በቦረና የሰውና የቀንድ ከብት የሕይወት ትሥሥር

Views: 141
  • ከብቶች ጤነኛ ሲሆኑ ማኅበረሰቡ በተድላ ይኖራል፤

በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን ሀብት የሚለካው አንድ ሰው ባለው የከብቶች ብዛት፤ ንግድ የሚካሄደውም በከብቶች፤ የጋብቻ ጥሎሽም የሚሰጠው ከብት ነው፡፡ በአጠቃላይ በአካባቢው ችግር ካለ እንኳን የሚፈታው ከብቶችን በመስጠት ነው፡፡

በቦረና አካባቢ ከብቶች ጤነኛ ሲሆኑ፣ ማህበረሰቡ በተድላ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ከብቶች ከታመሙና ከሞቱ የማህበረሰቡ ህይወት ይዘበራረቃል ሲሉ የዘገቡት በአካባቢው ‹‹አክሽን አጌነስት ሀንገር›› በተሰኘው የግብረ ሠናይ ድርጅት የኮሚኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ሊስ አራንጎ ናቸው፡፡

በአካባቢው ያልተጠበቀ የአየር ንብረት ለውጥ በቁም ከብቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት በየጊዜው እንደሚያደርስባቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም በቦረና ዞን በቴሶ ቄሎ መንደር በተከሰተው ድርቅ ነዋሪዎቹ ላሞቻቸውና ሌሎች የቁም ከብቶቻቸውን በሞት አጥተዋል፡፡ በአካባቢው ከብቶቹ የሚበሉት ግጦች ሲደርቅና ውኃ ሲጠፋ የተወሰኑትን ለመሸጥ ወደ ገበያ ይዘው ቢወጡም፣ ከብቶቹ ከስተው ስለነበር ማንም ሊገዛቸው ፍቃደኛ እንዳልሆነ የመንደሯ ነዋሪ አቶ ጋርቢቻና ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡

በወቅቱ በተከሰተው ድርቅ ጋርቢቻና ቤተሰቡ ለረሀብ ተጋልጠው አሰቃቂ ጊዜ እንዳሳለፉ ይናገራሉ፡፡ “ከአምስቱ ልጆቼ ውስጥ ሦስቱ ከባድ የምግብ እጥረት ውስጥ ሲገቡብኝ በአካባቢያችን ወደ አለው አክሽን አጌነስት ሀንገር ፕሮግራም አስገብቻቸው፤ ከሳምንታት ህክምና እና እንክብካቤ በኋላ ሊያገግሙ ችለዋል” ብለዋል፡፡

በዚህ ዓመትም ለአካባቢው ማህበረሰብ ይህ ድርቅ አስጊ እንደደሆነ የሚያሳየው በአካባቢው ያሉት አብዛኛዎቹ የውሃ ቦታዎች ባዶ ሲሆኑ፣ ውሃ ያላቸው ሁለት ቦታዎች ብቻ እንደሆኑ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች ውሃ ለማግኘት የሦስት ሰዓት የእግር መንገድ ተጉዘው ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውል ውሃ ያመጣሉ፤ በተመሳሳይም ከብቶቻቸውን ይዘው ለሦስት ሰዓታት ውሃ ለማግኘት ይጓዛሉ፡፡

“ይህ ጉዳይ በዚሁ ከቀጠለ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ አሁን ለከብቶቻችን የሚሆን ግጦች አለን ነገር ግን ውሃ ከጠፋ ሁሉም ነገር ይጠፋና ከብቶቻችን ያልቁብናል፤ እነሱ ደግሞ ህልውናችን ናቸው” ያሉት የአካባቢው ነዋሪ አቶ ገርቢቻ ናቸው፡፡

አክሽን አጌነስት ሀንገር የአካባቢውን ነዋሪዎች በሚያጋጥማቸው የውሃ እጥረትና የግጦሽ ሳር ድርቅ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሁሉም የአካባቢው አርብቶ አደሮች መሬትን በማጠርና ቁጥቋጦዋችን፤ ደረቅ ዛፎችንና አረምን በማፅዳት ለግጦሽ የሚውለው ሳር እንዲያሳድጉ በማድረግ የከብቶቻቸውን ህይወት እንዲያራዝሙ እየሰራ ነው፡፡

በድርጅቱ የማህበረሰብ ወኪል የሆኑት አቶ ኤዳኦ ወርቁ ይህ እንቅስቃሴ ነዋሪዎች እንዴት ረሃብን ለመዋጋት እንደሚረዳቸው ሲገልፁ፣ ዝናብ የሚዘንብበት ጊዜ ሲዛባ የግጦሽ መሬቶች ይደርቃሉ፤ በዚህ ጊዜ ነዋሪዎቹ ለችግር ጊዜ ብለው ያከማቹትን ሳር ለከብቶቻቸው እንዲመግቡ በማድረግ በህይወት እንዲቆዩ ማድረግ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ነገር ግን፣ ይህ ሁሉንም ችግር ይፈታል ወይም ዘላቂ መፍትሄ ነው ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም፣ የውሃ ፍላጎት ሁሌም እየጨመረ ስለሚሄድ ሌሎች መፍትሄዎች መምጣት አለባቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com