ዜና

የብሔራዊ ስሜት- አብነት!

Views: 380

(የሀገር ፍቅር ሲወደስ)

ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነውን DC-6 B አይሮፕላን፣ መስከረም 3 ቀን 1962 ዓ.ም. በሶሪያ የወንበዴዎች ቡድን (ጀብሃን ለማለት ነው) ተገድዶ ኤደን ባረፈ ጊዜ፣ የመንገደኞቹን ሕይወትና አይሮፕላኑንም ከቃጠሎ ያዳነው ም/አለቃ ካሳዬ ታደሰን የያዘው አይሮፕላን ከድሬዳዋ አዲስ አበባ፣ ትናንት ጥቅምት 3 ቀን 1962 ዓ.ም በዘጠኝ ሰዓት ተኩል ገብቷል። ቀድሞ በምድር ጦር ውስጥ ምክትል የአስር አለቃ የነበረውና አሁን በሲቪል አቪዬሽን ውስጥ የበረራ ደኅንነት ኢንስፔክተር የሆነው ካሳዬ ታደሰ፣ ከቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ በቀጥታ ወደ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ኼዶ፣ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ዘንድ ቀርቧል።

ጃንሆይም፣ ካሳዬ ታደሰ በቆራጥነትና በጋለ ብሔራዊ ስሜት ስለፈፀመው የጀግንነት ሙያው ባለአንድ ዘንባባ የቅዱስ ጊዮርጊስ የጀብዱ ሜዳይ/ኒሻን ሸልመውታል። እንዲሁም የምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግና ለቤሰቡም ጭምር የገንዘብ ስጦታ አድርገውለታል (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ማክሰኞጥቅምት 4 ቀን 1962 .ም፣ ገጽ 1)

“በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ምንም እንኳን ካሳዬ የአይሮፕለኑን ደኅንነት መጠበቅ ሥራው ቢሆንም፣ ለሥራ ግዴታው ብቻ ሳይሆን “ለሀገሩ ለኢትዮጵያ ያለውን ፍቅርና ብሔራዊ ስሜቱን ነው በግብር ያስመሰከረው” ሲሉ አድንቀዋል። ካሳዬ የተጓዦቹን ሕይወትና የአየር መንገዱን መልካም ስምና ክብር ሚያጎድፉትን ወንበዴዎች በጀግንነት ተቋቁሞ ይህንን ጀብዱ ስለፈፀመ ከፍተኛ ውለታ ለኢትዮጵያ ሀገሩ ውሎላታል። ያሳየው ምሳሌነትም ለብዙዎች አትጊና አርአያነትም የተሞላበት እንደሆነ ተስማምተዋል። ብዙዎች “እንደምን ተደርጎ ም/የመቶ አለቃ ካሳዬ ታደሰን ብሔራዊ ስሜት መግለጽ ይቻላል?” ሲሉ በአንድ ድምፅ ጠይቀዋል (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ማክሰኞጥቅምት 4 ቀን 1962 .ም፣ ገጽ 1 እና 6)

ከላይ ባሉት ሦስት አንቀጾች ላይ እንደተመለከትነው፣ ካሳዬ በተግባር ያስመሰከረው ለሀገሩ ያለውን ፍቅር (ስሜት) ነው። ይህም የሀገር ፍቅር (ስሜት)፣ ብሔራዊ ስሜት ነው እያሉ በተለዋጭነት የሚጠቀሙት አሉ። ለመሆኑ፣ ‘የብሔራዊ ስሜት ስንል ምን ማታችን ነው?’ ‘የቃሉ ፍቺና ትርጓሜስ በአማርኛችን አለ እንዴ?’ ካለስ ‘ፋይዳው ምንድነው?’ በተለይም፣ ‘ዘመኑ ራሱ ለብሔራዊ አስተሳሰብና ለብሔራዊ ስሜት ማቆጥቆጥ የተመቸ ነውን?’ ወይስ ‘በየሬዲዮውና በየቴሌቪዥኑ ላይ እንደምንሰማውና እንደምንመለከተው “የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች” (ምንም ማለባበስ አያስፈልግም “የጎሳና የጎሰኝነት”) ዘመን ነው?’ እነዚህንና እነዚህን መሰል ጥያቄዎች ለመመለስና ይህን “ብሔራዊ ስሜት” የተባለውን አኃዝ ምንነት ለመመርመር ይህ መጣጥፍ ጥረት ይደረጋል። በቅድሚያ ግን “አብነት” የሚለውን ቃል ትርጉም በመበየን እንጀምራለን።

