ሀገረሰባዊ እምነት በሰባት-ቤት ጉራጌ -፩-

Views: 265

በሰባት ቤት ጉራጌ ከክርስትና እና እስልምና ሃይማኖቶች በተጨማሪ፣ በአንዳንድ የብሄረሰቡ አባላት በተለይም የሰባት ቤት ጉራጌ ህዝብ የሚያመልኩባቸው ልማዳዊ (ባሕላዊ) እምነቶች ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ባሕላዊ እምነቶች መካከል የቸሀ ዋቅ (አወጌት)፣ የደሟሚት (የሞየት) እና የቦዠ እምነቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የቸሀ ዋቅ የጦርነት አምላክ መሆኑ፣ በተለያዩ አፈታሪኮችና ትውፊታዊ መዝሙሮች ሲተረክ፤ ደሟሚት ደግሞ የልምላሜ አምላክ እንደሆነች ይተረክላታል፡፡

የዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ጉዳይ የሆነው ቦዠ ደግሞ ቅጣቱን በመብረቅ አማካይነት የሚሰነዝር የአደራ ጠባቂና የቁጣ አምላክ እንደሆነ ይተረካል፡፡

ማኅበረሰቡ፣ እነዚህን ባሕላዊ እምነቶች፣ ከመቼ ጀምሮ እንደተቀበላቸውና ከየት እንደመጡ በትክክል የሚያረጋግጡ ጥናቶች እስከዛሬ ድረስ አልቀረቡም፡፡ ሆኖም፣ በአካባቢው የሚገኙ ትውፊታዊ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ፣ የኦሪት እምነት ተከታይ በነበሩበትና ቀጥሎም የክርስትናን ሃይማኖት ተቀብለው ወደ ጉራጌ ምድር ከመጡት የሰሜን ነገዶች ጋር የመጡ መሆናቸውን ግምታቸውን የሚገልፁ ጸሐፊዎች አሉ፡፡ (ድንበሩ፣1987፣119)

እነዚህ ክርስትናን ይዘው የመጡት የብሄረሰቡ ቀደምት አባቶች፣ በእምነታቸው ፀንተው ሲኖሩ ቆይተው፣ የአህመድ ግራኝ ወረራ ወደ ጉራጌ በዘለቀበት ወቅት፣ ክርስተያኑ ህዝብ ሃይማኖቱን መተው ጀመረ፡፡ በወረራ ምክንያትም እምነታቸው በሌሎች የአምልኮ ሥርዓቶች እየተለወጠ ሄደ፡፡ ወረራው አብቅቶ ህዝቡ መረጋጋት ሲጀምር፣ የቀድሞ የካህናት ዘሮች ራሳቸውን “አበቄ” ብለው በመሰየም በተቃጠሉት አብያተክርስቲያናትና ደብሮች የቤተክርስቲያን ቅርፅ ያላቸው በአካባቢው አጠራር “የዋቅ ዘገር” በመባል የሚታወቁትን ጎጆዎች አሰርተው፣ የአምልኮ ሥርዓታቸውን ማከናወን ጀመሩ፡፡ (ድንበሩ፣1987፣203)

በአሁኑ ወቅት፣ እየተመለከባቸው ያሉትን የባሕላዊ እምነቶች መሪዎች የየግላቸው የማዕረግ ስም አላቸው፡፡ ለምሳሌ የቸሀ ዋቅ መንፈስ ያደረባቸው የወገፐቻደማም፣ የደሟሚት ሹም የወየ ደማም፣ የቦዠ መንፈስ ያደረባቸው ደግሞ ጎይታኩየ በሚባሉት ስያሜዎች ይጠራሉ፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ የእያንዳንዱ ቤተ ጉራጌ እና ጎሳ አማልክቶች አሉ፡፡ የየአካባቢው ጎሳ ዋቆች በየአካባቢው ነዋሪ የሚከበሩና የተለያየ ሥልጣን እንዳላቸው የሚታመንባቸው ናቸው፡፡ እንዲሁም በየቤተ ጉራጌው ካሉት ዋቆች በገድላቸውና በአንጋፋታቸው ብልጫ የሚሰጣቸው ዐብይ ዋቆች አሉ፡፡ እነሱም፡-

  • የቸሀ ዋቅ-አወጌት (አጌት)
  • የእኖር ዋቅ-ጀቨር
  • የእዣ ዋቅ-እንጌቨር
  • የእንደጋኝ ዋቅ-ሳእማር ናቸው፡:

