አራት የኤርትራ ባለሥልጣናት በአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው አለፈ ተባለ

Views: 124

– “ምንም የሰማሁትና የማውቀው ነገር የለም” በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር

ዓርብ ነሐሴ 3 ቀን 2011 ዓ.ም፡- አራት የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ በድንገት በተከሰተ የአውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ማለፉ በማህበራዊ ሚዲያ ይፋ ሆኗል፡፡ በአንፀሩ፣ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር አቶ አርዓያ ደስታ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ተከሰተ ተብሎ ስለተገለጸው አደጋ ምንም እንደማያውቁና መረጃ እንደሌላቸው ለኢትዮ-ኦንላይን ዘጋቢ በስልክ ገልጸዋል፡፡

እንደ ማህበራዊ ሚዲያ ዘገባ ከሆነ፣ በአደጋው ሦስት የኤርትራ አየር ኃይል አባላት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ አንዱ ግለሰብ ደግሞ በፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት የሚያገለግል እንደሆነ ነው የተጠቀሰው፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙት የኤርትራ አምባሳደር አቶ አርዓያ ደስታ፣ “በእርግጥ አደጋው ተከስቶ ከሆነ አረጋግጬ የተጣራ መረጃ ይዤ እድውልላችኋለሁ፤ ለጊዜው አደጋው ስለመከሰቱ የደረሰኝ መረጃ የለም” በማለት ለኢትዮ-ኦንላይን ተናግረዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የዜና ምንጭ ተደርጋ የተጠቀሰችው፣ በውጪ ሀገር የምትኖረውና የኤርትራን መንግሥት በመቃወም የምትታወቀው ሰላም ኪዳኔ የተባለች ግለሰብ ናት፡፡ በእርሷ የማህበራዊ ገጽ ላይ የሟቾቹን ፎቶ አመላክታለች፡፡

የአውሮፕላን አደጋ ስለመከሰቱ ሌሎች የኤርትራ ምንጮችም የገለጹ ቢሆንም፣ እስካሁን ስለ አደጋው ዝርዝር ሁኔታ በኤርትራ መንግሥት በኩል ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com