ዜና

ከኮንሶ ወደ ዞን መቀየር ጋር ተያይዞ በደቡብ ኢትዮጵያ ዝርፊያ እና ድብደባ እየተፈፀመ ነው

Views: 272

በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሰገን ወረዳና አካባቢው ነዋሪዎች ላይ ዝርፊያ፣ድብደባና እንግልት እየተፈፀመ ነው፡፡ ዝርፊያው የተፈፀመው ቤት ለቤት በመዘዋወር ነው፡፡ ዝርፊያ ፈፃሚዎቹ በኮማንድ ፖስት የሚመሩ ታጣቂዎች መሆናቸውንም የአካባቢው ኗሪዎች ገልፀዋል፡፡ ግጭቱ የተፈጠረው የሰገን አካባቢ ሕዝቦች ዞን ወደ ኮንሶ ዞን ሲቀየር የንብረት ክፍፍልንና የሠራተኞች ድልድልን በተመለከተ በነዋሪዎች ላይ በተፈጠረ ግጭት መሆኑን የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሓላፊው አቶ አንድነት አሸናፊ በተለይ ለኢትዮ ኦን ላይን ገልፀዋል፡፡

እንደ ሓላፊው ገለፃ የኮማንድ ፖስት አባላት ግጭቱን ለማረጋጋት ሲሉ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ነሐሴ 14 ቀን ወደ ሰማይ ተኩሰዋል፡፡ ቤት ለቤት በመዘዋወርም በፍተሻ የጦር መሳሪያዎችን ማስፈታታቸውን ገልፀዋል፡፡ ‹‹ይህ የተሰጣቸው ስልጣን ነው፡፡ ፍተሻው ሕጋዊ ነው፡፡ ወደ ፊትም ይቀጥላል፡፡›› ብለዋል አቶ አንድነት አሸናፊ፡፡

በአንፃሩ የኮንሶ ባለሥልጣናት በሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እየታጀቡ እቃ ሊወስዱና አካባቢውን ሊረከቡ እንደሄዱ በመግለፅ በጉማይዴ ከተማ ሁከት እየፈጠሩ እንደሆነም ኗሪዎች ገልፀዋል፡፡ የዞን ሠራተኞችና የሰገን ከተማ አስተዳድር ሠራተኞች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የሐምሌ ወር ደሞዛቸው ታግዷል፡፡ ሠራተኞቹ አቤቱታቸውን በማቅረብ ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

ለሊቱን መሳሪያ ሲተኩሱ ያድራሉ የተባሉት የክልሉ ልዩ ኃይል አባላትና የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ሌሊቱ ሲነጋ አርሶ አደሮችን ‹‹እናንተ ናችሁ የተኮሳችሁት›› በሚል በድብደባና እስር እያሰቃዩ መሆኑንም የአካባቢው ምንጮች ገልፀዋል፡፡ ተጎጂዎቹ ወደ ሕክምና ተቋም እንዳይሄዱም መከልከላቸውን ገልፀዋ፡፡ የክልሉ የሰላምና ደህንነት ቢሮ ሓላፊ በበኩላቸው አንድም ሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን ገልፀዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com