ሦስት ሰዎች በጎርፍ አደጋ ህይወታቸውን አጡ

Views: 128

በዐማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ሊቡ ከምከም ወረዳ የርብ ወንዝና ገባሮቹ በመሙላታቸው የሦስት ሰዎችን ህይወት ያጠፋ ሲሆን የንብረትና የእርሻ ሰብሎችም ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተባለ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ በሊቦከምከምና በፎገራ ወረዳዎች የሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች በውሀ በመጥለቅለቃቸው የአካባቢው ኅብረተሰብ የሚበላው አጥቷል ማለታቸውን የጀርመን ራዲዮ ዘግቦታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሦስት ጀልባዎች የአካባቢውን ነዋሪዎች ከሥፍራው እያነሱ ቢሆንም፣ ባጋጠማቸው የነዳጅ እጥረት የማዳን ተልዕኮአቸውን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን እንዳልቻሉም ተጠቁሟል፡፡

የርብ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት ተጠባባቂ ተጠሪ የሆኑት ኢንጅነር አሸብር ቶንጃ ለዐማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት እንዳሉት በላይኛው የግድቡ ተፋሰስ ከፍተኛ ዝናብ በመጣሉ ትላንት ነሐሴ 6 ምሽት 4፡00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ግድቡ ሞልቷል፡፡

ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሀ በግድቡ ማስተንፈሻዎች በኩል መውጣት ጀምሯል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኢንጅነሩ፣ ከዚህ ቀደም ከግድቡ ማስተንፈሻ በኩል ውሀ ሊለቀቀ እንደሚችል አስጠንቅቀው የነበሩ ሲሆን፣ አሁንም በታችኛው የርብ ተፋሰስ የሚገኙ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com