እነዚህ ዋቆቹ እንዳረፉባቸው በሚታመንባቸው ቦታዎች ገራራ/ ቤተ እምነት የተሰራላቸው ሲሆን፣ በየአመቱ አንድ ጊዜ ክብረ በዓላቸው ይከናወናል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ፣ በጎሳ አባላት ብቻ የሚመለኩ በየጎሳው ስም የሚጠሩ ወይም የተወሰኑ ጎሳዎች በጋራ የሚያመልኳቸው በርካታ አዋቅ/ዋቆች አሉ፡፡ (የወንድወሰን፣1998 ፣29)

የጉራጌ ብሄረሰብ በዋናነት የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮችን የያዘ ነው፡፡ በተጨማሪም፣ የባሕላዊ እምነት ተከታዮች የሚገኙበት በመሆኑ፣ በእነዚህ ሃይማኖቶችና ባሕላዊ እምነቶች ስር የሚገኙ በርካታ በዓላት በኅብረተሰቡ ዘንድ ይከበራሉ፡፡ ከእነዚህ ክብረ በዓላት መካከልም በአብዛኛው የኅብረተሰብ አባላት ዘንድ በስፋትና በድምቀት የሚከበሩት የመስቀልና የዓረፋ (ኢድ አል አድሀ) በዓላት ናቸው፡፡

ሁለቱም በዓላት፣ የየሃይማኖታቸውን ሥነ-ሥርዓቶች ተከተለው የሚከበሩ ቢሆንም፣ የብሄረሰቡ ባሕሎች ይንፀባረቅባቸዋል፡፡ ከዚህ መካከልም በሁለቱም በዓላት በወንዶችና በሴቶች የሚከናወኑት ቅደመ ዝግጅቶች ይመሳሰላሉ፡፡

መስቀልና ኢድ አል አድሀ (ዓረፋ)፣ ከሁሉም በዓላት ይበልጥ በደመቀ ሁኔታ ቢከበሩም፣ በብሄረሰቡ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በሌሎች የእምነቱ ተከታዮች  የሚከበሩ በዓላትም በተመሳሳይ ይከበራሉ፡፡

በአንዳንድ ቤተ-ጉራጌዎች በድምቀት የሚከበሩ ሌሎች በዓላት ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በቸሀ ውስጥ ልዩ ስማቸው የቢጣራ እና ሞኬረር በሚባሉት ቀበሌዎች የሚከበረው ሰንቸ (የደሟሚት ክብረ በዓል) በዚሁ ቤተ-ጉራጌ አበዜ ወይም ወገፐቻ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ የሚከበረው ጭሽት (የቸሀ ዋቅ ክብረ በዓል) እና በእኖር ቤተ-ጉራጌ እናንጋራ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ የሚከበረው ንፑአር (የቦዠ ክብረ በዓል) ከሌሎች የባህላዊ  እምነቶች በዓላት ሁሉ ይበልጥ ብዙ ህዝብ የሚገኝባቸውና በድምቀት የሚከበሩ ናቸው፡፡

እነዚህ በዓላት በይበልጥ በስፋት የሚከበሩት በሰባት ቤት ጉራጌ ሲሆን፣ የክርስትናው ሃይማኖት በአህመድ ግራኝና በዮዲት ጉዲት ጥፋት በተዳከመበት ዘመንና የእስልምና ሃይማኖት በአካባቢው ባልተስፋፋበት ወቅት፣ በሁሉም ቤተ-ጉራጌዎች ዘንድ ሲከበሩ የቆዩ ጥንታዊ እምነቶች ናቸው፡፡

፡-

ቦዠ፣ በሰባት ቤት ጉራጌዎች ዘንድ እጅግ የሚፈራና የሚከበር የመብረቅ አምላክ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በማኅበረሰቡ የቤት መቃጠል፣ የእንሰት በመብረቅ መመታት እና የመብረቅ በከብቶች ላይ መውደቅ በሚያጋጥምበት ጊዜ ማጋዎች ካልመጡ በስተቀር ማንም ሰው የሚቃጠለው ቤት ውስጥ ያለ ንብረትን ለማውጣት የማይሞክር ሲሆን፣ ከዚያ ይልቅ በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች  እሳቱ እንዲጠፋና ንብረት ላይ ብዙ ጉዳት እንዳይከሰት ይርር (እልል) በማለት ለቦዠ ልመና እና ተማፅኖ በማቅረብ ከቁጣው እንዲበርድ ይለምናሉ፡፡

In Gurage religious beliefs, in the distant past, Boza their “Thunder god”; was handed over from yegzer their otiose high god, the responsibility for regulating the moral conduct and social behavior of Gurage towards one another.Boza omnipresence is manifested periodically through a stoke of lighting, and property thus destroyed in held to be asanction administered for abreach of the moral code, wittingly commited or not. (Shack, 1974, 19)

