ዜና

እሬት ለጤና በረከት

Views: 8880

መግቢያ፡-

የእሬት ተክል ሲበዛ መድኃኒትነት እንዳለው ተደጋግሞ የተወሳ ነው፡፡ በዚሁ ኢትዮ ኦንላይን የመረጃ መረብ ላይ ለፀጉር እና ለሰውነት ቆዳ እንክብካቤ ስለ አዘገጃጀቱ እና አጠቃቀሙ ቀርቧል፡፡ እዚያው ላይ ማንበብ ስለሚቻል በዚህ ርዕስ ላይ በድጋሚ ማብራራት አይጠበቅም፡፡ ማጣቀሻ አንድ

ሀ.  የእሬት ተክል ዋና ዋና ጥቅሞች

 • ለማንኛውም የቆዳ ህመም፣ ቁስል፣ የእሳት ቃጠሎ፣ የፀሐይ ንዳድ፣ ፈንገስ፣ ቋቁቻ፣ ፓሶሪያሲስ እና ለመሳሰሉት ፍቱን ነው፤
 • ለእራስ ቆዳ ጤና እና ለፀጉር እድገት ድንቅ ነው፤
 • የኢትዮጵያ የባሕል ሐኪሞች በብዙ ሁኔታ ለመድኃኒት ይገለገሉበታል፤
 • በዓለም ላይ ለብዙ የውበት መጠበቂያ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃነት በመቅረቡ የፀጉር ሻምፖ፣ ሎሽን፣ ክሬም፣ ጄል፣ ቅባት፣ ሳሙና ወዘተ ይመረትበታል፤
 • በዓለም ላይ የመድኃኒት ፋብሪካዎች በከፍተኛ ሁኔታ ለጥሬ እቃነት ይጠቀማሉ፤
 • በቤት ውስጥ በማዘጋጀት፣ ለስኳር ህመም፣ ለጨጓራ፣ ለአንጀት ወዘተ ይውላል፤
 • ከቤት እንስሳት ሆድ ውስጥ ጥገኛ ተውሳክ ለማስወገድ ተመራጭ ነው፤
 • ለቤት እንስሳት የቆዳ ላይ ጥገኞች፣ ለተባይ፣ ለፈንገስ እና ለመሳሰሉት ተፈላጊ ነው፤
 • ሌሎችም ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

የእሬት ተክል በሌላ የዓለም አገራት ብዙ እንክብካቤ ይደረግለታል እናም ብዙ ጥቅም ይገኝበታል፡፡ በሰፋፊ እርሻዎች ያለማሉ፡፡ በአነስተኛ መጠን ግን ብዙ የአውሮፓ እና የኤሸያ ቤተሰቦች በቤታቸው  ከሚያለሙት ዋናዎቹ ውስጥ አንዱ ነው፡፡

ለ.  በቀላሉ የማልማት ዘዴ

 1. ሰፊ ቦታ የለንም የምትሉ ሰዎች እንደዚህ ትከሉ፤
 • በርከት ያለ የውሃ ላስቲክ በአንድ በኩል ሰንጥቁ፤ እንደ በር ቆርጣችሁ አንሱለት፤
 • ከሥር ትንንሽ ቀዳዳ ይኑረው፣ ውሃ እንዳያቁር፤
 • የዳበረ አፈር ሙሉበት፤
 • ከዳር እና ከዳር ሁለት አነስ ያሉ እሬት ትከሉበት፤ ወይም
 • መሐል ላይ አንድ መካከለኛ ትከሉበት፣
 • ብትፈልጉ ለምሳሌ የአጥር ግርግዳ ላይ፣ ወይም በግቢ በሚገኝ ዛፍ ላይ አንጠልጥሉት፤
 • የተለያዩ ፕላስቲኮች ውስጥ አፈር ሞልታችሁ በዚሁ ዘዴ ትከሉ፤
 • እሬቱ እድገቱን ሲጨምር ቦታ እና እቃውን ቀይሩለት፣

