ቀይ መስቀል ከስደት ተመላሾችን እያቋቋመ ነው

Views: 132

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርና የቀይ መስቀል ዓለም አቀፍ ኮሚቴ በመቀሌ ከተማ ለሚኖሩ ከአንድ ሺህ በላይ ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከስደት የተመለሱ ዜጎችን በተለያዩ አነስተኛ አትራፊ ሥራዎች በምርጫቸው ሰርተው ራሳቸውን በገቢ መደገፍ እንዲችሉ ለማድረግ እንደሆነ የቀይ መስቀል ዓለም አቀፍ ኮሚቴ ተወካይ ሚስተር ኩርሼድ ሙሰያቶቭ ተናግረዋል፡፡

በቀይ መስቀል የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ከስደት ተመላሾች እንደሚሉት፣ ፕሮጀክቱ በተለያዩ የሥራ መስኮች እንድንሰማራ የገንዘብና የማሽን ድጋፍ እያደረገልን እራሳችንን እና ቤተሰባችንን መደገፍ ችለናል ብለዋል፡፡

ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆነችው ወ/ሮ ህይወት ገ/እግዚአብሔር፣ በስደት ከምትኖርበት ኤርትራ ወደ ሀገሯ ተመልሳ ስትመጣ ምን እንደምትሰራ እና ልጇን እና ራስዋን በምን እንደምታስተዳድር ግራ ተጋብታ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር በጥገኝነት መኖር በጀመረችበት ወቅት እንደ እድል ሆኖ ብዙም ሳትቆይ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የራሷን ገቢ እንድታገኝ የልብስ ስፌት ማሽን ከነመሳሪያዎቹ ድጋፍ እንደተደረገላት ትናገራለች፡፡

“አሁን እያገዝኩ ያለሁት ራሴን ብቻ ሳይሆን ለልጄ በቂ ገንዘብ በመላክ ትምህርቷን በተገቢው ሁኔታ እንድትማር እያደረኩ ነው፤ ከዚህ በፊት ይህን ለማድረግ የሚታሰብ አልነበረም” ብላለች፡፡

ሌላው ከዚህ እድል ተጠቃሚ የሆነው ወጣት ከስደት ተመለሽ ገ/ጊዮርጊስ ብርሀኑ እንደሚናገረው፣ ቀይ መስቀል የልብስ ማጠቢያ ማሽን እና ተያያዥ ዕቃዎችን ሰጥቶኝ. አሁን የራሴን ገቢ በማግኘት ራሴን እና ቤተሰቦቼን እያገዝኩኝ ነው ብሏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com