“አብነት” የሚለውን ቃል፣ ደስታ ተክለ ወልድ፣ “ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት” በሚለው መጽሐፋቸው በገጽ 76፣ እንዲህ ሲሉ ይፈቱታል። “አብነት (ሲጠብቅ)፣ አባትነት፣ አባት መሆን፤ ምሳሌነት፣ መምህርነት፣ አርኣያ መሆን፤” አያለ ይቀጥልና፣ ሲላላ ደግሞም “ፍቱን መድኃኒት፣” ማለት ነው ይላል። በተጨማሪም፣ አብነት ማለት፣ ልዩነት ያለው የትርጓሜ ባህል ነው ይሉናል። ለማለት የፈለጉትም፣ የአንዱ ጎሳ የህልም ትርጓሜ ባህል ከሌላው ጎሳ ጋር ስምም አይሆንም ነው። ያንዱ “ብሔር” (በነገራችን ላይ ቃሉ ግዕዝ ሲሆን ትርጉሙም፣ “ሀገር” ማለት ነው፤) ከሌላው ብሔር በአኗኗሩና በሕይወት ትርጓሜው ልዩነት አለው። ያንን ልዩነት የመጠገኛውም ዘዴ “ብሔራዊ ስሜት” ይባላል (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም፣ብሔራዊ ስሜት ምን ማለት ነው?’ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ መስከረም 15 ቀን 1962 .ም። ገጽ 2 እና 8)

እንደፕሮፌሰሩ አተያይ፣ “ብሔራዊ ስሜት ከዝምድና፣ ከቋንቋ፣ ከሃይማኖት፣ ከትውልድ ቀዬና አውራጃም የሰፋ አስተውህሎትን የሚጠይቅ፤ በድካምና በጥረትም የሚፈጠር እንጂ፣ እንዲያው በዘፈቀደ የሚገኝ፣” አልቦ-ስሜት አይደለም። ስሜቱ፣ በአንድ ሀገር ውስጥ ያለውን ሕዝብ እርስ በርሱ እንዲቀራረብ፣ እንዲዋደድ፣ እንዲተሳሰብና እንዲረዳዳ የሚያደርግ ነው። የውስጥ ልዩነትን ጠግኖ የዘር፣ የቋንቋን፣ የሃይማኖትንና የሌላውንም ዓይነት ልዩነት የሚፈውሰው” ፍቱን መድሃኒቱ (አብነቱ) የብሔራዊ ስሜት ነው ሊሉ ከጅለዋል።

ወደ ሌሎች ሃተታዎች ከማለፋችን በፊት፣ በመጀመሪያ እስቲ ስለቃሉ ፍቺ አንዳንድ ነጥቦችን ማውሳት እንጀምር። ዶ/ር አብርሃም ደምወዝ በ1962 ዓ.ም፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንደገለጹት፣ “ብሔራ ስሜት ስንል፣ የቃሉ ፍቺ በተናጠል “ብሔራዊ” እና “ስሜት” ነው። ወይም ከእንግሊዝኛው “ናሺናሊዝም” የተዋስነው ሃረግ ነው። የዚህንም ሀረግ ሙሉ ትርጉም ለማግኘት በሰው ጠባይና በሰው እድገት ውስጥ ያለውን አንድ ዓይነት ስሜት መመርመር ያሻል። ልጁ መጀመሪያ “እኔ” የሚለው ቃል በጣም ይማርከዋል። ሁሉም ሰው “እኔ” በሚለው “እርሱነቱ” ዙሪያ ብቻም የሚኖር ፍጡር ሆኖ ይሰማዋል። ከዚያም ቀጥሎ ግን፣ “እኛ” የሚለውን ቃልና ስያሜም ለመያዝ ይጥራል። ይፍጨረጨራል።”

