የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባውን ዛሬ ይጀምራል

Views: 131

ገዥው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በድርጅታዊና ሀገራዊ ወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያይ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የድርጅቱ አፈፃፀም እና ወቅታዊ ጉዳዮችን ገምግሞ ቀጣይ የፖለቲካ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል፡፡

36 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ስብሰባዎች በአመዛኙ ከአንድ እስከ ሁለት ቀናት የሚወስድ ሲሆን፣ ዛሬ የሚጀመረው ስብሰሰባ ግን ከዚህም በላይ ሊረዝም እንደሚችል ይገመታል ሲሉ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ግንባሩ በአሁኑ ጊዜ በውስጥ እና በውጭ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ይገኛል፤ ብሔር ተኮር አደረጃጀቱ በግንባር አባላቱ መካከል ልዩነቶችን በመፍጠር ለቀውስ ዳርጎታል ብለዋል፡፡

በአራቱ የኢሕአዴግ ግንባር ድርጅቶች መካከል በይፋ ባይገለፀም የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች በተግባር ጎልተው ይታያልም ሲሉ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡

ህወሓትና አዴፓ በቅርቡ ያወጧቸው የልዩነት መግለጫዎች የማዕከላዊ ኮሚቴውን ስብሰባ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ይገመታል ተብሏል፡፡

በዐማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) መካከልም አለመግባባቶች እንዳሉ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው፡፡

በክልልነት ጥያቄዎች ውጥረት የገጠመው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጉዳይም የኢሕአዴግን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ውስብስብ እንደሚያደርገው ይጠበቃል፡፡

የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አብይ አህመድ ‹‹በኢሕአዴግ ውስጥ ግንባርና አጋር የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ አንድ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ እንመሠርታለን፡፡›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ሕወሓት በበኩሉ እንኳንስ ለመዋሐድ ከአዴፓ ጋር አብሮ እንደማይሠራ አስታውቋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com