ኮሚሽኑ ከሀምሳ ስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን እንደያዘ አስታወቀ

Views: 119

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት፣ ከሀምሳ ስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው  በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገቡ የነበሩና ከሀገር ሊወጡ የነበሩ የተለያዩ ዓይነት ዕቃዎችን መያዙን አስታወቀ፡፡

በጠቅላላ ከተሰበሰቡት ዕቃዎች ውስጥ ከአርባ አራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ወደ ሀገር ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሚገቡ ዕቃዎች ሲሆን፣ የተቀረው ከሀገር ውጭ በሕገ-ወጥ መንገድ ሊወጡ ሲሉ ከተያዙ ዕቃዎች እንደሆነ የኢትዮጵያ የጉምሩክ ኮሚሽን ሪፖርት ገልጿል፡፡

በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው በኮንትሮባድ ሲጓጓዙ የነበሩት ዕቃዎች የተያዙት በአስራ አራቱም የጉምሩክ መፈተሻ ጣቢያዎች ነው፡፡

የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ወደ ሀገር ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ሊገቡ ሲሉ ከተያዙት ዕቃዎች ውስጥ ሃያ አምስት በመቶ የሚሆነውን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ ከኮሚሽኑ ያገኘውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

የሀዋሳ፣ የጅግጅጋ እና ሚሌ የጉምሩክ መፈተሻዎች እያንዳንዳቸው አስራ ሁለት በመቶ የሚሆነውን በሕገወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በመያዝ እንዲሁም ሞያሌና አዲስ አበባ የአቃቂ ጉምሩክ ፍተሻ ጣቢያዎች እያንዳንዳቸው ዘጠኝ በመቶ የሚሆነውን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎችን እንደያዙ ተነግሯል፡፡

ወደ ሀገሪቷ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሚገቡ ምርቶች ውስጥ አዳዲስ አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክሶች፣ ምግብና መጠጥ፣ አደንዛዥ ዕጾች፣ ሲጋራ፣ መድሀኒቶች፣ የተሸከርካሪ መለዋወጫዎችና የጦር መሳሪያዎች እንደሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ከነበሩ ውስጥ ስልሳ ስምንት በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድና በጅግጅጋ ጉምሩክ የተያዙ ናቸው፡፡

በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ሀገራት የሚወጡት የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች፣ አደንዛዥ ዕጾች፣ ምግቦች፣ ጫት፣ ሚንራሎች፣ ነዳጅ እና የቁም ከብቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com