የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ

Views: 444

ከእጓለ : ገብረ : ዮሐንስ (ዶ/ር)

በአገራችን ዘመናዊ ትምህርት ከተተከለ በኋላ፣ የዘመናዊ ትምህርት ፍልስፍና እና ፋይዳው፣ የመጣበት መንገድ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታው እንዲሁም ባጠቃላይ ስለ ትምህርት ምንነት እና ጠቀሜታ ብዙ ተብሏል፤ እየተባለም ነው:: ታዲያ፣ ከነዚህ ምሁራዊ ጥረቶች አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዩኒቨርስቲ ሲመሠረት እጓለ ገብረ ዮሐንስ በሬዲዮ ያስተላለፉት መልዕክት ነው:: ያኔ በሬዲዮ የተላለፈውን መልዕክት ነው ከዓመታት በኋላ በመጽሐፍ መልክ ታትሞ፣ ዛሬ ለምጥን ዳሰሣዬ የመረጥኩት:: ተከተሉኝ ታተርፋላችሁ!!!

         “The Proper study of Mankind is Man”

                               Alexander Pop

የትምህርት ፍልስፍና በሚለው ክፍል ውስጥ እጓለ ስለ ትምህርት ይህን ይላሉ “ሰው ትክክለኛውን ትምህርት ያገኘ እንደሆነ፣ ለስላሳና (ኖብል) እግዜርን የሚመስል ፍጥረት ነው:: ትምህርት ያላገኘ እንደሆነ ግን፣ በምድር ላይ ካሉት አራዊት ሁሉ የባሰ ነው::” ይህ ቀጥተኛ የሆነ ገለጻ ጉዳዩን በበለጠ ቁምነገር ዕንድናየው የሚያስገድደን ኃያል ገለጻ ነው::

እነዚህን እና በቀጣይ የምናያቸውን ገለጻዎች እንዲሁም ፍልስፍናዊ ኃሳቦች ደራሲው ከተለያዩ አሳብያን እና ከንባብ ልምዳቸው እንዳገኙት በግልጽነት ይነግሩናል:: በወጣትነታቸው በአቴና (ግሪክ) እና በጀርመን አገር ተማሪ ሳሉ ከዘመን አቻዎቻቸቸው ጋር ባደረጓቸው ክርክሮችና ውይይቶች ዕውቀታቸውን እንዳዳበሩ ብሎም ለዚህ ውለታቸው ጓደኞቻቸው መመስገን ሲያንሳቸው እንደሆነ ይነግሩናል::

             “እውነት የራሷም የውሸትም ማስረጃ ነች”

ስፒኖዛ

    “አንድ ሠው ለራሱ የማይመስለውን ነገር ለማፍረስ ብቻ ይሰለፋል:: ሌላው ደግሞ ማፍረስን ለሌላው ትቶ በገዛ ኃሳቡ መሠረት አዲስ ለመገንባት ብቻ ያስባል:: … ባሮጌ ቤት የሚኖረውን ሰው ተጠግቶ ቤትህ የማይረባ ነው ማለት አይገባም:: ከበረቱ አጠገቡ አዲስ ቤት መሥራት ነው:: ይህ አዲስ ቤት ስለራሱም አዲስነት ስለ ሌላውም አሮጌነት ብቻውን ይናገራል::” እውነተኛዋ እውቀት፣ የምታንጸው እውቀት ለራሷም ለማይረቡትም ምሥክር ሆና እንደምትቀርብ ሊነግሩን ይህን ምሣሌ ያስቀመጡ ይመስላሉ እጓለ::

የትምህርት ፍልስፍና

    ፍልስፍና ሲባል ሠፊ ነገር ነው:: በምሣሌ ለመናገር ሁለት ቅርንጫፎች ያሉት ዛፍ ይመስላል:: አንደኛው በሩቅና በቅርብ የሚገኘው የሥነ ፍጥረት ዓለም ነው:: ሁለተኛው ከሰው መንፈስ የተገኘው የታሪክ ወይም የሥልጣኔ ዓለም ነው:: ሁለቱም ዓለማት የሚገናኙበት አንድ ቦታ አላቸው:: ሰው ይባላል:: ሰው በሁለት ዓለማት መካከል የሚገኝ ዐማካይ ፍጥረት ነው:: በዐካሉ የጉልህ ዓለም ተካፋይ ነው:: በመንፈሱ የረቀቁ የዘላቂው ዓለም ተሳታፊ ነው:: በሥነ ፍጥረት ላይ የሚጸናው የግዴታ ሕግ በእሱም ላይ ይጸናል:: በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚጸናው የነጻት ሕግ በሱም ላይ ይጸናል:: ስለ ሁለቱም ዓለማት አግባብ አለው:: ስለዚህ የምርመራውን አቅጣጫ ወደ ሁለቱም ይመራል:: የፍልስፍና መንፈስ እነዚህን ሁለት ነገሮች መርምሮ ስለመላው ዓለምና ስለ ሰው ሕይወት ትክክለኛና በሕገ ምክንያት የተመሠረተ ዐስተያት ለማቅረብ ይጣጣራል ::

ፍልስፍናን ከላይ በተመለከትነው መልኩ ከተነተኑት በኋላ፣ ስለትምህርት ፍልስፍና ደግሞ “ስለትምህርት የሚናገር ሰው ሁሉ ሦስት ጥያቄዎቹን ለመመለስ አስቀድሞ መዘጋጀት አለበት :-

  • ትምህርት ሲባል ምንድን ነው?
  • ትምህርት ለምን ዓላማ መዋል ይገባዋል?
  • ትምህርት እንዴት ባለ ዘዴ ሊሠጥ ይገባል?