የቤት መቃጠልም ሆነ  ተመሳሳይ አደጋዎች የሚያጋጥሙት ሰው ቦዠን የሚያስቆጣ ተግባር በመፈፀሙ ሊሆን እንደሚችል  ስለሚታመን፣ ይህንን ቁጣ ለማብረድና በድጋሚ አደጋው በሱና በቤተሰቡ ላይ እንዳይደርስ ለማድረግ የሚፈፅማቸው የተለያዩ ተግባራትና ሥርዓተ- ክዋኔዎች አሉ፡፡

እነዚህ ተግባራት የሚከናወኑት አደጋ የደረሰበት ሰው ቤተሰቦችና የቅርብ ዘመዶች በሚያከናውኗቸው የጋራ ተግባራት ሲሆን፣ እነዚህን ተግባራት ሳያከናውኑ ቢቀሩ፣ የሚደርስባቸው አደጋ እስከ ሰባት ቤት (ዘር) ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ይታመናል፡፡

ቦዠ፣ በአካባቢው ኅብረተሰብ በተለያየ መልኩ የሚገለፅ ሲሆን፣ ፈጣሪ ነው፤ ከፈጣሪ ሦስት ልጆች አንዱ ነው፤ መልአክ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም፣ ቦዠ- መብረቅ ማለት ነው በማለት በተለያየ መልኩ ይገልፁታል፡፡ (እልፍኝ፣ 2ዐዐ2፣ 4)

ቦዠ ማለት፣ የአምላኮች አምላክና የእግዚአብሔር የቅርብ መልዕክተኛ ማለት እንደሆነም በብሄረሰቡ ላይ ጥናት ያካሄዱ ጸሐፍት ይገልፃሉ፡፡ (መልስ፣ 198ዐ፣1) የቦዠ አምላክ ማለት የመብረቅ አምላክ ማለት ሲሆን፣ ቦዠ የሚለው ቃል መብረቅ የሚለውን ቃል ሊተካ ይችላል፡፡

በመብረቅ አምላክ ማምለክና ማመን በዓለም በብዙ ቦታዎች የተለመደ ነው፡፡ ይህም መብረቅ በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ቁጣ ከመፍራት እና ራስን ከአደጋ ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንዲሁም ሰዎች ለፈፀሙት  ያልታየ ወንጀል ቅጣቱን እንደሚሰጥ  ይታመናል፡፡ (Hammond, 1994, 488) (Hearst, 2004, 23)

According to the famous poet Homer, who wrote the Iliad and the Odyssey, Zeus was considered the supreme god and ruled over the gods and goddesses in Greek mythology. He also ruled over humans. He was the god of thunder, god of the sky, god of rain, cloud gatherer, and god of justice. He is usually shown as a bearded man with long hair holding a thunderbolt in his right hand. His messenger was a strong eagle. He is usually symbolized by a thunderbolt, an eagle, a bull, or an oak. Zeus also had the ability to shape shift.[1]

በሌሎች የዓለም ክፍሎች በሚገኙ በብዙ አማልክት በሚያምኑ ህዝቦች ዘንድ ይኸው የመብረቅ አምላክ ይመለካል፡፡ ከአማልክቱ ሁሉ ዋና እና የሌሎች ነገሮች ፈጣሪ፤ ከሁሉም አማልክት የበለጠ ወይንም የአማልክቱ አባት ወይም የበላይ ተደርጐ ይወሰዳል፡፡

በኢስቶኒያ፣ በባልቲክ አገሮች፣ በቻይና፣ በዩርባና በሌሎች አገራት ይኸው አምላክ በቀደምት ትረካዎች ይገኛል፡፡ እንደየ አገራቱ የተለያየ ትርጉምና ስያሜ ተሰጥቶት ይገኛል፡፡ በስዊድን፣ በኖርዌይና በአይስላድ አካባቢዎች  በቀደምት ጊዜያት የታነፁ የመብረቅ አምላክ ማምለኪያ ሥፍራዎች የተገኙ ሲሆን፣ ለመብረቅ አምላክም “Thor” የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ Thursday (ሃሙስ) “Thor” ከሚለው ስያሜና ለመብረቅ አምላኩ መታሰቢያ ቀን እንዳዋለና በዚያ መነሻም ለቀን መጠሪያነት እንደዋለ ይታመናል፡፡ (Davidson, 1965, 3)

Sango is the God of Thunder. He lives in the sky and he creates the thunder that comes to the earth. His thunder bolt kills those that offend him of lights their houses on fire….. all Yourba people make offering to the gods they worship. Each god has favorite foods that a person may leave at the god’s shrine. Worshippers’ of a certain deity might wear beads or special clothing to show that the worship a particular god. (Hearst, 2004, 23)

