ቡና

Views: 210
  • ገቢው ቀንሷል
  • ብራንድ ታስቦለታል
  • ቡና ላኪዎች ተሸልመዋል
  • እሴት መጨመር የሞት ሽረት ነው ተብሏል

ኢትዮጵያ ከቡና የወጪ ንግድ ታገኝ የነበረው ዓመታዊ ገቢ በማይጠበቅ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ከቡና ይገኝ የነበረው ገቢ ባለፉት አስርት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየወረደ መምጣቱን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከቡና የወጪ ንግድ ብቻ ሳይሆን፣ ከሻይ እና ቅመማ ቅመም ምርቶች የውጭ ገበያ ያገኘችው ገቢ ቅናሽ አሳይቷል።

በ2011 በጀት ዓመት ሪፖርት መሠረት፣ ወደ ውጭ የሚላከው የቡና ምርት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ15 በመቶ ቅናሽ ሊያሳይ ችሏል፡፡

የተገኘው ውጤት ላለፉት 13 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ቅናሽ ሲሆን፣ ለቅናሹ እንደ ምክንያት የተቀመጠው፣ የገበያ መቀነስ ቅሸባ (የተደራጀ የቡና ዝርፊያ)፣ የቡና ገዢ አገራት ውል የመሰረዝ እና ወደ ውጪ እሴት ጨምሮ አለመላክ በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ኢትዮጵያ በ2010 በጀት ዓመት 238 ሺህ 465 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 838 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ፤ በተጠናቀቀው የ2011 በጀት ዓመት ደግሞ 230 ሺህ 764 ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ 763 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

የኢትዮጵያን የቡና የምርት መለያ (ብራንድ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራ ከመስከረም 2012 ዓ.ም እንደሚጀመር ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያን የቡና ምርት ብራንድ በሚመለከት፣ ከአሁን በፊት የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ላይ የሚያስተዋወቅ አንድ መልክ ወይም ገጽ የለም።

የሐረር፣ ሲዳሞና ይርጋጨፌ የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቢሆንም፣ እንደ ሌሎች አገራት የኢትዮጵያን ቡና የሚያስተዋውቅ አገራዊ የቡና የምርት መለያ አለመኖሩ ችግር ሊፈጥር ችሏል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የቡና አውደ ርዕይና ጉባኤዎች ላይ ዋና የቡና ምርት መለያ ባለመኖሩ አንድ አይነት ገጽታ እንደሌለና ከዚህም አኳያ ኢትዮጵያ በሌሎች አገራት ብልጫ ሲወሰድባት ቆይቷል፡፡

ከኢትዮጵያ የቡና ምርት ጥራት ያነሰ ያላቸው አገራት ብራንዳቸውን አጉልተው በማስተዋወቅ በተሻለ ዋጋ ቡናቸውን እየሸጡ ናቸው፡፡ ሌሎች አገራት የሚያዘጋጇቸው የምርት መለያዎች በሰው አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋና የማይረሳ እንደሆነ ገልጸው ከዚህም አኳያ የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ያላትን ታሪክ ተጠቅማ የቡና ብራንድ ሊኖራት እንደሚገባ ታምኖበታል።

የኢትዮጵያን የቡና ምርት የሚያስተዋወቅ መለያ በማስፈለጉ ከአንድ ዓመት በላይ በወሰደ ጊዜ ብራንድ እንደተዘጋጀ ሲሆን፣ በጃፓን ርዕሰ መዲና ቶኪዮ ከመስከረም 1 እስከ 3 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የልዩ ጣዕም ቡና አውደ ርዕይና ጉባኤ ላይ በይፋ ማስተዋወቅ ይጀመራል።

አሁን አሁን እንደሚሰማው፣ ለኢትዮጵያ ቡና እየተዘጋጀ ያለው ብራንድ፣ በኢትዮጵያ ያለውን የቡና ታሪካዊ አመጣጥን ተከትሎ የተዘጋጀ ብራንድ እንደሆነ ታውቋል።

