መንፈሣዊው ጦርነት! “የማዕከለ ሰብዕ ትንሣዔ በኤረር ተራራ ድምጾች” በጤንነት ሠጠኝ

Views: 406

የዛሬው የመጽሐፍ ጥቆማዊ-ዳሠሣችን ከቀደሙት መጽሐፍት በተለየ ይዘት ዓለማቀፋዊውን እና አገራቀፉን ፖለቲካዊም ሆነ ዓለማዊ ኩነት በመንፈሣዊ መነጽር ስለመመርመር ይሆናል::

“በኤረር ተራራ ድምጾች” የተሠኘው መጽሐፍ በደራሲ ጤንነት ሠጠኝ (ወ/ሩፋዔል) የተጻፈ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ደራሲው የተለያዩ መጽሐፍትን አሳትሟል፤ ከእነዚህ መጽሐፍት መካከል በ2004 ዓ.ም ያሳተመው “ምሥጢረ ሠማያትና ምሥጢረ ኢትዮጵያ ፍልስፍና” ተጠቃሽ ነው፡፡

ማዕከለ ሰብዕ እየተባሉ የተጠቀሱት ህዝቦች በሠው ልጆች ታሪክ ውስጥ በከፍተኛ የኃሳብ ልዕልና ሥር የኖሩ ህዝቦችን የሚመለከት ነው:: የእነዚህ ህዝቦች አስተሳሰብ በየደረጃው ሁሉንም የሠው ልጆች ኃሳብ ዐቅፎ መያዝ የሚያስችል የክብር ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው:: ይህም በጥቅሉ ለሠው ልጆች ሁሉ ድልና ነጻነትን የሚሠጥ ነው::”

    “የማዕከለ ሰብዕ ርስት ሀገር፤ በታላቅ የኃሳብ ልዕልና ሲኖሩ የነበሩ ህዝቦች ይገኙበት የነበረበትን መልክዐ-ምድር የሚመለከት ነው :: የማዕከለ ሰብዕ ርስት ሀገር ህዝች ፤ በአሁኑ ወቅት በነዚህ ሥፍራዎች ላይ የሚኖሩትን ህዝቦች የሚመለከት ነው:: የማዕከለ ሰብዕ ልዕለ ኃያል የሆነው ኃሳብ ያልተገለጠላቸው ነገር ግን በርስት ሀገሩ ውስጥ በሌሎች መንፈሳዊ ኃሳቦች እየኖሩ ያሉትን ህዝቦች የሚመለከት ነው::”

    “የማዕከለ ሰብዕ ወገኖች፤ አንድም በገጸ ነፍሳቸው በኩል የማዕከለ ሰብእ ወገን የሆኑትን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ልዕለ ኃያል በሆነው በማዕከለ ሰብዕ ሀሳብ የሚኖሩትን ህዝቦች የሚናገር ነው::”

ደራሲው ጤንነት ሠጠኝ፣ እነዚህን ኃሳቦች ከፈታ እና ካፍታታ በኋላ የራሱን የሕይወት ጉዞ እየተረከ ወደ ዋናው መንፈሳዊ መገለጥ እና ስለተገለጡለት ነገሮች እየተነተነ ከምዕራፍ ምዕራፍ ይቀጥላል::

ደራሲው በወጣትነታቸው ወቅት ተሳትፎ ካደረጉበት የፖለቲካ ፓርቲ ጋር በተያያዘ፣ በመንግሥት ወታደሮች ከነ ጓዶቻቸው መታደን ውስጥ ይወድቃሉ:: ከዚህ አደን ለማምለጥ ከጓዶቻቸው ጋር ወደ ኤረር ተራራ ጫካ ገብው ይደበቃሉ፡፡ ከዋና ከተማው ባይርቁም፣ በአካባቢው ደን-ነት የተነሳ ሠላማቸውን ያገኛሉ፤ እዚህ ጫካ ውስጥ ሆነው የፖለቲካ እንቅሳቃሴና መሥመራቸውን የመገምገሚያ ዕድል ያገኙት ወጣቶች፣ ጫካ ውስጥ ሆነው ሲፋጩ ከርመዋል:: በዚህ ቆይታቸው ነበር የበቁ እና ሥውራን ስለሆኑ ዐባቶች መሥማት የጀመሩት፤ በጉዳዩም የተሳቡት::