“ለጠቅ አድርጎም፣” ይላሉ ዶ/ር አብርሃም፣ “እናትና አባቱን “እኛ” በሚለው አኃዝ ውስጥ ይከታቸዋል። ከናቱና ካባቱም ለጥቆ ቤተሰቦቹን፣ ቤተ ዘመዱን እያስተዋለ ይሄዳል። አድማሰ አእምሮው እየሰፋ ሲሄድም ለመንደሩ ሰዎች፣ ከዚያም አልፎ ለወረዳውና ለአውራጃው፣ ብሎም ለክፍለ ሀገሩና ለሀገሩ ሰዎች፣ ወይም ደግሞ በአንድ ዓይነት ሁኔታ፤ ማለትም በመልክ፣ በዘር፣ በጠባይ፣ በሃይማኖት፣ በባሕልና በሌላም ነገር የሚመስሉትን ሰዎች “እኛ”ነት ውስጥ ይጨምራቸዋል።”

እንደ ዶ/ር አብርሃም አባባል ከሆነ፣ ይህም የእኛነት ስሜት ጫፍ ላይ ሲደርስ የ“ብሔራዊ ስሜትነት” ርካብን ይረግጣል። የብሔራዊነት ደረጃም ላይ የደረሰ ስሜት ያለው ሕፃን “እኛ” በሚለው አኃዝ ውስጥ፣ ልጁ በተወለደበት አገር የሚኖሩትን ሰዎች በሙሉ ያጠቃልልና፣ “እነርሱ” የሚለው አኃዝ ደግሞ ልጁ ከተወለደበት አገር ውጭ ያሉትን ባዕዳን የሚጠቀልል ስሜት ይሆናል። ስለዚህም፣ “ብሔራዊ ስሜት” ሲባል፣ በተባለው አገር ውስጥ የሚኖሩትን ዜጎች ሁሉ አጠቃልሎ እንደ አንድ ሕዝብ የመቁጠር ስሜት ነው (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 19 ቀን 1962 .ም፣ ገጽ 2 እና 4)

ፀጋዬ ገብረመድኅን በበኩሉ ስለብሔራዊ ስሜት ተጠይቆ ሲመልስ፣ “ብሔራዊ ስሜት የሚመነጨው ሀገርን ከማወቅ ጥልቅ እምነት ነው። ማለትም በሀገር አምኖ ለሀገርም ከመታመን አብነት ነው። ለምን ቢሉ በእምነት ላይ ያልተመሠረተ ብሔራዊ ስሜት ይዋልላል። ይዋዥቃልም። በቀላሉም ሊድበሰበስ ይችላል። ባንዳችም ግጭት ጊዜ በቀላሉ ሊጎብጥ፣ ብሎም ሊሰበር ይችላል። “አምኖ የመታመን እምነትም” ስንል፣ ያው በአገር ፍቅር ላይ የተመሠረተውን ስሜት ለማለት ነው። ይህ ስሜት፣ ለአገሩ ተወላጆች የአገሩ፣ የባሕሉ፣ የታሪኩና የእምነቱም ጭምር የባለቤትነት ስሜት የማካተት ኃይል አለው። “ብሔራዊ ስሜት፣” ለአገርና ለወገን የመቆርቆር ስሜት ነው። ጥቃትን ለመመከት የራስን ሕልውና መስዋዕት የሚያስከፍል እምነት ካለ፣ ያ ከብሔራዊ ስሜት የሚመነጭ ነው” (አዲስ ዘመን፣ ኅዳር 3 ቀን 1962 .ም፣ ገጽ 2 እና 5)። ።

የ“ሀገር ፍቅር ስሜት”ም ሲባል፣ የተራራው፣ የሜዳው፣ የቋጥኙ፣ የወንዙና የሸንተረሩ ፍቅር ብቻ አይደለም። በይበልጥ የተራራው፣ የሜዳው፣ የወንዙና የሸንተረሩ ባለቤት ለሆነውም ሕዝብ የሚሰጥ ነው። ብሔራዊ ስሜት፣ ዜጎች ከታሪካቸው፣ ከሃይማኖታቸውና ከሥልጣኔያቸው የሚያመነጩት፣ የራሳቸው ባሕል ልዩ መልክና ቅጂ ነው።

