ዜና

የቆዳ በሽታን (Skin Disease) በአብሽ፣እሬት፣ቁልቋል፣ቁርቁራ፣ግራዋ፣እንዶድ እና እርድ በቀላሉ ታከሙት

Views: 9373

የቆዳ በሽታ ጥቂት ምሳሌዎች

መግቢያ:- 

ቀደም ሲል፣ ፀጉርዎን እንዲህ ተንከባከቡ በሚል ለራስ ቆዳ እና ለጸጉር ጤንነት የሚረዱ ምክሮችን አስነብበን ነበር፡፡ አሁን ከዚያ የቀጠለ የሰውነት ቆዳን እንዴት ባለ ቀላል ዘዴ እቤት ውስጥ ሊዘጋጁ በሚችሉ የተፈጥሮ ነገሮች መንከባከብ እንደምትችሉ እናስነብባለን፡፡

ከሰውነት ክፍሎቻችን ትልቁ ቆዳችን ነው፡፡ ዋና ሥራው፡-

 • የሰውነትን እርጥበት እና ፈሳሽ ሚዛን መጠበቅ፤
 • ከፀሐይ ንዳድ መከላከል፣
 • የውስጥ አባል አካልን ሸፍኖ መጠበቅ፣
 • ከጀርሞች፣ አደገኛ ነገሮች እና ኢንፌክሽን መከላከል እና እጅግ የበዙ ሥራዎች ናቸው፡፡

ሀ)  የጎሉ የቆዳ ላይ ችግሮች

በሰው ቆዳ ላይ ብዙ ጊዜ ችግሮችን ከሚያስከትሉት ከፊሎቹ እነዚህ ናቸው፤ ማጣቀሻ አንድ

·         ፈንገስ  (Fungus)

·         ቋቁቻ

·         ፎረፎር (Dandruff )

·         አጓጉት ላሽ (Ring worm)

·         ጭርት፣

·         ፓሶሪያሲስ  (Psoriasis) ፎረፎር የመሰለ ነገር ግን የማይድን፣ የቆዳ ላይ በሽታ፤

·         የፀሐይ ቃጠሎ፣

·         የቆዳ ድርቀት፣

·         ችፌ፣ (eczema)

·         እከክ፣ (Scabies)

·         ሻህኝ (Kala-azer )

·         ብጉር፣ (Acne)

·         ማድያት፣ (Blemish)

·         ቆረቆር፣

·         የቆዳ ብልዝ ማለት፣

·         የቆዳ ኢንፌክሽን፣ (Skin infections)

·         እዥ ቋጠር፣ (Blister)

·         የቆዳ ላይ ሽፍታ፣ (Hives

·         ቦግ ያለ ቅላት፣ (Rosacea)

·         ንፍርቅ እባጭ፣ (Carbuncle)

·         ባክቴሪያ ወይም ፈንገስ ቆዳ ሥር ገብቶ ማጉረብረብ፣ (Cellulitis)

·         ኩፍኝ፣ (Measles)

·         የቆዳ ላይ ኪንታሮት (Wart)   እና ሌሎችም ይገኛሉ፡፡

ለ)  የከፋ የቆዳ ህመም ምልክቶች

 • ቀላ ወይም ነጣ ያለ እበጥ፤
 • ህመም ያለው ወይም የሚለበልብ ሽፍታ መውጣት፤
 • የቆዳ መቀረፍ ወይም መላጥ፤
 • የቆዳ መደደር፣ መሻከር፤
 • ቶሎ የማይድን ቁስል፤
 • ክፍት ቁስል፤
 • የቆዳ ቀለም መቀየር (መዥጎርጎር)፤
 • እዥ የቋጠረ እብጠት፤
 • ኪንታሮት፣ ጉብ ጉብ ያሉ ነገሮች፤
 • ማሳከክ፣መነፍረቅ፤
 • ከላይ ከተነገሩት ሁለትም፣ ሦስትም ዓይነት በአንድ ጊዜ መከሰት፤

