መዓዛ አሸናፊ አነጋጋሪ ሆነዋል

Views: 170

በሀብቴ ታደሰ እና ጌጥዬ ያለው

“በትግራይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብና ፍትሕን ለማስፈን፣ የመከላከያ ሠራዊት እገዛ የግድ ነው” ሲሉ የኢፌድሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፣ መናገራቸው በማኅበራዊ ሚዲያ እያነጋገረ ነው፡፡

ባለፈው ዓርብ በተጀመረው ዓመታዊው የፍትሕ አካላት ስብሰባ ላይ በተካሄደው ውይይት፣ ‹‹በትግራይ ክልል ተሰባስበው የሚገኙ ተጠርጣሪ አካላትን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋልና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር፣ የክልሉ መንግሥት ተባባሪ ባለመሆኑ፤ ፌዴራል ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል›› በማለት መናገራቸውን ምንጮች ለኢትዮ-ኦንላይን ተናግረዋል፡፡

የፍርድ ቤት ውሳኔ እየተፈጸመ አይደለም ያሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፤ ፍርድ ቤቶች ይታሰሩ ያሏቸውን ሰዎች ክልሎች ከለላ ሰጥተው በማስቀመጥ ለሕግ አስፈፃሚው አካልና ለፌዴራል መንግሥት ዳተኛ ሆነዋል ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ቢሞከርም፣ የክልሉ መንግሥት ግን ተባባሪ አለመሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘደንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ገልጸዋል መባሉን ተከትሎ፣ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው፡፡

ወ/ሮ መዓዛ፣ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ በመቸገራቸው፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብቶ እንዲያግዛቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ሕግ አስፈፃሚው የመንግሥት አካል ያለው አቋም አለመታወቁን ብዙኃን መገናኛ ዘግበዋል፡፡

የፕሬዚደንቷ ንግግር ጠላትን በመፍጠር የሕዝብ ውግንናን የማግኘት ፍላጎት ላለው ህወሓት ጠቃሚ የፖለቲካ ምኅዳር እንደሚፈጥርለት ብሎም በሕዝብ ዘንድ ፍርሀትን በማሰራጨት ድጋፍ ያሰባስብበታል ሲል ዘገባው አብራርቷል፡፡

ህወሓትን በመደገፍ የሚታወቁ የፖለቲካ አቀንቃኞችም በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን የወይዘሮ መዓዛ አሸናፊን ንግግር ሲኮንኑ ሰንብተዋል፡፡ እነኝህ አቀንቃኞች ህወሓት “ዲጂታል ወያኔ” በማለት የሚጠራቸው እና በማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም የሚያቀነቅኑ ናቸው፡፡

እነዚህ አቀንቃኞች ‹‹የፌዴራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ላይ ጦርነት እንደሚያውጅ ማሳያ ነው›› በማለት ተቃውሞቸውን እያሰሙ ነው፡፡

የፕሬዚደንቷን ጥሪ ተከትሎ አንዳንድ አቀንቃኞች ጦርነት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በመፃፍ፣ ‹‹መአዛ አሸናፊ እና አጋሮቻቸው ከታሪክ ሊማሩ ይገባል፡፡ በታሪክ ትግራይን የውጭ ኃይል ድል አድርጓት አያውቅም፡፡ ጊዜያዊ ጥቅማችሁን አታስቀድሙ፡፡ እንቀበላለን፡፡ ረዥም ትዝታ አለን፡፡ የሰሜኑ አባላት!›› በማለት የህወሓት የማሕበራዊ መገናኛ ብዙሃን አቀንቃኙ ዳንኤል ብርሃነ ፅፏል፡፡

ሌሎች የህወሓት አቀንቃኞች በበኩላቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቷ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቁ ጠይቀዋል፡፡ በፕሬዚደንቷ ላይ የነበራቸው እምነት መሸርሸሩንም ጠቁመዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከዚህ በፊት በዐማራ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ሕግን ለማስከበር ጣልቃ ገብቶ ሕግ ማስከበሩን ዘገባው አስታውሷል፡፡

ቦርከና ዶት ኮም በዘገባው፣ “በዚህ ጣልቃ ገብነት የፌዴራሉ መንግሥት እና የክልል መንግሥታት በትብብር መሥራታቸውንም ጠቁሞ፣ ‹‹በትግራይ ግን ይህ ሲሆን አይታይም፡፡›› ብሏል

በበርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ታላላቅ ወንጀሎች የሚፈለጉት አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ብዙ ተጠርጣሪዎች በክልሉ እንዳሉ ይታመናል ያለው ዘገባው የፍርድ ቤት ትዕዛዛት ግን ምላሽ አለማግኘታቸውን አብራርቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት መዓዛ አሸናፊ አነጋጋሪ ሆዋል፡፡ የመጀመሪያዋ የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የተሾሙበት የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ ጉዳዮች “የበላይና የመጨረሻ የዳኝነት ሥልጣን” ያለው ነው።

በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መሠረት ይኸው ፍርድ ቤት “መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ሥልጣን” ተሰጥቶታል።

የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች በሚያስተላልፏቸው ውሳኔዎች ላይ ይግባኝ የሚያዳምጠውም አሁን ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው።

የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌደራል ደረጃ ያሉ ፍርድ ቤቶችን የሚያስተዳድር ነው። በዚያው ስር የሰበር ችሎት አለ። ይኸ ሰበር በአጠቃላይ በአገሪቱ ሙሉ መሠረታዊ የሕግ ስሕተት አለባቸው የሚባሉ ጉዳዮችን አይቶ የመወሰን ሥልጣን ያለው ነው።

የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት  በአገሪቱ ትልቅ ሥልጣን ካላቸው ተቋማት መካከል የፍትሕ ሥርዓቱን ለማስተካከል ብዙ ኃላፊነት የሚወስድ ዋናው ተቋም ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ መዓዛ አሸናፊን በዕጩነት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት “ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕ እንዲያረጋግጥ የተገነባው ተቋም ፍትሕን በገንዘብ የሚሸጥ፤ ለደሐ እና ለእውነት መቆም ሲገባው ፍትሕ በማጓደል ደሐ የሚያስለቅስ” ሆኗል ሲሉ ወርፈዋል። ጠቅላይ ምኒስትሩ የአገሪቱን ሕግ የመተርጎም ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጠውን የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲመሩ የተሾሙት ወይዘሮ መዓዛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሕዝብ የሚሰጧቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት ቀን ከሌት ተግተው እንደሚሰሩ ተስፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተወልደው ያደጉት የ55 አመቷ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ኃላፊነታቸውን በቅንነት፣ በታታሪነት እና ሕግና ሥርዓትን መሠረት በማድረግ ለመወጣት ቃለ-መሐላ ፈፅመው ‹‹ከዛሬ ጀምሮ የፌድራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ከሆንኩ በኋላ የመጀመሪያ የቢሮ ሥራዬ የፍርድ ቤቱ ኹኔታ ያለበትን ማጥናት ነው›› ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር። ወይዘሮዋ በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ከፍተኛውን የሥልጣን ዕርከን ሲቆናጠጡ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው።

የወይዘሮ መዓዛ ሹመት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚዎች ዘንድ አዎንታዊ አቀባበል ነበር የገጠመው፡፡ ወይዘሮ መዓዛ ያላቸውን የሥራ ልምድ እና ስኬቶቻቸውን እየጠቀሱ ትክክለኛ ውሳኔ ሲሉ አድናቆታቸውን የገለጹ በርካቶች ናቸው።

ወይዘሮ መዓዛ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር መሥራች እና የመጀመሪያዋ ዋና ዳይሬክተር ነበሩ። ማኅበሩ የኢትዮጵያ ሕግጋት ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በመወትወት፣ አነስተኛ ገቢ ላላቸው እንስቶች ሕጋዊ ድጋፍ በማቅረብ እና ሴቶችን የተመለከቱ ርዕሰ-ጉዳዮች ብሔራዊ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ እንዲሆኑ ባደረጋቸው ጥረቶች ተለይቶ ይታወቃል።

የቀድሞዋ ጠበቃ በምሥራቅ አፍሪቃ ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ-ሐብታዊ እና የጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚሰራውን ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በኃላፊነት መርተዋል። የአፍሪቃ ቻይልድ ፖሊሲ ፎረም ከፍተኛ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል። በሙያቸው በኢትዮጵያ የሕገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ኮሚሽን የአፍሪቃ የጾታ እና ማኅበራዊ ልማት ማዕከል ውስጥ ተሳትፎ አድርገዋል።

ከሕግ ሙያቸው ባሻገር ሴት ሥራ ፈጣሪዎች እና ባለሙያዎችን አሰባስበው የመጀመሪያውን የሴቶች ባንክ እንዲቋቋም አድርገዋል። ‹‹እናት›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይኸው ባንክ የኢትዮጵያ ሴቶች የሚያገኙትን የፋይናንስ አገልግሎት የማሳደግ ሕልም አለው። ወይዘሮ መዓዛ የእናት ባንክ የቦርድ ሊቀ-መንበር ሆነው አገልግለዋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com