ፣
 • ከሌላ ፈሳሽ ጋር በጥብጦ አስፈላጊ ቦታ ሁሉ ላይ በመርጨት፣ መጠቀም ይቻላል፡፡

5/ ሽያ ቅቤ

ሽያ ቅቤ (Shea butter) ከዛፍ ላይ የሚገኝ ጥሩ መዳኒታማ ቅባት ነው፡፡  ምናልባት አለርጂ ከሆኑ መጠንቀቅ ነው፡፡ ማታ ማታ በመቀባት ትንኞችን መከላከል ይቻላል፡፡

6/ የተነደፈውን ቦታ በቀላል ማከም

በማንኛውም ትንኝ የተነደፈ ቦታ ይለባለባል፣ ይቀላል፣ ያማል፣ ያብጣል፣ ውሃ ይቋጥራል፣ ወዘተ ለዚህ የሚረዱ የቤት ውስጥ መፍትሔ ከሚከተሉት ውስጥ የተገኘውን በቀላሉ መጠቀም ይቻላል፡፡

 • የፈረንጅ አጃ (ኦትስ ዱቄት) በውሃ ለውሶ ቦታው ላይ መቀባት፣
 • ንፁህ ወለላ ማር መቀባት፣
 • የእሬት ዝልግልግ ፈሳሽ መለቅለቅ፣
 • የዳቦ ሶዳ (ቤኪንግ ሶዳ) በውሃ አሟምቶ መቀባት፣
 • በበሶቢላ ወይም በአጁባን ቅጠል ማሸት፣
 • በሌመን ባልም ቅጠል ማሸት፣
 • በቀይ ሽንኩርት ክፋይ ወይም በነጭ ሽንኩርት ክፋይ ማሸት፣
 • በእርጥብ ጦስኝ ቅጠል ማሸት፣
 • የቀዘቀዘ የካሞሜላ ሻይ መቀባት ወይም
 • ከአፕል የሚዘጋጅ ኮምጣጤ (አፕል ሲደር ቨኒገር) በስሱ መቀባት፣

7/ ማጥመጃ ማበጀት

እጅግ በዝተው በሚያስቸግሩበት ወራት በተለያየ ዘዴ፤ የትንኝ ማጥመጃ ማበጀት እና በዚያ ውስጥ ተሰባስበው እንዲሞቱ ማድረግ ሌላው ብልሃት ነው፡፡

8/ ልዩ ጥንቃቄ አድርጉ 

ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የምትኖሩት በተለይ፣ ልዩ ጥንቃቄን አድርጉ፡፡ ወባ መቸም የጥቂት ወራት ችግር ስለሆነ፣ ይህ ምክር አመቱን ሙሉ አይደለም እና እባካችሁ አሰልቺ አይምሰላችሁ፡፡

 • ጠቆር ካለው ይልቅ ነጣ ያለ ልበስ ልበሱ
 • እንቦጭ፣ እና ሌሎች የውሃ ላይ አረም፣ ተግታችሁ ተቆጣጠሩ፣
 • ፓፒረስ ወይም ማንኛውም ቄጠማ የሳር ዓይነት በግቢ ውስጥ አትትከሉ፣ እቤት ውስጥም ለጌጥ ብላችሁ አታስገቡ፣
 • በፖታስየም የዳበሩ ምግቦች ቢቻልስ ለማታ እራት አትመገቡ፡
 • በወባ ወራት ጨው የበዛው ምግብ አትመገቡ፣
 • ለህፃናት፣ ለእርጉዝ እናቶች እና ለሚያጠቡት የበለጠ ክብባቤ አድርጉ፣
 • ማንኛውንም ትንኝ የሚስብ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ወዘተ ማታ ከመኝታ ክፍል አርቁት፣
 • የአትክልት እና የፍራፍሬ ልጣጭ ከቤት አታሳድሩ፣
 • በር እና መስኮት ማታ በጊዜ ዝጉ፣ ሌሎችም የትንኝ መግቢያ ቀዳዳዎችን ዝጉ፣

ማጠቃለያ፣

በምድር ላይ የሚገኙ ትንኞች ከጉዳታቸውም ሌላ፤ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በጠቀሜታ ብቻም ባይሆን በምንም ጥበብ ቢሆን ትንኝን ከምድር ላይ መጨረስ አይቻልም፡፡ ስለዚህ በሽታው እንዳያጠቃን በተቻለ አቅም የተለያየ ዘዴ በመጠቀም የትንኞቹን ጉዳት መከላከል አለብን፡፡ በሽታውም ቢከሰት በወቅቱ መታከም ይገባል፡፡ ከዘመናዊ ሕክምና በተጨማሪ ሌሎች ተፈጥሯዊ የሕክምና ዘዴን በዚሁ ርዕስ ክፍል ሁለት ላይ ይቀርባል፡፡

ትንኝን ተከላከሉ፣ ጤናችሁን ጠብቁ፡፡

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ አንድ ህዳር 18፣ 2011 እ.ኢ.አ (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት

ማጣቀሻ ሁለት የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ  እ.ኤ.አ የ2019 የበልግ ወቅት የአየር ጠባይ ግምገማና

የ2019 የክረምት ወቅት የአየር ጠባይ አዝማሚያ አ ህ ፅ ሮ ት  (Executive Summary)

ማጣቀሻ ሶስት https://www.healthline.com/health/why-mosquito-bites-itch#prevention

ማጣቀሻ አራት http://theconversation.com/health-check-why-mosquitoes-seem-to-bite-some-people-more

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com