በአፍሪካ ለምሣሌ በዩርባ የመብረቅ አምላክ ይታመናል፡፡ ይህ የመብረቅ አምላክ የማምለኪያ ሥፍራ ያለው ሲሆን፣ ሳንጎ በመባል ይታወቃል፡፡ በሰባት ቤት ጉራጌም ይኸው የመብረቅ አምላክ የሚታመን ሲሆን፣ በአደራ ጠባቂነት ይታወቃል፡፡ በማህበረሰቡ በቦዠ የሚጠበቅ ማንኛውም ንብረት ላይ ሥርቆት ያካሄደ ሰው መብረቅ በቤቱና በንብረቱ ላይ ጉዳት በማድረስ እንደሚቀጣም ይታመናል፡፡ በቦዠ እየተጠበቀ መሆኑን የሚገልፅ ምልክት የተደረገበትን ንብረት  በብሄረሰቡ ደፍሮ ለመስረቅና ለማጥፋት አይሞከርም፡፡ ይህንን ደፍሮ የሚያደርግ ቢገኝም ቦዠ ቅጣቱን እንደሚያወርድበት ይታመናል፡፡

በብሄረሰቡ በቦዠ የሚጠበቅ ንብረት ላይ ሁለት ዓይነት የመጠበቂያ መንገዶች (ምልክቶች) አሉ፡፡ እነዚህ ምልክቶችም ሸነ እና አረር በመባል ይታወቃሉ፡፡

  • ሸነ፡- ሸነ ቀጥተኛ የአማርኛ ትርጉሙ ከሰል ማለት ሲሆን፣ አንድ ሰው ተንቀሳቃሽ በሆነ ንብረቱ ላይ የሚያስተክለው ምልክት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- እንደሣር፣ የተቆረጠ እንጨትና የመሳሰሉትና በቀላሉ ከቦታ ወደቦታ የሚጓጓዙ እቃዎችን ሌባ እንዳይነካ በቦዠ የሚጠበቅ መሆኑን በሚገልፅ መልኩ የሚደረግ ምልክት ነው፡፡ ይህ ተግባር በአካባቢው ለሚገኝ ማጋ ጥቂት ብሮች በመስጠት ይከወናል፡፡ማጋውም በባለንብረቱ ጠያቂነት አንድ እንጨት ጫፉን ሰንጥቆ የከሰል ስባሪ በመሃሉ በማድረግና ንብረቱ በሚገኝበት አካባቢ ላይ በመስቀል ይፈፀማል፡፡
  • አረር/ቀይ ጨርቅ/፡- አረር አንድ ግለሰብ ቋሚ የሆኑ ንብረቶቹን እንደቤት ባህርዛፍ፣ ጫት፣ ፅድ፣ ዝግባና ሌሎች ለማስጠበቅ የሚጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡ ይህንንም አረር የአካባቢው ማጋ የሚያስረው ሲሆን፣ ቀይ ጨርቅ በእንጨት በመቋጠርና ንብረቱን ባለበት ቦታ ላይ በማስቀመጥ ሥርዓቱ ይፈፀማል፡፡

ሸነም ሆነ አረር የተሰቀለበት ንብረት ባለቤቱ እንደፈለገ መጠቀም ይችላል፡፡ ነገርግን፣ ሌላ ሰው ንብረቱን ቢነካ፣ ይህንን በፈፀመው ሰው ላይ ቦዠ መብረቅ በራሱ ላይ አሊያም በንብረቱ ላይ በመጣል ይቀጣዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሁለቱንም ምልክቶች  ባለንብረቱ በፈለገ ጊዜ ማሰቀልም ሆነ ማስነሳት ይችላል፡፡ ይህንን ምልክት የመትከል ወይንም የማንሳት ሥልጣን ያላቸው  ማጋዎች ብቻ ናቸው፡፡

ስለ ቦዠ ወደ ጉራጌ አመጣጥ የተለያዩ ታሪኮች ይነገራሉ፡፡ ከነዚህ መካከልም አጎራባች ከሆኑት ብሄሮች ከሲዳማ እና ከከምባታ በደንብ ስላልተያዙ ወደ ጉራጌ እንደመጡ የሚገልፁ የብሄረሰቡ ተወላጆች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በጉራጌዎች የእርስበርስ ጦርነት ወቅት ወደ ግዛታቸው እንደመጡና በአንድነት እንዲኖሩ ለማድረግ (ጦርነቱን ለማስቆም) እንደመጡና በኋላም መኖሪያቸውን እዚያው በማድረግ መቀመጣቸውን የሚገልፁ አዛውንቶች ይገኛሉ፡፡ በሰባት ቤት ጉራጌዎች ስለቦዠ አመጣጥ በስፋት የሚተረከው ትረካ  ዥምውድ ከተባለች ሴት ጋር የተያያዘ ነው፡፡

 

[1] www.lessonsnip.com

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com