ከክርስቶስ ልደት በፊት 10ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ግዛቶች መካከል በከፋ ካሊድ የሚባል የፍየል እረኛ ከሚጠብቃቸው ፍየሎች መካከል አንደኛዋ የሆነ የዛፍ ፍሬን ውይም ቅጠልን በልታ እንደ መዝለልና መጨፈር አይነት ባህርይ እንዳሳየች በታሪክ ይጠቀሳል።

ካሊድ የዛን ዛፍ ቅጠል ወይም ፍሬ ቤቱ ወስዶ ሲቆላው ደስ የሚልና ልዩ ስሜት የሚሰጥ ሽታ እንደሸተተውና ከዛም በኋላ ቡናን በተለያየ መልክ መጠቀም መጀመሩ ይነገራል።

የምርት መለያው ካሊድን፣ ፍየሉን እና ቅጠሉን ወይም ፍሬውን እንደያዘና መለያው ቡናን በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ለማስተዋወቅ እንደሚረዳም እየተነገረ ነው።

ብራንዱን የማስተዋወቅ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ እንደሆነና የምርት መለያውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ጥራት ያለው ቡና ለዓለም ገበያ ማቅረብ ወሳኝ መሆኑንና ጥራት ያለው ቡና መላክ የምርት መለያውን ደረጃ እንደሚጠበቅም እምነት ተጥሏል።

የኢትዮጵያን ቡና የሚወክል የምርት መለያ መዘጋጀቱን ቡናን በማስተዋወቅ እያሽቆለቆለ የመጣውን የኤክስፖርት ቡና ምርት ገቢ ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል፡፡

ብራንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ መመዝገቡ ሌሎች አገራትና ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ቡና የራሳቸው ምርት አድርገው እንዳይጠቀሙ ስለሚያደርግ ጠቀሜታው ብዙ ነው፡፡

ብራንዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡት የሐረር፣ ሲዳሞና ይርጋጨፌ የቡና ስያሜዎችና የንግድ ምልክት በጋራ እንደሚተዋወቁም አመልክተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የቡና ምርትን በጥራት አዘጋጅተው ወደ ውጭ በመላክና በተለያዩ የቡና ንግድ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ 60 ቡና ላኪዎች፣ ሐምሌ 28 ቀን 2011 መሸለማቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ጋር በመሆን ትናንት የተጀመረው የውይይትና የእውቅና መድረክ ላይ በዕለቱ 60 ለሚሆኑ የቡና ላኪዎች የእውቅናና ሽልማት ሥነስርዓት ተካሂዷል።

በዚህም የቡና ምርትን በጥራት አዘጋጀተዉ ወደ ውጪ በመላክ ከፍተኛ ገቢ ያስገኙ አርሶ አደሮችና ሴት ባለ ሃብቶች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል። የቡና ምርትን እሴት በመጨመር ወደ ውጪ በመላክ ከፍተኛ ገቢ ያስገኙም ተሸላሚ ሆነዋል።

ቀርጫንሺ ትሬዲግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ትራኮን ትሬዲግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና አደም ከድር ሐጂ ሀሰን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ተሸልመዋል።

የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ላይ በስፋት እንድታወቅ ለማድረግ እሴት ጨምሮ መላክ ላይ ትኩረት ማድርግ እንደሚገባ እየታመነበት መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ በዘንድሮ ዓመት ለውጭ ገበያ ካቀረበችው የቡና ምርት 70 በመቶ የሚሆነው ያልታጠበቀ ጥሬ ቡና መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለውጭ ገበያ ከቀረበው 30 በመቶው ብቻ የታጠበ ቡና ሲሆን እሴት ጨምሮ በማቅረብም ብዙ አልተሰራበትም።

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ታዋቂ ስም እንዲኖረውና ጥሩ ገቢ እንዲኖረው ለማስቻል እሴት ጨምሮ መላክ ላይ ትኩረት ማድርግ እንደሚያስፈልግ የቡና ላኪዎች እምነት ነው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com