(በፕላስቲክ ውስጥ የተተከሉ እና የአጥር ግርግዳ ላይ  የተንጠለጠሉ የእሬት ተክሎች)

 1. በጓሮ ቦታ ያላችሁ እንደዚህ ትከሉት
 • እንደ ተክሉ መጠን በመስመር በእያንዳንዱ መሐል ከ2ዐ እስከ 4ዐ ሳንቲ ሜትር አራርቁ፤
 • ከሌሎች ተክሎች ለይታችሁ በአንድ ተርታ ትከሉት፤ ወይም
 • በቂ ቦታ ካለ ሁለትም ሦስትም መስመር የምትፈልጉትን መጠን ትከሉ፣
 1. ሰፊ ማሳ ያላችሁ በስፋት አልሙት
 • ከፍ ባለ መጠን ለማምረት የፈለጋችሁ፣ በእርሻ ባለሙያ ማሠራት እና ለገበያ ማቅረብ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን የሚገዛው ወገን ምን ዓይነት ዝርያ፣ በምን መጠን እንደሚፈልግ  ማስጠናት ያስፈልጋል፡፡

ሐ. እሬት ከየት ይገኛል

 • በመግዛት ይገኛል፣ ችግኝ አሳድገው ከሚሸጡት ዘንድ በግዢ ታገኛላችሁ፡፡ በዚህ በክረምት ወራት ከዱር እየነቀሉ ወደ ከተማ አምጥተው የሚሸጡም አሉላችሁ፡፡
 • ከሌሎች ጠይቁ፣  ቀድመው ተክለው ካላቸው ዘንድ ከሥር በኩል በጎን ላይ ትንንሽ ብቃዮችን ለይቶ መውሰድ፣
 • ከዱር ወይም ከመስክ ፈልጉ፣ ካለበት አካባቢ ከዱር ሄዶ ነቅሎ ወደ ቤት ማምጣት፡፡
 • ከሩቅ ቦታ አስመጡ፤ እሬት በብዛት ከሚገኝበት አካባቢ በሰው ማስመጣት፡፡

ከታች በሰንጠረዥ ላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ እና ከሌሎችም ቦታ ማስመጣት አንድ ዘዴ ነው፡፡

መ. ለእሬት እንክብካቤ አርጉ

 • በየጊዜው በቂ ውሃ ማጠጣት አለባችሁ፣
 • በጣም ሰፊ ቅጠል ሲያወጡ በአግባቡ ቅጠሉን እያቆረጣችሁ ተጠቀሙ፣
 • ከሥር ሌላ ብቃይ ሲያወጣ ለይታችሁ ትከሉት፣
 • የሙዝ ልጣጭ እየፈጫችሁ፣ በውሃ በጥብጡት፣ ግሩም ማዳበሪያ ይሆናል፣
 • ለ2 ሰዓት ያህል አቆዩትና በእሬቱ ተክል በዙሪያው ጨምሩ፣ ወደ ውስጥ እንዲገባ ኮትኩቱ፤
 • በየሁለት ሳምንቱ ብትጨምሩ ጥሩ ነው፡፡

የሙዝ ልጣጭ በዚህ ዓይነት ለብዙ ተክሎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ እባካችሁ ሙዝ  አከፋፋዮችን፣ ሙዝ የሚሸጡትን አበረታቱ፤ ማዳበሪያ ይሆናል ብለው መልሰው እንዲሸጡት ምከሩ፡፡ የትም በስብሶ ከሚቀር ተመልሶ ጥቅም ላይ ቢውል መልካም ነው፡፡

ሠ. የእሬት ዝርያው

የእሬት ዝርያ በእኛም አገር ሆነ በዓለም ላይ በጣም ብዙ ዓይነት ነው፡፡ በመላው ዓለም ላይ እኛ ከምናውቀው ሌላ በጣም ብዙ ዓይነት አሉ፡፡ በቀለሙ፣ በመጠኑ፣ በቅጠሉ ስፋት፣ በመድኃኒት ይዘቱ፣ በመርዛማነቱ፣ በሚበቅልበት ቦታ ወዘተ የትየለሌ ነው፡፡ አጀብ! ለማለት ከፈለጋችሁ ምስሉን በጎግል እና በተለያየ መረጃ መረብ ላይ ተመልከቱ፡፡