ሐ.  መነሻ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉት

 • በቆዳ ቀዳዳዎች ውስጥ የባክቴሪያ መግባት፤
 • ፈንገስ ወይም በዐይን የማይታዩ ጥገኞች በቆዳ ላይ መኖር፤
 • ቫይረስ፤
 • የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም፤
 • የቆዳ መቆጣት ከሚያስከትሉት ነገሮች ጋር መነካካት፤
 • በስኳር በሽተኞች ላይ በባክቴሪያ፣ ፈንገስ፣ ችግሮች የሚከሰት፤
 • በጨጓራ ባክቴሪያ ምክንያት (ኤች.ፓይሎሪ የሚባለው)፤
 • ለሆድ ውስጥ በሽታ የሚወሰዱ አንዳንድ መድኃኒት፤

መ  የቤት ውስጥ ተፈጥሮአዊ ሕክምና ስትሹ ማቀጠሻ ሁለት

በዘመናዊ ሕክምና ምርመራ ማድረግ እና መታከም እንዳለ ሆኖ፤ ይህ የቤት ውስጥ የቆዳ ሕክምና ቀላል እና ለአብዛኞቹም ፍቱን ነው፡፡ በቤት የምታደርጉትን ሕክምና፣ የአካባቢ ሰዎችን በማማከር፣ የባሕል ሐኪሞችን በማማከር እንዲሁም ስለጉዳዩ ከመጽሐፍት ወይም ከመረጃ መረብ ላይ በማንበብ  የተሻለ ውጤታማ ልታደርጉት ትችላላችሁ፡፡

 1. በአብሽ ገላን መታጠብ

ሁለት  የሾርባ ማንኪያ የአብሽ ዱቄት፣ ግማሽ ሊትር ውሃ ላይ መነስነስ፣ ዱቄቱ ወደ ታች ወረዶ ሊጥ ሆኖ ሲወፍር በእጅ ወይም በትንሽ መምቻ መምታት እና ማዘጋጀት፤

 • ለዘወትር ከሆነ ሙሉ ገላን መለቃለቅ እና ትንሽ አቆይቶ መታጠብ፡፡
 • ከላይ የተነገሩ ችግሮችን ለማከም ከሆነ፣ በዚያ በተጎዳው ክፍል ላይ የአብሹን ሊጥ ለተወሰኑ ሰዓታት፣ ለአንድ ለሊት ወዘተ ቀብቶ ሸፍኖ ማቆየት እና መታጠብ፤

አብሽ ፀረ ፈንገስ፣ ፀረ ባክቴሪያ ስለሆነ፤ ለሰው ቆዳ ሲበዛ መልካም፣ ውበት እና ወዝ ይሰጣል፡፡

“በሰውነታችን ላይ ሽታ ያስከትላል” የምትሉ ባታውቁት ነው፤ ከቶም ሽታ አያስከትልም፡፡ ለማንኛውም መጨረሻ ላይ ገላችሁን በሎሚ ውሃ ተለቃለቁት፡፡ ስለ አብሽ፣ አዘገጃጀት፣ አጠቃቀም ወዘተ ከዚህ ሰፋ ባለ ሁኔታ በዚሁ ድር ገጽ ላይ “ፀጉርን እንደዚህ ተንከባከቡ” የሚለውን አንብቡ፡፡

“አብሽ ይሸታል፤ ይመራል” እያልን ሐሜት ስንሰንቅለት ኖርን፤ ያውላችሁ የሚያውቁት ሰበሰቡት፡፡ በዓለም ደረጃ ማን አብሽን በእህል ዋጋ እየገዛ እንደሚሰበስብ እና መልሶ በመድኃኒት ዋጋ እንደሚሸጥ በዚሁ ድረ ገጽ ላይ  “አብሽ ታሪካዊ የዋጋ ንረት አስመዘገበ!” የሚለውን አንብቡት፡፡ አበው/እመው “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል”  ነበር ሚሉት፤ አሁን እርሱ ቀርቶ “ከሞኝ ደጃፍ አዝመራ ይታፈሳል” ሆኗል ነገሩ፡፡

 1. በእሬት ጆሮ ታጠቡ

ወፍራም የእሬት ጆሮ ከሁለቱም ጎኑ ላይ ጠንካራ እሾህ መሳዩን ቆርጦ ማንሳት፣ ለሁለት መሰንጠቅ እና እንደ ሳሙና ይዞ ሰውነትን መቀባት፡፡

