ዜና

ኢሕአፓ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች አጋርነቱን እንደሚቀጥል አስታወቀ

Views: 722

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በኢትዮጵያ ውስጥ ለነፃነት፣ ለፍትሕ እና ለእኩልነት የሚያደርገውን ትግል እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡ ለአርሶ አደሮች፣ ለሠራተኞች ብሎም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ማሕበረሰብ ሁሉ አጋር እንደሚሆንም ጠቁሟል፡፡

የፓርቲው የአመራር አባላት ካለፈው ነሐሴ 11 እና 12 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ካዛንቺስ በሚገኘው የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ጥናታዊ ጉባዔ አካሂደዋል፡፡ በጉባዔው ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ አርባ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡ በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ የወጣት ዘርፍ አመራሮችም በጉባዔው ተገኝተዋል፡፡

ዓውደ ጥናቱ፣ በፓርቲው ታሪክ፣ ኢሕአፓ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ባደረገው ተሳትፎ ላይ ስለሚቀርቡ ቅሬታዎች፣ ማሕበራዊ ዴሞክራሲ ላይ በሚያተኩረው የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም ላይ፣ በኢትዮጵያ ሊኖር ስለሚገባው የፌዴራላዊ ሥርዓት አወቃቀር፣ በወቅታዊ የፓርቲው እንቅስቃሴ፣ የአባላት አደረጃጀት እና የአመራር መሠረታዊ እውቀት ላይ ያተኮረ እንደነበር ፓርቲው ለኢትዮ ኦን ላይን በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

ማሕበራዊ ዴሞክራሲ የተሰኘው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ሠራተኞችን እና ሌሎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎችን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡

ኢሕአፓ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን አባላቱ እና አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም ፓርቲው አሳስቧል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com