አብዲ ኢሌን ለማስለቀቅ አሲረዋል የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

Views: 126

የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳት የነበሩትና በሶማሌ ክልል በተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ግድያ፣ አካል ማጉደል፤ ማፈናቀል እና አብያተ ክርስትያናትንና የንግድ ተቋማትን በማቃጠል ክስ ተመስርቶባቸው ማረሚያ ቤት የሚገኙትን አብዲ ሞሐመድ ዑመርን፣ ሐምሌ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ከነበራቸው ችሎት ወጥተው ወደ ማረሚያ ቤት ሲሄዱ ለማስመለጥ አሲረዋል የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡

አቶ አብዲ ኢሌ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የነበራቸውን ቀጠሮ ጨርሰው ወደ ማረሚያ ቤት ሲሄዱ፣ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መግቢያ አካባቢ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች መኪና በማዘጋጀት የተከሳሹን መምጣት በመጠባበቅ ላይ እያሉ ያቆሙትን መኪና ከማረሚያ ቤቱ አካባቢ እንዲያነሱ በትራፊክ ፖሊስ ቢጠየቁም፣ አናነሳም በማለታቸው ጥርጣሬ የገባቸው የፖሊስ አባላት መኪናው እንዲፈተሸ ሲጠየቁ እንቢ በማለታቸውና ፀብ በማንሳታቸው ከፖሊሶች ጋር ተኩስ ተለዋውጠው አንድ ሰው መመታቱ ተዘግቧል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የተወሰኑት ሲያመልጡ፣ አንዲት ሴትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው በምርመራ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አካባቢ ቤት ተከራይተው እንደነበርና በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ በርካታ የጦር መሳሪያዎችም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ሪፖርተር ጋዜጣ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቦታል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com