 • አዘውትሮ ለመታጠብ ከሆነ፤ ተቀብቶ ቢቻል ትንሽ ጊዜ የማለዳ ፀሐይ ተሙቆ መታጠብ ነው፡፡
 • ለተጎዳ የቆዳ ክፍል ከሆነ የተሰነጠቀውን የእሬት ጆሮ (ቅጠል) በፍም ላይ ሞቅ አድርጎ በላዩ ማሰር ነው፡፡ በቀን ሁለትም ሶስትም ጊዜ ቢሆን እንደዚህ አድርጎ ሲያበቁ መታጠብ ነው፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ለሳምንታት መጠቀም በእጅጉ ያሽላል፡፡

እሬት ኃይለኛ ፀረ-ፈንገስ እና ፀረ ባክቴሪያ ስለሆነ፣ በቆዳ ላይ ያሉ ችግሮችን በቶሎ ያስወግዳል፡፡

ስለ እሬት፣ አዘገጃጀት እና አጠቃቀም ከዚህ ሰፋ ባለ ሁኔታ በዚሁ ድር ገጽ ላይ “ፀጉርን እንደዚህ ተንከባከቡ” የሚለውን አንብቡ፡፡

ደብረ ብርሀን ዙሪያን ያየ፣ ሰሜን ጃናሞራን ወይም ቦረና ያቤሎን ያየ እሬት እንዴት ዱር የተተወ ወርቃማ ዘንጐች እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ እንደሚባለው ከሆነ በህንድ፣ በአውሮፓ እና በሌሎችም በዕውቀት የዳበሩ አገራት በየቤታቸው እሬትን ያለማሉ፡፡ እኛስ ብናለማ ምን ነበር?

 1. በቁልቋል በለስ ቅጠል ታጠቡ

ወፍራም የቁልቋል ቅጠል እያገላበጡ በፍም ወይም በብረት ምጣድ ላይ እሾሁን መለብለብ፡፡ ለሁለት መሰንጠቅ፤ እንደሳሙና ይዞ ገላን መቀባት፣ ትንሽ አቆይቶ መታጠብ፡፡

 • አዘውትሮ ለመታጠብ ይሆናል፡፡
 • ለተጎዳው ቦታ ከሆነ ግን ከላይ ለእሬት እንደተነገረው ደጋግሞ በላዩ ማሰር ነው

ቁልቋል በለስ ቆረቆር፣ ፈንገስ፣ ጭርት፣ ፎረፎር ወዘተ ድራሹን ያጠፋል፡፡

 1. በቁርቁራ ቅጠል (በቀሲል)  ታጠቡ

የቁርቁራ ዛፍ ቅጠል ደርቆ ይወቀጣል ወይም ይፈጫል፡፡ ይህ እጅግ የሚገርም የገላ መታጠቢያ ነው፡፡ ሁለት የሾርባ ማንኪያ ዱቄቱን ሁለት ኩባያ ውሃ ላይ አርሶ መበጥበጥ ነው፡ እጅግ የለደልዳል፡፡

 • ገላን መለቃለቅ እና ተቀብቶ፣ ትንሽ አቆይቶ መታጠብ ነው፡፡
 • ለተጎዳ የገላ አካል ከሆነ በወፍራሙ ቀብቶ ለሰዓታት፣ ወይም ለአንድ ለሊት ማሳደር ነው፡፡

የቀሲል ዱቄት በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል በጣም ይታወቃል፡፡ መርካቶ የባሕል መድኃኒት እና ቅመማ ቅመም የሚሸጥበት ተራ እንደ ልብ ይገኛል፡፡

ስለ ቁልቋል በለስ እና ቀሲል አዘገጃጀት እና አጠቃቀም ይበልጡን ከዚህ ሰፋ ባለ ሁኔታ በዚሁ ድር ገጽ ላይ “ፀጉርን እንደዚህ ተንከባከቡ” የሚለውን አንብቡ፡፡

 1. በግራዋ ቅጠል ታጠቡ

እርጥብ የግራዋ ቅጠል ደህና አድርጎ ማጠብ እና መጨፍጨፍ (መውቀጥ) ነው፡፡ በስስ ጨርቅ ውስጥ አድርጎ ውሃ እየነከሩ ገላን ማሸት እና መታጠብ፡፡

 • ለቆዳ መለባለብ፣ ለሚያሳክክ፣ ለፈንገስ፣ ወዘተ ጥሩ አብነት ነው፡፡

የግራዋ ቅጠል በእኛ አገር ብዙ ያልተነገረለት የመድኃኒት ቅጠል ነው፡፡ ገና ወደፊት ገናና ዜና ይነገርለታል፡፡ ጠብቁን፡፡ (“የእንስራ ማጠቢያ!”  እየተባለ ሲታማ እንደኖረው አይደለም፡፡)