በተለይም “ባሕል” የሚባለው አኃዝ፣ በነዚህ በሦስቱ ላይ ተንተርሶ በጊዜው ላለው ትውልድ የሚመጥነውን መታወቂያ ይሠጠዋል። ትውልዱንም ልዩ የሚያደርገውን መለዮም ያለብሰዋል። በዘመኑ ካሉትም የሩቅና የቅርብ ጎረቤቶቹ የሚያመሳስለውን ወይም የሚያለያየውን passporort/መታወቂያ ይሰጠዋል። ሙሉ መብት፣ ክብርና ጥቅም የሚያቀዳጀውን፣ ሙሉ ኢትዮጵያዊ የሚያሰኘውንና ከኬንያዊው ወይም ከኩርዱ የተለየ ለኢትዮጵያ ስሜትና ራሮት እንዲኖረው የሚያደርገው ብሔራዊ ስሜቱ ነው። (የኢትዮጵያና የግብፅ ብሔራዊ ቡድኖች እግር ኳስ ሲጫወቱ፣ ለግብፅ የሚደግፍ ዜጋ/ዜጎች ካለ/ካሉ የብሔራዊ ስሜታቸው ወይም በኢትዮጵያዊነታቸው ያላቸው እምነትና መታመናቸው መመርመር አለበት። የእግር ኳሱን ግጥሚያ ወደለየለት የድንበር ግጭት ብንወስደውማ የስንቱ ብሔራዊ ስሜት የቱጋ እንደሆነ ይጋለጣል።)

በ1780ዎቹ የፈረንሳይ አብዮት ወቅት እንደተጀመረ የሚታወቀው nationalism በሁለት ማዳወሪያዎች ላይ የሚሽከረከር ታሪካዊ ዳራ አለው። አንደኛው የሚያጠነጥነው፣ የልዕለ-ኃይልን የበላይነት ከማስፈን ግብና የሌላውንም ሀገር ብሔራዊ ስሜት ከመሸርሸር አንጻር የሚሰላ ስሌት ሲሆን፤ ይህ ለሀገር ደኅንነት ሲባል የሚደረግ በመሆኑ የብሔራዊ ስሜት በጎ ጎኑ ነው። ሁለተኛው መገለጫው ግን አፍራሽ ነው። በሌላ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ መገንጠል የሚፈልጉትን ብሔሮች ወይም ክፍለ ሀገሮች ወይም ክልሎች በለየለት የአመጽና የሽብር/የውንብድና ተልዕኳቸው እንዲገፉበት የመሣሪያ፣ የስንቅና የሥልጠና ድጋፎችን በማድረግ እኩይነት ላይ የተመሠረተ ነው (Dictionary of Philosophy, (1980), Pp. 284-5)

ከአፍራሽ ጎኑ እንደምንገነዘበው፣ “ብሔራዊ ስሜት” በአፍራሻው ከበጎ መለዮው አልፎ-ተርፎ ክፉ ጠባያትን ወደ ውስጡ የሚያሰርጽበት ጊዜም አለው። የብሔረተኝነትን መለዮ ጠባይ የተላበሰ ሲሆንና፣ የከፍተኝነት (chauvinistic) ሕመም ፈጥሮ በዜጎች ላይ ከንቱ ተምኔት ያጫረ እንደሆነ፣ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ ጎረቤት ጋር ለዘላለሙ ያቀያይማል። ያራርቃልም። የበላይነቱን አባዜ፣ ብሔረተኛው በራሱ ባሕል ተፅዕኖ ምክንያት ያመጣው እንደሆነም የለየለት ጦርነት ውስጥ ይከተዋል። ለምሳሌ፣ የፋሺስት ፍልስፍና ወይም “የሱፐር ሬስ” (ማለትም የነጭ የበላይነት) ስሜት ሲኖረው አደገኛ ነው። ክፉ ደዌም ይሆናል። ዘረኛ ያደርጋል። “ከኔ ወዲያ ላሳር!” ያሰኛል። “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፤” እንዳለችው ፍጡር ያደርጋል። ወይም፣ እኛ ካልመራናችሁ/ካልገዛናችሁ በስተቀር ትበታተናላችሁ! ትፈራርሳላችሁ!”አይነቱን “የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ-መላልሶ” ያስከትላል። ስለዚህም ነው፣ የብሔራዊን ስሜት በሁለቱም አንጻር መመልከቱ ተገቢ የሚሆነው።