ልብ በሉ፣ እሬትን “አሎ ቬራ” ብለውት ሁሉንም በጅምላ የሚጠሩ አሉ፡፡ ከደብረ ብርሀን ያመጡትን የእሬት ምርት  “አሎ ቬራ” እያሉ ሲያስተዋውቁ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ይህ ሊታረም ይገባል፡፡ ሁሉም እሬት   “አሎ ቬራ” ተብሎ አይጠራም፡፡ ለምሳሌ የሚከተለውን ዝርዝር ስሞች አጢኑ፡፡

ይህ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት በጣም ጥቂቶቹን እንኳን ለማስረዳት ያህል ነው፡፡

የዕፀዋት ስያሜ የሚሰጠው በሳይንሳዊ ትንታኔ መነሻ  እና  በልዩ ገላጭ ተጨማሪ ስም ነው፡፡ ያም ስያሜ ልዩ መለያው  ወይም ልዩ ስሙ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ  ከሚገኙት የእሬት ስያሜ ጥቂቱን እንመልከት ማጣቀሻ  ሁለትና ሶስት

*(Aloe gilbertii  Reynolds ex Sebsebe & Brandham) “ሬት  ጊልበርት” ልዩ መጠሪያው ነው፡፡ በኤም፡ጂ፡ጊልበርት  (M.G Gilbert)   የተሰየመ ነው፡፡   ሪይኖልደስ ስያሜውን መጀመሪያ የሰጠ ሰው ነው፡፡ ቀጥሎም ፕሮፌሰር ሰብስቤ እና ብራንድሃም በዚህ ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳተሙ ናቸው፡፡ ጊልበርት እራሱ ታዋቂ የስነ ዕፀዋት ተመራማሪ እና ባለውለታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፍሎራ (7 ሺ የሚደርሱ የኢትዮጵያ ዕፀዋት በሙሉ ተጠንተው ተካተው የተፃፉባቸው ትልልቅ መጽሐፍት) ሲዘጋጁ  ጉልህ  ድርሻ ያበረከተ ሰው ነው፡፡

* * (Aloe pulcherrima Gilbert  & Sebsebe) ሬት ቡልቸሪማ”  ልዩ መጠሪያው ነው፡፡  ጊልበርት እና ሰብስቤ በ1997 እ፡ኤ፡አ  ይህን ሬት እንዲህ ብለው ስያሜ ሲሰጡት እሾህ አልባ እና የሚያምር በመሆኑ ነበር፡፡  (ከ21 አመት በፊት ነው፡፡)

***  (Aloe rivae  Baker)    ሬት ሪቫ፣” ይህ ልዩ ስሙ ነው፡፡ ባከር ስያሜውን የሰጠ  ወይም ያሰጠ፣ ወይም  በዚህ ስም መጀመሪያ ያሳተመ  ሰው ነው፡፡  ይህን የሬት ዓይነት ባከር በ1898 እ፡ኤ፡አ  የሰየመው ጣሊያናዊ የህክምና ዶክተር በሆነው ዶመኒኮ ሪቫ (Domenico Riva)   ነው፡፡  ዶመኒኮ ሪቫ (Domenico Riva)   በ1893 እ፡ኤ፡አ  በደቡብ ኢትዮጰያ ባደረገው አሰሳ ከሰበሰባቸው ውስጥ የተገኘ  የሬት ዓይነት ነው፡፡ (ከ 12ዐ አመት በፊት ነው፡፡)