 1. በእንዶድ ቅጠል እሽት አድርጉ

በአንዳንድ ችግሮች የተጎዳን ቦታ በእንዶድ ቅጠል ማሸት ጥሩ ነው፡፡ ፀረ-ፈንገስ፣ ስለሆነ ለብዙ የቆዳ ችግር በጣም ይረዳል፡፡

የአገሪቱ ቀደምት ባለ ሎሬት የሆኖቱ ዶ/ር አክሊሉ ለማ፣ ከእንዶድ ያገኙት የቢለሃርዚያ መድኃኒት መኖሩን አስተውሉ፡፡

 1. እርድ እና የአብሽ ዱቄት ተቀቡ

አንድ ሾርባ ማንኪያ እርድ ዱቄት እና አንድ የሾርባ ማንኪያ የአብሽ ዱቄት በአንድነት ቀይጡ  እና በውሃ በጥብጡት፡፡ በተጎዳው የሰውነት ቆዳ ላይ ቀቡት፣ ለሰዓታት ወይም ለአንድ ቀን አቆይታችሁ ታጠቡ፡፡ ውጤቱን በጥቂት ቀናት ታያላችሁ፡፡

የእርድ ቀለም ልብስ ያበላሻል፡፡ ነገር ግን ከአብሽ ሲደመር ደህና ይሆናል፡፡ እርድ ለሰውነት ግሩም መድኃኒት ሲሆን፣ ከፀሐይ ግን ተከለሉ፡፡

 1. ኤች ፓይሎሪ ባክቴሪያን አስወግዱ

በጨጓራ ውስጥ የምትገኝ ጠንቀኛ ባክቴሪያ አለች፡፡ የእሷ ችግር በፊት ቆዳ ላይ የቀለም መበላሸትን ያስከትላል፡፡ ያቺን ባክቴሪያ ማስወገድ ነው መፍትሔው፡፡ በዚሁ ድረ ገጽ “ኤች ፓይሎሪ አደብ ትግዛ”  የሚለው ርዕስ  ሥር አንብቡ

ማጠቃለያ፡-   

 • ለቆዳ ውበት እና ጤና ዘወትር በቂ ውሃ መጠጣት ያስፈልጋል፤
 • በተቻለ አቅም ከቀትር የፀሐይ ጨረር መከላከል ያስፈልጋል፤
 • በፊት ላይ ምርግ የሚሉትን ቅባት አለማዘውተር፤
 • ቢያንስ በየሳምንቱ ሰውነትን መታጠብ ተገቢ ነው፤
 • በ አንቲኦክሲደንት የዳበሩ ምግቦችን መመገብ፣ (ለምሳሌ፣ አረንጓዴ ፍራፍሬዎች፣ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው አትክልቶች እና ፍራፍሬ፣ ጥቁር አረንጓዴ የሆኑ ተክሎች እና በቫይታሚን ሲ የዳበሩ አትክልቶች)  ማለት ነው፡፡
 • ተልባ  ሙቀት ሳይጐዳው ማመስ እና ወቅጦ መብላት ወይም መጠጣት ለቆዳ ጤንነት እና ውበት ይለግሳል፤
 • አብሽ መጠጣት ለቆዳ ጤንነት እና ውበት ይለግሳል፡፡
 • ማንኛውም የቆዳ ላይ ችግር ሲከሰት ጊዜ አለመስጠት ነው፡፡
  • በቤት ውስጥ አማራጭ መድኃኒት ቶሎ- ቶሎ እራስን ማከም፣ በዚህ ካልተሻለ
  • ቶሎ ምርመራ አድርጎ ምን እንደሆነ ለይቶ ማወቅ፤ የሚሰጠውን መድኃኒት በአግባብ መጠቀም፣
  • በዘመናዊ ሐኪም ወይም በባሕል ሐኪም የተነገረውን ምክር መከተል፡፡

ለቆዳችሁ ጤንነት አብዝታችሁ ተጠንቀቁ፡፡

ማጣቀሻ፡-

1.      https://www.healthline.com/health/skin-disorders

2.     https//ethio-online.com

3. Sources, Courtesy tohttps://www.shutterstock.com/image-vector/skin-diseases-

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com