ደራሲው ጤንነት ሠጠኝ የክርስትና ሥሜ ነው ባለን ወ/ሩፋዔል አማካኝነት መንፈሳዊውን ዓለም ይመረምራል፤ ከወልደ ሩፋዔል ጋር ይወያያል:: የመጽሐፉም ብዙው ክፍል ይህ በጤንነት እና በወልደ ሩፋዔል መካከል የሚደረግ ውይይት ነው:: ስለ ኤረር ወልደሩፋዔል ይኼን ይላል:-

“የኤረር ተራራ በምሥራቅ አቅጣጫ በአሁኑ መጠሪያው ‹‹ቱሉ ፈራ›› የሚባለው ተራራ ያዋስነዋል:: በሠሜን ደግሞ የእንጦጦ ተራሮች ያዋስኑታል:: በምዕራብ ፉሪ ተራራ ያዋስነዋል:: በደቡብ የዝቋላ ተራራ ያዋስነዋል:: በዛን ጊዜ ላይ ወደ ሥውሩ ዓለም የሚገባው ንጉሥ እና እሡን የሚተካው ንጉሥ ሠራዊቶቻቸውን ይዘው ቱሉ ፈራ ተራራ ላይ ይገናኛሉ::

ሁለቱም አስከትለዋቸው የመጡትን ሠራዊቶቻቸውን እዛው ሥፍራው ላይ ትተው፣ የመጀመሪያው ንጉሥና ተተኪው ንጉሥ ብቻውን ወደዚህ ሥፍራ ይመጣሉ:: እዚህ ሥፍራ ከመድረሳቸው በፊት የዚህ ሥፍራ የመጀመሪያ ክፍል ከሆነው የማዕከለ ሰብዕ ካህን መልከጸዴቅ ዋሻ ቤተመቅደስ ሲደርሱ ከእሱ ዘንድ ገብተው የሚገባውን ሥርዓት ይቀበላሉ::” (ገጽ 10)

ወልደ ሩፋዕል ለጤንነት ይህን መሠል የምሥጢራዊውን ዓለም ሥርዓት እና መሠል ክንውኖች ይዘረዝርለታል:: በዚህ መልኩ ምድራዊ ንግሥናቸውን ጨርሰው ወደ ምሥጢራዊው ዓለም ከገቡ ኢትዮጵያዊ ነገሥታት አንዱ ላሊበላ እንደሆነም ወልደ ሩፋዔል ጠቅሶለታል::

ጤንነት እና አራቱ ኤረር ተራራ ላይ ለመቆየት የወሰኑት ጓደኞቹ የበቁትን ዐባቶች መገናኘት ከጀመሩ በኋላ፣ ስለ አገራቸው ተወያይተዋል:: ጤንነት እና ጓደኞቹ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም እና መንግሥትን በመለወጥ እንደሆነ ሲከራከሩ የበቁት ዐባቶች በበኩላቸው የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው “በርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰቦች ሳይሆን፣ በመንፈሳዊ ክፍል ውስጥ በሚካሄድ ትግል እንደሚፈታ አስረዱን” ይላል ወልደሩፋዔል:: ኃሳቡን ሲያፍታታም :-

“…እንደ ነገደ ማዕከለ ሰብዕ አስተሳሰብ መሠረት፣ የሰው ልጅ ባሕል ወይም አኗኗር የተገነባው በ ሰባቱ (7ቱ) የጥበብ ዐምዶች ነው:: እነዚህም የጥበብ ዐምዶች ሰው በየደረጃው የሚገኝባቸውን የመገለጥ ደረጃዎች የሚናገሩ ናቸው:: ወይም ሰው በየደረጃው ነገሮችን የሚመለከትበትን ወይም የሚረዳበትን የኃሳብ ዕይታ የሚያስረዳ ነው:: እነዚህ ከትንሽ የክብር ደረጃ ካለው እስከ ከፍተኛው የክብር ደረጃ ላይ እስካለው እንመልከታቸው ካልን፡ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ሀገር፣ ኃይማኖት፣ መንፈስና ጥበብ ናቸው::”

ሥውሩን እና የተገለጠውን ዓለም፣ ዓለማዊውንና መንፈሣዊውን ህይወት እንዲሁም ምሥጢረ ህላዌን ጤንነት በሌላኛው ማንነቱ ወልደ ሩፋዔል ዐማካኝነት እየተነተና እና እያስተነተነ ይቀጥላል:: ለብዙዎቻችን ዕንግዳ የሆኑ ኃሳቦችን፣ ምናልባትም ለማመን የሚቸግሩንን ጉዳዮች ደራሲው በእርግጠኝነት ያነሱልናል::

