“የችርቻሮ ሱቆች የሕገወጥ ነጋዴዎች ምርት ማራገፊያ ሆነዋል”

Views: 554

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት፣ በክፍለ ከተማው “የሕገወጥ ነጋዴዎች ምርት ማራገፊያ ሆነዋል” ያላቸውን የችርቻሮ ሱቆች ማሸጉን ገለጸ፡፡ ሱቆቹ ሸቀጥ የሚረከቧቸው ሕገወጥ ነጋዴዎች፣ ምርቶችን በኮንትሮባንድ ያስገባሉ፤ ያስገቡትን ምርት ደግሞ ያለደረሰኝ በቅናሽ ዋጋ ለባለ ሱቆች ያስረክባሉ ሲል ለኢትዮ-ኦንላይን አስታውቋል፡፡

የቂርቆስ ክ/ከተማ የኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት፣ “ከመርካቶ ዕቃ የገዛችሁበትን ደረሰኝ አልያዛችሁም” በሚል፣ ሱቃቸውን ያሸገባቸውን የሸቀጣ-ሸቀጥ ባለቤቶችን ቅሬታ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሆኖም፣ የክፍለ ከተማው የኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት፣ 24 የሚሆኑ ድርጅቶችን ብቻ ማሸጉን ነው ለኢትዮ-ኦንላይን የገለጸው፡፡

በቂርቆስ ክ/ከተማ የወረዳ 02 አስተዳደር የኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት፣ የንግድ ክትትል እና ቁጥጥር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ቲቶ በየነ፣ ሱቆቹ የታሸጉበትን ምክንያት ሲያስረዱ ማነኛውም ቸርቻሪ ነጋዴ ከጅምላ ነጋዴው ዕቃዎችን ሲገዛ በደረሰኝ መሆን አለበት፡፡

ነገር ግን፣ ነጋዴው ሲሸጥ በደረሰኝ እንዲሸጥ አይጠበቅበትም፤ ሆኖም፣ ትክክለኛውን የዋጋ ተመን በድርጅቱ ላይ መለጠፍ ደግሞ ግዴታው ነው፤ በተጨማሪም የንግድ ፍቃድን በሚታይ ቦታ መስቀል አለበት የሚለውን መመሪያ ማክበር አለባቸው፤ ሆንም ይህን ያልተገበሩትን አሽገናል ብለዋል፡፡

በየአካባቢው የምናያቸው የችርቻሮ ሱቆች “የሕገወጥ ነጋዴዎች ምርት ማራገፊያ ሆነዋል፡፡” እነዚህ ሕገወጥ ነጋዴዎች ምርቶችን በኮንትሮባንድ ያስገባሉ፤ ያስገቡትን ምርት ደግሞ ያለደረሰኝ በቅናሽ ዋጋ ለባለ ሱቆች እንደሚያስረክቡ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሕገወጥ የንግድ ሂደት ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ለመንግሥት ግብር አይከፍሉም፤ በደረሰኝ የሚሸጡ ሕጋዊ ጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች ደግሞ ግብር እየከፈሉ በአግባቡ ለመስራት ሲሞክሩ ከገበያው ከስረው የሚወጡበት አጋጣሚም እንዳለም አቶ ቲቶ ጠቁመዋል፡፡

ሌላው ደግሞ ችርቻሮ ሱቆች ላይ የተስተዋለው ችግር ቀደም ብለው ያመጡትን ምርት ተወደደ ሲባል ያለአግባብ ዋጋ ጨምረው ይሸጣሉ፤ ይህን ሁሉ ሕገወጥ ሥራ ለመግታት ነው ሱቆቹ የታሸጉት ብለዋል፡፡

ከመርካቶ ስትገዙ ደረሰኝ አልሰጥም ያላችሁ አከፋፋይ ካለ ስሙንና አድራሻውን ጽፋችሁ ስጡን ባለ ድርጅቱ ሲከሰስም ምስክር ትሆኑናላችሁ ብለናቸውም ነጋዴዎቹ ሌላ ጊዜ ልንገዛ ስንሄድ አይሸጡልንም በማለት ከለላ ያደርጉላቸዋል ብለዋል፡፡

ሱቆቹ ከመታሸጋቸው በፊት በስብሰባ ግንዛቤ ማስጨበጫ አድርገናል፤ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል፤ ሁለቱን ማስጠንቀቂያዎች ተግባራዊ ያላደረጉ ባለሱቆችን ሱቆቻቸውን አሽገናል፤ ከዚህ በኋላ ግን አስተዳደሩ ወደ ክስ እንደሚሄድ ጠቁመዋል፡፡

ሕግን የማስከበር ሂደቱ ከስር ያሉትን ችርቻሮ ሱቆችን ወደ ሕጋዊ መንገድ በማምጣት፣ ሕገ-ወጥ አከፋፋዮቹን መጣል እንችላለን በሚል ነው ብለዋል፡፡

ነጋዴዎቹ ህብረተሰቡን ለማጭበርበር የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ ከዚህም ውስጥ ሚዛን ያጭበረብራሉ፤ ጊዜው ያለፈበት ምርት ይይዛሉ፤ እንዲሁም ያልተገባ ዋጋ ይጨምራሉ፤ ይህን ሁሉ ለማስቆም ድንገተኛ ፍተሻ እንደሚደረግባቸውና እርምጃ እንደሚወስድባቸው አቶ ቲቶ ገልጸዋል፡፡

የታሸጉት ሱቆች የተከፈተላቸው ነጋዴዎች፣ ከዚህ በኋላ ንግድ ፍቀዳቸውን በትክክለኛው ቦታ እንዲሰቅሉ፤ የዋጋ ዝርዝር እንዲለጥፉ እና የሚገዟቸውን ምርቶች በደረሰኝ እንዲሆን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነው፡፡ ይህን ካላደረጉ ግን የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ባወጣው አዋጅ መሠረት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተጠቁሟል፡፡

“ትልልቆቹ የጅምላ ነጋዴዎች ያለደረሰኝ ሲሸጡልን ምንም ዓይነት ሕጋዊ እርምጃ ያልወሰደው የክፍለ ከተማው የኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት፣ እኛን ትንንሽ የችርቻሮ ነጋዴዎች ከእነርሱ ላይ ያለ ደረሰኝ ገዝታችኋል በሚል መቅጣት አግባብ አይደለም” ሲሉ ለኢትዮ-ኦንላይን ቅሬታቸውን የገለጹ የችርቻሮ ሱቆች ባለቤቶች፣ “ሁኔታውን ለማስተካከል ከምንጩ ሳይጀምር፣ ትንሹን ወገን ለብቻ በመቅጣት ማስተካከል አይቻልም” በማለት መግለፃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com