አንድ ሰው በአንድ አገር ውስጥ በመወለዱና እትብቱም በዚያው አገር በመቀበሩ ብቻ ብሔራዊ ስሜት አይኖረውም። የተወለደበት አካባቢና መንደር፣ የተወለደበትም ቤተሰብ ባህልና አኗኗር ዘይቤ ወራሽ ስለሆነ፣ አስተዳደጉንና እምነቱንም ያንፁታል። በመወለዱ ምክንያት፣ አንድ ሰው ለብሔራዊ ፍቅሩ ሥር መስደጃ ለም መሬትን ያገኛል። ፍፁም ሆኖ ይመሠረታል ለማለት ግን ያዳግታል። ያገሩ ሁናቴ፣ ያካባቢውና የሕዝቡ አኗኗር በብዙ ፍቅር ቢያሳድሩበትም ቅሉ፣ በአካል ተወልዶ በሕዝቡ ታሪክም አብሮ ካልተወለደ፣ ወይም የአዲስነት (የመጤነት) ስሜት ካለው፣ ወይም የተወለደበትን አገር ባህል ካላፈቀረው፣ ብሔራዊ ስሜቱን ሊያስቆጣ፣ አልፎ ተርፎም ክፉኛ ሊያመር ይችላል።

ለምሳሌ፣ በደቡብ አፍሪካ እንደነበሩት የነጭ ልጆች፣ ወይም በጣሊያን ጊዜ እንደነበሩት የባንዶች ልጆች ከሕሊና ወቀሳ “Guilty Conciousness” ጋር ስለሚያድጉ ብሔራዊ ስሜታቸው የተውገረገረ፣ የተጥበረበረና የተወላገደም ይሆናል። ጥቅም፣ ዝና፣ ገንዘብና ስልጣንም እስካመጣ ድረስ ለጫናቸው ሁሉ የሚጫኑ “ወደሎች” ይወጣቸዋል። ስሜታቸው ብሔራዊ በመሆን ፈንታ፣ ጥቅምና ፍርፋሪ በመለቃቀሙ ላይ ይተጋል። ስለዚህም ነው፣ ተወላጁ በስጋ (በእትብት) ብቻ መወለድ ሳይሆን በሀገሪቷ ታሪክና በሕዝቡም ባህል መወለድ የሚኖርበት።

አንድ ዜጋ ብሔራዊ ስሜቱ ከፍታና ዝቅታ የሚለየው በአድራጎቱ ነው። ተግባሩ ከስሜቱ የሚፈልቅ ነውና በዕለት ተለት የኑሮ ሁናቴው ላይም ይታያል። ለምሳሌም ያህልም፣ አፄ ምኒሊክ አድዋ ላይ ከጣሊያን ወራሪ ጋር በገጠሙበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያዊው ሕዝብ ያደረገውን ከፍተኛ ተጋድሎና ጀብዱ መጥቀሱ በእጅጉ ብሔራዊ እምነትን ይገልጻል። ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለው፣ ስለብሔራዊ ስሜት ወይም ደግሞ ስለሀገር ፍቅር ነው። ሰማዕታቱ ለታሪካቸው፣ ለባሕላቸውና ለሃይማኖታቸው/ለእምነታቸው ያላቸውን ቀናዊነት በአድራጎታቸው ገለጡት። “ነፃነት”ንም ለኛ ለልጆቻቸው አቆዩልን። ስለዚህም ነው፣ ብሔራዊ ስሜት የሚታወቀውና የሚገለጠውም በአድራጎት ነው የሚባለው።

