ከደብረ ታቦር ጠላ እስከ ቡሄ ዳቦ!

Views: 376

ከወርኀ ነሐሴ ልዩ ምልክቶች አንዱ ቡሄ ነው፡፡ ቡሄ የልጆች ጭፈራ በመኾን ይታወቅ እንጂ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ግን “ደብረ ታቦር” ተሰኝቶ፣ ከተሥአቱ (ዘጠኙ) ዐበይት በዐላት አንዱ ኾኖ ይታወቃል፡፡

በዓልነቱ እንደምነው ቢሉ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ መለኮቱን የገለጸበት በመኾኑ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ደብረ ታቦር በመካከለኛው ምሥራቅ እስራኤል ሀገር ኢየሩሳሌም አካባቢ፣ ከገሊላ በምዕራባዊ በኩል ፲ ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡

ተራራው ከባህር ጠለል ፭፻፹፪ ሜትር ከፍታ ያለው ሲኾን፣ ባርቅ ሲሳራን ድል ነስቶበታል፤ (መጽ.መሳ. ፬∙—፳፬)፡፡ ታቦር ብዙ ታሪኮች የተሠሩበት ሲኾን፣ በተለይም ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከልደቱ በኋላ በ፴ኛው ዓመቱ ምሥጢረ መለኮቱን የገለጸበት ተራራ ስለመኾኑ ነው የሚታወቀው፡፡

በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የሚከበረው ደብረ ታቦር፣ በአባቶቻችን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ ትውፊት መሠረት ልዩ በኾነ መንገድ ይከበራል፡፡

ይኸውም፣ የየጉባኤ ቤቱ መምህራን የቆሎ ተማሪዎቻቸውን በማስተባበር፣ ተማሪው በኮሚቴ መልክ እየተመራረጠ በልዩ ልዩ የሥራ ክፍል ተመድቦ፣ ከየመንደሩና ከየገበሬው እህል ለምኖ፣ ጠላ በመጥመቅ የሰበካው ገበሬንና ካህናትን እየጠራ ይዘክራል፡፡

ይህ እንደዚህ ሊኾን የቻለውም፣ በአጠቃላይ ተማሪው በረከትን ከጌታችን ለማግኘት ሲኾን፣ በተለይም ደግሞ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ምሥጢረ መለኮቱን ለደቀ መዛሙርቱ እንደገለጸላቸው” ለእኛም ትምህርታችንን ይገልጽልናል በሚል ፅኑ መንፈሳዊ ተስፋ ነው፡፡

ከዚህም የተነሣ ለዝክረ ደብረ ታቦር ከሚዘጋጀው የጠላ ድፍድፍ፣ በመምህራኑ አማካይነት ውዳሴ ማርያምና መልክአ ኢየሱስ እየተደገመ፣ ለተማሪዎች እንደ ልዩ ፀበል እየታሰበ ስለሚሰጥ ብዙዎቹ በዚህ ምክንያት ብሩህ ተስፋ እንደሚያገኙ ይታወቃል፡፡

ደብረ ታቦር በዐበይት ትምህርት ጉባኤዎች ማለትም በትርጓሜ መጻሕፍት ቤት፣ በቅኔ ቤት፣ በዜማ ቤት፣ በአቋቋምና በመዝገበ ቅዳሴ ቤት፣ ልዩ መንፈሳዊ ትዝታ ያለው እንደሆነ ያለፉበት ሰዎች ይናገራሉ፡፡

እንደሚናገሩትም፣ የየጉባኤ ቤቱ ተማሪ ለደብረ ታቦር በሚደረገው ዝክር ምክንያት፣ ከአንዱ ትምህርት ቤት ወደ ሌላው ትምህርት ቤት ጥሪ እየተደረገ፣ ዳቦውንና ጥሬውን ጎዝጎዝ በማድረግ፣ ግሩም ጣዕም ያለውን የደብረ ታቦር ጠላ እየተጎነጨ፣ ልዩ ልዩ የወረብና ባህላዊ ጨዋታ ይጫወታል፡፡

ደብረ ታቦር በሌላ በኩል “ቡሄ” በሚል ስያሜ የሚታጠራው ነው፡፡ ቡሄ ሊቃውንት እንደሚተርኩት፣ ጌታ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ለደቀ መዛሙርቱ በገለጠ ጊዜ በተራራው ዙሪያ ብርሃን ሆኗል፡፡ ስለዚህ በተራራው ዙሪያ የነበሩ እረኞች ጊዜው አልመሸም መስሏቸው እስከ ጨለማ ከብቶቻችውን ሲያበሉ ቆይተዋል፡፡

አባቶቻቸውም “ልጆቻችን ምን ኾኑ ወይስ ምን አግኝቷቸው ይኾን?” ብለው መብራት አብርተው፣ ዳቦ ይዘውላቸው ቢኼዱም ከብቶቻውን እያበሉ፣ ዢራፍ እያጮሁ ሲጫወቱ አገኟቸው፡፡ “ምነው እንዲህ እስቲጨልም ቆያችሁ?” ብለው ቢጠይቋቸው “በሔ” አሉ፡፡ በሔ ማለትም አምላክ ማለት ነው፡፡

ዛሬም ልጆች ይህን ቃል ለቃል አያያዝ የመጣውን ልማድ ይዘው፣ ትልልቆቹ “ቡሄ ቡሄ” እያሉ ከመንደር መንደር እየዞሩ ዳቦ ይቀበላሉ፡፡ በቀድሞ ዘመን በዚሁ ቀን በዥራፍ የመጋረፍ ጨዋታ እንደነበርም አባቶች ይናገራሉ፡፡ በሰሜን ሸዋ፣ በትግራይ፣ በጎንደር እና ጎጃም በመሳሰሉ የበዓሉ አክባሪዎች ቡሄ የተለየዩ ዜማዎችና ግጥሞች አሉት፡፡

ከእነዚህም ውስጥ፡- “ቡሄና ቡሄ በሉ

ቡሄ በሉ ልጆች ሁሉ

አጨብጭቡ ዝም አትበሉ”  ይላሉ፡፡

በደቡብ ጎንደር በቡሄ ሰሞን፣ ፀጉሩን የሚላጭ ልጅ ካለ ፀጉሩን የሚታጠበው በውሃ ሳይኾን በአጓት ነው፡፡ ምክንያቱም በውሃ ታጥቦ ከተላጨ መላጣ ኾኖ ይቀራል ስለሚታመን ነው፡፡ ስለዚህ የደቡብ ጎንደር ልጆች፡-

“ቡሄ መጣ ያ መላጣ

ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ” እያሉ ይጨፍራሉ፡፡  በሥነ ቃልም “ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት፣ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” ይባላል፡፡ ክረምቱ እየቀለለ ስለሚኼድ፣ ፀሐይ ስለምትገልጥ ነው፡፡ በቤተክርስቲያን አቆጣጠር ግን ክረምት የሚያበቃው መስከረም ፳፭ ላይ ነው፡፡ ዶሮ ከጮኸ በኋላም ቢኾን ሌሊት አለ፡፡ ከእነአባባሉ፡-

“ቡሄ ካለፈ አለ ክረምት

እነ እኝኝ ብላ እነቋግሚት

ዶሮም ከጮኸ አለ ሌሊት

እነቁርቁሪት እነ ድንግዝግዚት” እንዲል፡፡ በአዲስ አበባ የደብረ ታቦር በዓል ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ በየዓመቱ በልዩ ዝግጅት የሚከበረው በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም  ብቻ መኾኑን ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ?

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com