ማመን አለማመን እንዳለ ሆኖ ግን፣ የተነሱትን ኃሳቦች እና የሚነገሩትን ታሪኮች አንብቦ አለመገረም እና በአዕምሮ ጥያቄዎችን አለማንሳት አይቻልም:: ወዲህ ደሞ ትንታኔዎቹም ሆኑ ታሪኮች አገራዊ ዕውቀት እና መገለጥ ናቸውና በሡም አለመደሰት አይቻልም:: ለየት ካሉት እና በመጽሐፉ ከተካተቱት ኃሳቦች አንዱን ልጥቀስና ጥቆማዊ ዳሰሳዬን ላብቃ:-

“በሰማያተ ሰማያት ከምናገኛቸው ፍጥረታት ትልቁን ሥፍራ የሚይዙትና በታላቅ ክብር ደረጃ የሚገኙት ጊዜ፣ ግዝፈትና ኃይል ናቸው:: ጊዜ በሰማያተ ሰማያት አንድ ገጽ ሲኖረው፣ በምድራዊ ሰማያት ሦስት ገጽ በሥውሩ ምድራዊ ሰማያት ደግሞ አንድ ገጽ አለው:: ግዝፈት በሰማየ ሰማያት አራት ገጽ በምድራዊ ሰማያት አራት ገጽ በሥውሩ ምድራዊ ሰማያት እንዲሁ አራት ገጽ አለው:: በዚህ መሠረት በግዝፈት ሥር ከሚነሱት እሳቤዎች ውስጥ አቅጣጫ፣ አምሳልና መመዝገብ ዋናዎቹ ናቸው :: ወይም ግዝፈት አቅጣጫን ይመለከታል::

አንድ ፍጥረት ግዝፈት አገኘ ስንል ወይም ህልው ሆነ ስንል በአራት አቅጣጫ ተቀመጠ ማለት ነው:: በሌላ በኩል ይህ ዓለም ከትንሹ ጀምሮ እስከ ትልቁ ድረስ እራሱን በተመሳሳይ ሥርዓት ውስጥ እየደገመ የሚያመጣ እንደመሆኑ ይህ የመድገም ሂደት አምሣል ይሰኛል:: አንደኛው የአንደኛው አምሣል ነው እንደማለት ነው::

… ሆኖም ግን፣ እኛ በዚህ ምድራዊ ሰማያት ላይ እነዚህን ፍጥረታት የምናያቸው በሁለት ገጽ ብቻ ነው:: ወይም በምድራዊ ሰማያት ላይ የሚገኙ ፍጥረታት ግዝፈታዊ አካላቸው የሚታየው በሁለት ገጽ ብቻ ያለው ነው:: በስውሩ ምድራዊ ሰማያት ግን ፍጥረታት በአራቱም ገጽታቸው ይታያሉ:: ይህም በመሆኑ፣ በምድራዊ ሰማያት ከምናያቸው በተሻለ በስውሩ ምድራዊ ሰማያት ያለው ግዝፈታቸው ውበት አለው ::”

“የማዕከለ ሰብዕ ትንሣዔ በኤረር ተራራ ድምጾች ” ከረቂቁ እስከ ግዙፉ፣ ከድብቁ እስከ ግልጹ እንዲሁም ከመንፈሳዊው እሰከ ዓለማዊው ሕይወት የተዘረጋውን ህልውና ብዙም ባልለመድነው የምልከታ አንጻር ያስቃኘናል::

አገር በቀል በሆነ ኃሳብ፣ አገርንም ሆነ ዓለምን መተንተን መታደል ነው:: ይህ ዕውቀት እና መገለጥ ከዛም አልፎ ብዙ የህልውና ጥያቄዎችን መዳሰሱ ደግሞ የበለጠ ያኮራል:: ከማመን እና ካለማመን በላይ ሆነን ኃሳቡን ብናውጠነጥነው መዳረሻችን እንደ የግላችን ይለያይ ይሆናል::

አገርን አክሞ ለማዳን አይደለም የራሳችንን እና የባዕዳንንም ኃሳብ እንዋሳለን፤ እና ለእንዲህ ዓይነት የተለዩ ኃሳቦች ዐይንንም ጆሮንም መስጠት አክሳሪ አይደለም ማለት ተገቢ ይመስለኛል:: እንደ አድቬንቸር የሥነ-ጽሑፍ ዘውግ ራሡ ማንበቡ የተለየ ሥሜትን የሚያጎናጽፍ ሆኖ አግኝቸዋለሁ:: መልካም ንባብ!!!

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com