በዕለት ኑሮና አኳኋን ብሔራዊ ስሜት ይገለጣል። ኢትዮጵያን የሚያስጠቃ ነገር ሲኖር ሕሊናን ቆርቁሮ፣ ወኔን ያነሳሳል። የመቶ አለቃ ካሳዬ ታደሰን መሰል ጀግኖችን ባልታሰበ ሰዓት ገቢራዊ ያደርጋቸዋል። የአቡነ ጴጥሮስን ደረት ለመትረየስ፣ የዘርዓይ ድረስን ልብ ለፋሺስቶች የቁጣ በትር፣ የአፄ ዮሐንስንም አንገት ለደርቡሽ ጂሀዲስቶች መስዋዕት ያስደርጋል።

ሀገር፣ ከጊዜው ጋርም እድትራመድ የግሉን ድርሻ ያበረክታል። ብሔራዊ ስሜት ከጊዜው ጋር አብሮ በብርቱ የመራመድ ፈቃድና ኃይል አለው። ለጊዜው ፈቃድ ጋሬጣ መሆን የብሔራዊ ስሜት ጥሩ ማሳያ አይደለም። የሀገር ታሪክና የህዝብ ፈቃድ እንቅፋትነት ነው። መሰናክልነት ነው። ዋጋ ያስከፍላል። የብዙ አምባ ገነኖች ስሜትና ብሔራዊ እምነት ከዚህ የመሰናክል “ድንጋይነት” መላቀቅ አቅቷቸው መቀመቅ አውርዷቸዋል። ብዙ ብዙ ምሳሌዎችን ከቅርብም ከሩቅም መጥቀስ ይቻላል። (“ሆድ ይፍጀው!” ብለን ወደቀጣዩ ንባባችን እንለፍ።)

አድራጎቶች ሁሉ አንድም ከበጎ ፈቃድ አሊያም ከትዕዛዛት የሚመነጩ ናቸው። በትዕዛዝ የሚደረገው ነገር ከጥቅሙ የተነሳ ወይም ደግሞ ትዕዛዙን ካለማፍረስ ተብሎ፣ ወይም በፍርሃት ተገድዶ የሚሠራ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን፣ የፍቃደኛነትን ያህል ሽራፊ እንኳን እምነት የለውም። ለጥቅም ሲባልም፣“መርሲነሪ” ወይም ወዶ-ዘማች መሆንም ያው ነው። ዘማቹ፣ የጦር ታክቲክ ያውቃል። በእሲያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በቅርባችንም በሶማሊያና በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች እንደምናየው ጉልበቱና ዕውቀቱ ለውጊያ ሳይፈቅድለት ሲቀር፣ ዘመን አመጣሹንም የጦር ስልትና የውጊያ ብልሀት ሳያውቅበት ሲቀር፣ ወይም ደግሞ የራሱ ዜጎች በጦር ግንባር መሠለፍ አዋጪ ሳይሆንለት ሲቀር፣ የግድ ወዶ ዘማቾችን (mercenaries) ይቀጥራል። ተዋጊው በእርግጥ ለኢራቅ ነፃነት ወይም ደግሞ ለአፍጋኒስታን ሉአላዊነት ደንታም የለው። ብቸኛ ተጋድሎውን የሚያደርገው፣ ለጥቅም ሲል ነው። የሬሳ ኪስ በርብሮ የሚከብረው ወዶ ዘማች ቁጥር ቀላል አይደለም።

ነገር ግን፣ በብሔራዊ ስሜቱ ምክንያት የሚንቀሳቀሰው ሰው አድራጎቱ ከባለቤትነቱ ልዩ ፍቃድና ለሀገሩም በመቆርቆሩ ጭምር ነው የሚሰዋው። ትርፍ ለማግኘት ብሎ የሚጋደለውን (አለዚያ ጥቅም አጣለሁ ብሎ የሚሞተውን)፣ ለሀገሩ ታሪክ፣ ለሕዝቡ ባህልና ለእምነቱም ሲል አምኖና ታምኖ በሙሉ ፍቃደኝነት “ፋኖ-ፋኖ!” ብሎ ከሚሞተው ጽኑ ባላገር (የሀገሩ ባለቤት) መለያየት አለብን። የቅጥረኛው ስሜቱ በንዋይና በጥቅም ስካር የተተመነ ሲሆን፣ የጽኑው ተጋድሎ ግን መለካት ካለበት፣ በሀገር ፍቅር ስሜት ከመንደድና በባለቤትነት ከመቆርቆር የሚገነፍል እልህ ኾኖ ነው።

