የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ፍላጎቶች ጨምሯል ተባለ

Views: 137

በተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የህፃናት ጉዳይ ድንገተኛ ፈንድ (ዩኒሴፍ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ፍላጎቷ ጨምሮ እንደቆየ አስታወቀ፡፡

ከፈረንጆቹ 2019 ጥር ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶች፤ የወረርሽኝ በሽታዎች፤ በድርቅና በጎርፍ እንዲሁም በሌሎች አስቸኳይ ምክንያቶች ሳቢያ በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜያት የሰብዓዊ ፍላጎቶች ተባብሶ እንደቆየ የዩኒሴፍ የስድስት ወር ሪፖርት ገለጸ፡፡

ከባለፈው ጥር ወር እስከ ሰኔ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ፤ በጉልበት ብዝበዛ፤ በጥቃት እና በስደት ከሚገኙ እና የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ከተለዩ ከ አራት ሚሊዮን በላይ ህፃናት ውስጥ 1.9 ሚሊዮን የሚሆኑት በእርስ በእርስ ግጭት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የቆዩ እና አንፃራዊ ሰላም ሲፈጠር ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

በሀገሪቷ በተፈጠሩ ሰው ሰራሽም ሆነ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች የተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ እንደ ጤና ባሉ ለዜጎች በጣም አስፈላጊ አገልግሎቶች ላይ ተፅዕኖ አድርጓል ሲል ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 863 ሰዎች በኮሌራ፤ 10341 ሰዎች በኩፍኝ በሽታ እና በአንድ ሰው ላይ የፖሊዮ ጉዳት እንደደረሰ የዩኒሴፍ ሪፖርት ይገልፃል፡፡

በተለይም በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የነበረው የሰብዓዊ ቀውስ ከፍተኛ እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡

ከጥር ወር ጀምሮ በሀገሪቱ እየተባባሰ የመጣው የህፃናት የምግብ እጥረት ተጋላጭነት፤ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭነት፤ የስነ ልቦና ጭንቀት፤ ግጭትና በደል እንዲሁም የተፈናቀሉ ህፃናት የትምህርት ዕድል እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኖ እንደቆ ተጠቅሷል፡፡

በፈረንጆቹ 2019 የካቲት ወር ላይ ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 3.2 ሚሊዮን ደርሶ የነበር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1.9 ሚሊዮኑ ህፃናት እንደሆኑ ታውቋል፡፡

ከመጋቢት ወር ጀምሮ ስደተኞችን ወደ አካባቢያቸው በማስመለስ ሂደት ውስጥ 1.4 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንደተመለሱም በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ሆኖም ግን የተፈናቀሉት ዜጎች ወደ አካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላ የመጠለያ ፤ የምግብ እርዳታ እንዲሁም የፀጥታ ሁኔታው እንዲረጋገጥላቸው ይፈልጋሉ፡፡

ተፈናቃዮቹ ወደ አካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላ እንዲደገፉ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲሁም ዘላቂ የኑሮ ደረጃዎችን እንዲያገኙ ወሳኝ ኢንቨስትመንቶች ያስፈልጋሉ ተብሏል፡፡

በመጨረሻም ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትና በጤና ፤በትምህርት ፤በምግብ እና በህፃናት ጥበቃ ዘርፎች ስደተኞችን ለመደገፍ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com