**** (Aloe ruspoliana Baker) ሬት ሩስፖሊያና”  ጣሊያዊ ቄስ የሆነው ካውንት ኢጊንዮ ሩስፖሊ (Count Eugenio Ruspoli) በ1893 እ፡ኤ፡አ  በደቡብ ኢትዮጵያ ዘረዕፀዋት ፍለጋ (Expedition )  ባደረጉት ጉዞ ከነዶክተር ዶመኒኮ ሪቫ ጋር አብሮ የአሳሽ ቡድኑ ጉዞ መሪ ነበር፡፡ ኪዊ ላብረሪ ተፅፎ የተገኘው ማስታወሻ ሩስፖሊ  ሰጋና  ወንዝ አጠገብ ጋሙጎፋ ዞን፣ ታህሳስ 4  1893 እ፡ኤ፡አ በዝሆን እንደተገደለ ይገልፃል፡፡ ለዚህም መታሰቢያ  ብሎ ይሆናል ባከር በ1898 እ፡ኤ፡አ  እሱ (ሩስፖሊ) ቀድሞ ከሰበሰባቸው የሬት ዓይነቴዎች ውስጥ ይህን በዘመኑ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ከሆነው ሚልሚል እና ኢሚ መካከል የተገኘውን ሬት በ ሩስፖሊ የሰየመው፡፡  (ከ 12ዐ አመት በፊት ነው፡፡)

ማጠቃለያ፡-

ይህ ከላይ የተነገረው ስያሜ መጥቀስ ለምን አስፈለገ?

የህክምና ዶክተር የሆነው ዶመኒኮ ሪቫ እና ቄስ የሆነው ካውንት ኢጊንዮ ሩስፖሊ ዝሆን እስኪገለው ድረስ እሬት ፍለጋ፣ ወይም ዘረ እፀዋት ፍለጋ  ከዛሬ አንድ መቶ ሃያ (12ዐ) አመት በፊት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ምን አንከራተታቸው?  ብላችሁ አስቡ፡፡ ለምን እሬት ፈለጉ? ብላችሁ አሰላስሉ?

የእኛው እሬት ዛሬም እንደ ቀደሙ ሁሉ በዱር ውስጥ በበጋ ወራት ይደርቃል፣ ክረምት ያለመልማል፣ እንዲሁ ዘመናት አለፉ፡፡ እነሱማ አበጁ! በእነሱ እና እነሱን መሰል አሳሾች ድካም እና ትጋት አኅጉራቸው አውሮፓ በዕፀዋት ምርት የትየለሌ ሲራቀቁ ተመልከቱ፡፡ እኔ ደግሞ ገና ዛሬ ሶስት ላስቲክ ግርግዳ ላይ አንጠልጥዬ “እሬትን እንደዚህ ትከሉ” ማለቴ፤ መላ መምታት ነው? ወይስ መላ ማጣት ነው? ደጋግማችሁ ካላነበባችሁ ነገሩ በቀላሉ አይከነክንም፡፡

ነገሩ ሲገባችሁ፣ ዕልህ ስትገቡ፤ ጊቢአችሁን በእሬት ትሞሉት ይሆን!? እስቲ በዚህ ጉዳይ ተጨማሪ አንብቡ! አሰላስሉ!

                                                                                                                   

ማጣቀሻ

ማጣቀሻ አንድ፣  https://ethio-online.com/

ለጤናዎ እና ለውበትዎ! የሰውነትዎን ቆዳ በዚህ መንገድ ተንከባከቡ፤  እና ፀጉርን እንዲህ ተንከባከቡ 

ማጣቀሻ ሁለት፣  በቀለች ቶላ፣  2ዐዐ9 ዓ.ም  Glossary of Plant ‘s Name  in Scientific, Amharic and Others

የዕፀዋት መጠሪያ  በሳይንሳዊ   አማርኛ እና ሌሎችም፣ አልፋ አታሚዎች፣ አዲስ አበባ

ማጣቀሻ ሶስት  Sebsebe Demissew, Inger Nordal and Odd E.Stabbetorp, First edition 2003, FLOWERS OF ETHIOPIA AND ERITREA ALOES AND OTHER LILIES, Shama Books, Addis Ababa, Ethiopia.

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com