‹‹የወሎ ማንነት ኢትዮጵያዊነት ነው››

Views: 227

የወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማሕበር

  • ሕዝቡ በመቻቻል እና በትዕግስት ማለፉም እንደ ፍርሃት ተቆጥሮ የጥቃቱ መጠን እየጨመረ ነው ተብሏል

የወሎ ክፍለ ሀገር ታሪክ የተለያዩ ጎሳዎችን አቅፎ በተውጣጣ ባሕልና እምነት የዳበረ ማንነት ባለቤት ነው ሲል የወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማሕበር በመግለጫው ላይ አስረድቷል፡፡

ማህበሩ የአንድነት ምሳሌና ናሙና የሆነው እንዲሁም የሚያኮራውን ይህን ክፍለ ሃገር ከ28 ዓመት ወዲህ በተፈጠሩ ቡድኖች ሌላ ስምና መልክ እየሰጡት እንደሆነ ገልጿል፡፡

ይህም፣ በቤተሰብነት ደረጃ ተዋልዶና ተዛምዶ የኖረውን ሕዝብ ጭረሽ በማያምንበት የሴራ ገመድ እየተበተቡት እና እርስ በእርስ እንዲጋጭ ከማድረግ በተጨማሪ ኢትዮጵያን ከማፈራረስ ዓለማ በመነሳት ሕብረተሰቡን ነጥሎ ጥቃት እየተፈጸመበት ነው ብሏል በመግለጫው፡፡

በተለይም ለኢትዮጵያ ዋልታና ማገር የሆነው የአማራውን ሕብረተሰብ ነጥሎ በማጥቃት፣ መሬቱን በመንጠቅና በማፈናቀል የክተት ዓዋጁ ከታወጀ ዓመታት አልፎታል ሲልም አስታውቋል፡፡

ሕዝቡ በመቻቻል እና በትዕግስት ማለፉም እንደ ፍርሃት ተቆጥሮ የጥቃቱ መጠን እየጨመረ ነው ሲል የወሎ የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማሕበር በመግለጫው ላይ አብራርቷል፡፡

የዚህ ክፍለ ሀገር አዋሳኝ ከባቢያዎችን በመዋጥ ይዞታቸውን ለማስፋት በሰሜን በኩል የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር፣ በመሐልና በምስራቃዊ ደቡብ በኩል የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ) ኃይላቸውን አሰማርተው ጥቃት በማድረስ ላይ ናቸውም ብሏል፡፡

የወሎ ክፍለ ሀገር ነዋሪዎችን እንወክላለን፤ ተገደው የተያዙ ዜጎቻችንና ቦታውም የእኛ ይዞታ የነበረ ነው የሚሉ ቡድኖች መኖራቸውም ለጥቃቱ መድረስ ምክንያቶች እንደሆነ አስረድቷል፡፡

ማህበሩ እንደገለጸው ከሆነም በወሎና በሌላም ክፍላተ ሃገር ውስጥ ግን የዚህና የዚያ ጎሳ መሬት ተብሎ ተሸንሽኖ የተቀመጠ ታሪክ እንደሌለ ገልጿል፡፡

አሁን የይገባናል ጩኸትና የጥቃት እርምጃ በሚታይበት የወሎ ክፍለ ሃገር ስም ተደራጅተን የምንቀሳቀስ ማሕበር በመሆናችን  የክፍለ ሃገሩን ታሪካዊ ይዘትና መልክ ለማሳየት ብሎም ለማስከበር አስፈላጊ ከሆነም በታታኝና አፍራሽ ኃይሎች በመጡበት መንገድ ለመመለስ የሚገደድበት ደረጃ ላይ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

በመሆኑም፣ የዚህ ሀሉ ችግር መንስዔ ኢህአዴግ ራሱ ያስቀመጠው ሕገ መንግስት መሆኑን በመግለጫው ላይ አመላክቷል፡፡

የጎሳ መተካካትና የግለሰቦች መቀያየር መፍትሔ እንደማይሆን በገሃድ የታየ ሀቅ ነው ያለው ማሕበሩ፣ በባዶ ቃላት መጭበርበር ይብቃ በጆሯችን ሳይሆን በአይምሯችን እንመራ ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com