“የሳጥናኤል አበሳ” ቴአትር ቅዳሜ ለመድረክ ይበቃል

Views: 350

በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ በወለፈንድ (አብሰርድ) የቴአትር ጽሑፍና ዝግጅት ዘውግ የሚታወቀው የመምህር ጌታቸው ታረቀኝ ‹‹የሳጥናኤል አበሳ›› የተሰኘ ቴአትር፣ በመጪው ቅዳሜ በብሔራዊ ቴአትር እንደሚመረቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

‹‹የሳጥናኤል አበሳ›› ወለፈንድ ቴአትር፣ በአንጋፋው ተዋናይና የመድረክ ሰው ተስፋዬ ገብረሃና የተዘጋጀ ሲሆን፣ ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር በድምቀት ይመረቃል ተብሏል፡፡

የቴአትሩን የምረቃ መርሃ-ግብር እና ትግበራ ለማስተዋወቅ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጸሐፈ-ተውኔት እና የዩኒቨርስቲ መምህር ጌታቸው ታረቀኝ፣ ወለፈንድ (አብሰርድ) እና ሌሎች ዘውጎች ተውኔቶችን ከመፃፍና ለመድረክ ከማብቃት ባሻገር፣ በመጽሐፍ መድብል በማውጣት ቴአትርን ለአንባቢያን በማቅረብ ይታወቃል፡፡  ‹‹ቤጊዮሎጂ››፣ ‹‹ደራሲው በሰማይ ቤት›› እና ‹‹ማሙሽና በርባን›› ደግሞ በጣም ተወዳጅ ወለፈንድ ተውኔቶቹ ናቸው፡፡

ነዋሪነቱን በአሜሪካን አገር ያደረገው ደራሲ ጌታቸው ታረቀኝ፣ ከሀገር ከመሰደዱ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቴአትር መምህርነት፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ባሕልና ቴአትር ማዕከል (ማዘጋጃ ቤት) በሥራ አስኪያጅነት ማገልገሉ ይታወሳል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com