መደምደሚያ፤

ብሔራዊ ስሜትን ለዜጎች ማስረጽ የሚቻለው፣ አርኣያነትና ምሳሌነት ያላቸውን ባለውለታዎች ማንነትና ተጋድሎ በማስተማር ነው። አርኣያ፣ ምሳሌና መምህር የሚሆኑትን የብሔራዊ ስሜት አማኞች በዘዴና በአግባቡ መርምሮ ማስጠናት ብዙ የሀገር ፍቅር ስሜት ያላቸውን ወጣቶች ለማፍራት ያስችላል። አርአያዎች ከሌሉት፣ ተከታዩ ትውልድ የሚያምንበት እውነትና እምነት ያጣል። የሰረፀ የእምነት ቀንጃ ከሌለው ደግሞ – ብሔራዊ ስሜትና እምነት አይኖረውም። አርአያነት ስንልም ጥሩውን ከመጥፎው ለይተን/ነጥለን ለተመልካቹ ትውልድ የሚከተለውን አርአያ ከፍታ ማሳየት ይገባናል። ጥሩ አርአያን በማየት፣ ጥሩ ጥሩ ተከታዮች እንደሚሽቀዳደሙ ሁሉ፣ ለመጥፎውም አርአያ መጥፎ ተከታዮች ከያሉበት ይሯሯጣሉ። ዛሬ ኢትዮጵያ በነዚህ፣ የመጥፎዎች የፉክክርና የወለወልዳነት እሩጫ ላይ ደርሳለች። ለማንም አርአያና ምሳሌ የማይሆኑ ጀሌዎች አስተዳደሩን፣ አመራሩን፣ ቢሮክራሲውንና የእምነት ተቋማቱን ሳይቀር አጨናንቀውታል። መጥኔ!

ለወጣቱ ትውልድ ለማስተማርም ሲባል፣ በመጀመሪያ ሠርተነው መገኘት አለብን። ሌላውን ለማሳመን ስንፈልግ፣ መጀመሪያ ራሳችን አምነነው መገኘት አለብን። ያመኑትን “እምነት” ደግሞ በሥራ ማስመስከር ሲቻል መልካም “አርአያነት”፣ ፍቱንም አብነት ይሆናል። ለተከታዩ ትውልድም፣ ያንን አርአያነት፣ ያንን የእምነት አብነት፣ ምሳሌ ሆኖ፣ አርአያ ሆኖ፣ መምህርና አባትም ሆኖ ለማሳየት አያቅትም።

በስመ “ታላቁ መሪነት!”፣ በስመ “ጀግናነት!” በስመ “የልማት አርበኝነት!” እንዲሁም በስመ “የሕዳሴው ምንትስነት!” የማያምኑበትን “ጣዖት” ነጋ-ጠባ መደስኮሩ እርባናም የለው። ጊዜያዊ ጥቅሙም ቢሆን እምብዛም ነው። ምናልባትም፣ ወጣቱን ያዘናጋል ተብሎ የሚሠራ ፍጆታ ከመሆን የዘለለ ቁብም የለው። ብሔራዊ ስሜት ሆኖ የማንንም ቀልብ አይስብም። የአትሌቶቹንና የኳስ ተጫዋቾቹን ያህል እንኳን በብሔራዊ ስሜት ማንንም አያስተቃቅፍም። ጽዋም አያስነሳ። ከንቱ ጩኸት ነው። “ቢከፍቱት ተልባ ነው!” ቢከፍቱት ባዶ …! (አንድ ቀን ደግሞ በገሃድ መከፈቱ አይቀርም። የዚያን ጊዜ ሰዎች ይበለን!)

This site is protected by wp-copyrightpro.com