“ትምህርት ምንግዜም በየትም አገር ቢሆን ከዘመንና
ከቦታ ጋር የተያያዘ ነው ::”

ትምህርትን ለመረዳት የምንጠቀማቸውን ዘይቤዎችና በተለያየ ዘመን ሠዎች ያዳበሯቸውን እውቀቶች እየጠቀሱ ካሳዩን በኋላ ስለህሊና እና መንፈሳችን የሚሉን አላቸው:-

“ሕሊናችን ወይንም መንፈሳችን የሚሠራው እንደ ግድግዳ ሠዐት እንጥልጥል ካንዱ አኃዝ ወደ ተቃራኒው በመመለስ ነው:: በሁለቱ ተቃራኒነት ሕሊና የነገሩን ጠባይም ስለሚረዳ ከሦስተኛው ቦታ ይደርሳል:: እዚህ ዘንድ ተቃራኒነታቸው ቀርቶ ተጻማሪ ይሆናሉ:: እኒህ ሦስት የሕሊና ተግባሮች በፈረንጅ ቋንቋ ሦስት ሥሞች አሉዋቸው:: thesis (አንብሮ)፣ antithesis (ተቃርኖ)፣ synthesis (አስተጻምሮ)

         “ሠው ማለት ህሊና ያለው እንሥሣ ነው”

ስለ እውቀት፣ ፍልስፍና፣ መንፈስን እና ህሊና ካወሩን በኋላ፣ ሰው ህሊና ያለው እንስሳ መሆኑን የግሪክን ፈላስፎች ጠቅሰው ይነግሩናል:: እስኪ እንከተላቸው :-

“ሰውን ከሌላው ፍጥረት ከፍ ያደረገውና ከመለኮት ባህርይ ተካፋይነት ያደረሰው፣ ዕውቀቱ- አዕምሮው- ሕሊናው ነው:: ልቦና ደግሞ የምኞት የተምኔት ፍላጎት መደብር እንደ መሆኑ ክፋትና ተንኮል የተመላውን በዙሪያችን ያለውን ዓለም በመካድ፤ ጨርሶ በመዘንጋት፣ ደጉን መልካሙን፣ ሠናይ የሆነውን የፍላጎት መሠረት በማድረግ ሠላምና ኅብር ያለው አዲስ ዓለም በውስጡ ፈጥሮ በደስታ ይኖራል:: ለመኖር ይመኛል:: የሕሊና ርቀት ሳይንስን አስገኝቶአል:: የልቡና ንጹህነት የበጎ ምግባርን የሞራል ከፍተኛነት አስገኝቶአል::

የመጽሐፉ የመጀመሪያ ቅርጽ ንግግር ነውና ብዙ ኃሳቦችን ከእጓለ ንግግር እየጠቀስን እንቀጥላለን::

የሥልጣኔ ዘይቤ

    “ለአውሮፓውያን ቋንቋዎች አንድ ቃል ከዐማርኛችን ልናውሳቸው ብንችል፣ ‹ሥላጣኔ› የሚባለው ቃል መሆን አለበት:: በጣም የተዋጣለት ቃል ነው::

… “ካልቸር” የነፍስ የመንፈስ ወይም ውስጣዊ ሥላጣኔ ብለውታል:: ሁለተኛውን (ሲቪላይዝሽን ) አካላዊ ወይም አፋዊ ሥልጣኔ ብለውታል:: ሁለቱን በሚያመዛዝኑበት ግዜ ደግሞ የበለጠውን፤ ከፍተኛውን ዋጋ ለመጀመሪያው ማለት ለነፍስ መንፈሳዊ ሥልጣኔ ሲሰጡ ይገኛሉ:: ይህ ትክክለኛ ዐስተያየት መስሎ ይታየኛል:: የሥልጣኔ ነፍስ፤ (ዋናው ነገር) የሥልጣኔ ነፍስ ነው::

… “በዚህ ኃሳብ መሠረት፣ ሰው የሚመኘው የሚመርጠውም በገዛ ራሱና በዙሪያው ባሉት ነገሮች ላይ ሁሉ ሥልጣን እንዲኖረው ነው::”

