“ሕገ-መንግስቱ መሻሻል አለበት፤ ሕገ -መንግስቱ ሕይወት ያለው ሰነድ ነው” ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ

Views: 155

ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ዛሬ ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ‹‹የኢትዮያን የፖለቲካ አጀንዳ  አድማስ ማስፋት›› በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ባዘጋጀበት መድረክ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይቱን አካሂዷል፡፡

በውይይቱም የተለያዩ ምሁራን እና የፖለቲካ አመራሮችን በመጋበዝ በሀገራችን ወቅታዊ  ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን እንዲያንሸራሽሩም አድርጓል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝምና የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ፣ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዴሞክራሲያዊና የፌደራል ሥርዓት››ን አስመልክቶ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ሃሳብ ላይ ሕገ መንግስቱ መሻሻል አለበት፤ ሕገ መንግስቱ ሕይወት ያለው ሠነድ ነው፤ ይህንን ታሳቢ አድርጎም ማሻሻል ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሕገ መንግስታችን ከጸደቀ 25 ዓመቱን አስቆጥሯል ያሉት ዶ/ር ሲሳይ፣ እነ ደቡብ አፍሪካን የተመለከትን እንደሆነ ግን ሕገ መንግስታቸውን 17 ጊዜ አሻሽለዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

ሕገ መንግስቱ በፍጹም መነካት የለበትም የሚሉት አካላትም ሕገ መንግስቱን አያውቁትም ሲሉም በመደረኩ ላይ ገልጸዋል፡፡

ስለሆነም፣ ሕገ- መንግስቱ ለአንድነት ከመቆም ይልቅ ለመገንጠል ነው ቅድሚያ የሚሰጠው፤ ለምሳሌ ያየን እንደሆነም አንቀጽ 39ን ለአብት ማንሳት ይቻላል፤ ይህ ማለት ግን ሕገ መንግስቱ ምንም ጠቃሚ ሃሳቦች የሉትም ማለት አይደለም ሲሉም ዶ/ር ሲሳይ አስረድተዋል፡፡

የሀገራችንን ዴሞክራሲ አስመልክቶ ሲያበራሩም ኢሕአዴግ የሚከተለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢሆንም፣  ራሱ ድርጅቱ ዴሞክራሲን የማይተገብር በመሆኑ ለሀገራችን ዴሞከራሲያዊ ሥርዓትን  ያመጣል ብሎ ማሰብ ትክክልም አይደለም ብለዋል፡፡

በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩልም እርስ በእርስ ሲተፋፈኑ የምንመከተው ጉዳይ ነው ሲሉም በአሁን ወቅት ያለውን የሀገራችን የዴሞክራሲ ተፈጻሚነቱን አመላክተዋል፡፡

ፌዴራሊዝም ያለ ዴሞክራሲ ሊተገበር እና ውጤታማ ሊሆን እንማይችልም በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡

ከዶ/ር ሲሳይ በተጨማሪ በአሁን ወቅት በፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ በማስተማር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መላኩ ተገኝ ደግሞ በፓናል ውይይቱ ላይ የመሬት ጥያቄ ሕገ-መንግስት ውስጥ መካተት  እንዳልነበረበት ተናግረዋል፡፡

የብሔርተኝነነት ጥያቄን አስመልከቶም የብሔር ጥያቄ ዛሬ የመጣ ጥያቄ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ በነገድ አማካይነት ይነሳ የነበረ ጉዳይ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

እንዲሁም በአሁኑ ወቅት  በሀገራችን ስለ ልማት የተዛባ አስተሳሰብ ስላለ እሱን የማጥራት ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ እና ሰዎች የመደራጀት ሃሳባቸውን በነጻነት መግለፅም ይገባል ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባላሙያ እና የቀድሞ የኢዴፓ አመራር አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የሚታያው ስጋት እና ተስፋ መኖሩን ጠቅሰው የከረረ ብሔረተኝነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ኢህአዴግ ተቀባይነት አላቸው የሚባሉትን የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችን ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም እንዲያመቸው እነዚህን ሰዎች አሳጥቶናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም ይህ ዓይነቱ ውይይት በተለያዩ ርዕሶችን በማዘጋጀት ችግሮች በውይይት ሊፈቱ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት አጋርተዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com