ሲፒጄ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ለመንግሥት ጥሪ አቀረበ

Views: 153

ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ቡድን (ሲፒጄ)፣ በፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ድብቅ ካሜራ ይዘህ ገብተኃል ተብሎ በእስር ላይ የሚገኘውን ጋዜጠኛ ምስጋናው ጌታቸው፣ ከእስር እንዲፈታ ጥሪ አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኛውን እንዲለቀውና የፀረ-ሽብር ዓዋጁን ከለላ በማድረግ ጋዜጠኖች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳይገልፁ የሚያደርገውን አሰራር ማቆም ይገባዋል፡፡

በሕጉ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት እና የመረጃ ተደራሽነት የሚሉትን እንዲጠብቅ እንጠይቃል ሲል ሲፒጄ አስታውቋል፡፡

‹‹አፍሪካን ኒውስ ኤጀንሲ›› እንደዘገበው፣ ጋዜጠኛው በአዲስ አበባ ከአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውጪ የሕግ ባለሙያው የሆነውን ሄኖክ አክሊሉን ቃለ መጠይቅ ካደረገለት በኋላ፣ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ገልጿል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት ጀይላን አብዲ እንደሚሉት ደግሞ፣ ጋዜጠኛው በቁጥጥር ስር እንዲውል የተደረገው ቪዲዮ የሚቀርፅ የዓይን መነፅር በፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ያለ ፍቃድ አድርገህ ለመቅረፅ ሞክረሃል በሚል በፖሊስ መኮንንኖች እንደተያዘ ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቷ ፌደራል ፖሊስ ለሲፒጄ እንደገለጸው፣ ጋዜጠኛ ምስጋናው የተያዘው በፍርድ ቤቱ ግቢ ውስጥ ያለፍቃድ ቀረጻ አድርጓል በሚል ሲሆን፣ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ጋዜጠኛው የተያዘው በአማራ ክልል በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት እጁ አለበት በሚል እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ጋዜጠኛ ምስጋናው የፍርድ ቤት ጉዳይ ላይ ዘገባውን ካቀረበ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉ ኢትዮጵያ ሀሳብን የመግለፅ መብትን የፀረ-ሽብር ሕጉ በመጠቀም ተቃውሞዎችንና ትችቶችን ዝም ለማሰኘት ከዚህ በፊት በሀገሪቷ ይደረግ የነበረው የማፈን ሥርዓት ልትመለስበት ነው ያሉት በሲፒጄ ከሰሃራ በታች ላሉ አፍሪካ አገራት ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ ናቸው፡፡

ነሐሴ 4 ቀን 2011 ዓ.ም ጋዜጠኛው ችሎት የቀረበ ሲሆን፣ የፀረ-ሽብርተኝነት ዓዋጁን በመጣስ ክስ ተመስርቶበት ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀናት ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ባለፈው ወር ከአስራት ሚዲያ በሪሁን አዳና እና ጌታቸው አምባቸው የተባሉ ጋዜጠኞች መታሰራቸውንና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ በባልደራስ ጉዳይ በሽብር ወንጀል ተከሶ እንደሚገኝም አፍሪካን ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቦታል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com