ሥልጣኔን እና እውቀትን እየተነተኑ ይቀጥላሉ እጓለ፤ በእውቀት መደርጀት፣ ዘመንን በዘመነኛ አዲስ ኃሳብ መዋጀት፣ ተፈጥሮንና ሕይወትን በጠቃሚ እውቀት ኃይል አጋዥነት አስገዝቶ ኑሮን በተሻለ መኖር ለክቡሩ የሠው ልጅ የተሠጠ ጸጋ መሆኑን በንግግራቸው አጽንዖት ሠጥተው ይመክራሉ:: እኛ ኢትዮጵያውያንም ሆነ የዘመኑት አውሮፓውያንን ኃሳብ እና የኑሮ ቅጣቸውን እየፈተሹ ወደ ተሻለው መንገድ እንዴት መግባት እንዳለብን አማራጮችን ይዘረዝራሉ:: ብዙዎቹ እሳቤዎች እንኳ ያኔ ዛሬም በሠፊው የማይነሱ እና ብዙም ያላዳበርናቸው እንደሁኑ መታዘብ እንደ ተቆርቋሪ ዜጋ ያማል:: ዩኒቨርስቲ በከፈትንበት ዓመት በዚህ ደረጃ የበሠለ እና የደረጀ፤ ዘመናትን ተሻግሮ ማየት የሚችል ሊቅ የነበራት አገር ዛሬ ምሁሮቿ ያሉበትን ዐይቶ የተማረውንም ኃይል ትምህርትንም አለመፈተሸ አይቻልም::

         “ሰው ከእምነቱ ከእውቀቱ በስተቀር ምንም ነው”

እንደ ማጠቃለያ

               “በተዋኅዶ ከበረ::”

እጓለ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) በዚህ አስደናቂ ንግግራቸው፣ ተዝቀው የማያልቁ እውቀቶችን ለታዳሚዎቻቸው አድርሰዋል:: እንኳን በንግግር ብቻ ተደምጦ ይቅርና ተነቦም ቢሆን በአንድ ግዜ ብቻ የሚተው ሥራ አይደለም:: ከሼልፍ ላይ በየግዜው እያነሱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለመወያያነትም ሆነ ኃሰብ ለመዋስ ዓይነተኛ መጽሐፍ ነው:: የሠውየውን ጥልቅ የንባብ ሕይወት እና ብሩህ አዕምሮ ውጤት ነው- ይህ መጽሐፍ::

የኢትዮጵያን እውቀት፤ የያሬድን ዜማ እና ቅኔ ምንነት እና ጥልቀት፣ የምዕራባውያንን የሥልጣኔ መንፈስ እና የህዳሴ ጉዞ እንዲሁም ታላላቅ ፈላስፎቻቸው ያነሱትን ኃሳብ አውጥተው አውርደው እንዲሁም ተንትነው ሲያበቁ በተዋኅዶ ስለመክበር ባነሱበት ምዕራፍ ይህን ጠቅላይ ኃሳብ ያነሳሉ:-

“በዘመናችን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምሁር ፊት የተደቀነው
ሥራ ይህ ይመስለኛል:: ሁለቱን ሥልጣኔዎች የኢትዮጵያንና
የአውሮፓን በገዛ መንፈሳቸን ድልድይነት ማገናኘት፤ በጥረታችን
ግለትና ሙቀት እንዲዋኃዱ ለፍሬም እንዲበቁ ማድረስ ::”

ከ ሥድስት አሥርታት በኋላም እጓለ ምኞታቸው የሠመረ አይመስልም:: ኢትዮጵያንም የማያውቅ አውሮፓንም የማይመጥን የትምህርት ሥርዓት እና የተማረ የሠው ኃይል ነው አገሪቷን የወረራት:: የራሱን ጥሎ የሰው ለማንጠልጠል ሲለፋ፣ ባተሌ ሆኖ የቀረው ትውልድ፣ ከትላንት ያልተማረው የዛሬው የተማረ የሠው ኃይል አዋህዶ ያከብራል የሚል አደራን ተቀብሎ አለያይቶ ተዋርዶ አዋርዷል:: እንደተለመደው አዋቂዎችን የማይሰማ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆነ ሥርዓት አሁንም ዐየሩን እንደሞላው ነው:: የትምህርት ሥርዓታችን እና የትምህርት ጥራት ከነበረበት መጥፎ ደረጃ አሁን ተባብሶ በጣም መጥፎ ሆኗል:: በእጓለ ምርጥ ንግግር የተከፈተው ዩኒቨርስቲ፣ ዛሬ በኃሳብ ድኩማኖች እና በዐንደበተ ጎልዳፎች ባይዘጋም ገርበብ ብሏል- የዕውቀት በሩ::

እጓለ ገብረ ዮሐንስን ለማዳመጥ እና የተሻለ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት መነሻ ለማድረግ ሲያንሳቸው እንጂ አይበዛባቸውም:: ፈረንጆች እንደሚሉት “ወደ ፊት መሄድ ካልቻልክ ወደ ኋላ ተመለስ” ነው ነገሩ:: ወደፊት ለመሄድ የሚረዳንን ኋላችንን ለማስታወስ ነው ይህን ጽሑፍ መጻፍም ያስፈለገው::

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com