ዜና

አየር መንገዱ የካናዳ አውሮፕላን ተረከበ

Views: 266

በአፍሪካ ግዙፉ የበረራ ኩባንያ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ዳሽ 8-400 (Dash 8-400) የተሰኘ አውሮፕላን ከአምራች ኩባንያው ተረክቧል፡፡

ተቀማጭነቱን በካናዳ ኦንታሪዮ ያደረገው ዲ ሃቪላንድ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ፣ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ 25ተኛውን ዳሽ 8-400 አውሮፕላን ለማስረከብ ችሏል፡፡

በካናዳ ኦንታሪዮ በሚገኘው ዋና መ/ቤት በተደረገው ርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ፣ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ጅራ ጨምሮ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እና የዴ ሃቪላድ ኩባንያ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱም ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም እንደተናገሩ “የDash 8-400 አውሮፕላን፤ በአፍሪካ ውስጥ ያለንን ተቀባይነት ይበልጥ የሚያሳደግ እና ክልላዊ ግንኙነታችንንም በተመሳሳይ የሚያጠነክርልን ነው›› ብለዋል፡፡

ዲ ሃቪላንድ ኩባንያ ዋና የኦፕሬሽን ኦፊስር ቶድ ያንግ ኩባንያቸውን ወክለው እንደገለጹት፣ ‹‹ኩባንያችን ለገበያ ካቀረባቸው አውሮፕላኖች ውስጥ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስረከብነው 600ኛ “የDash 8-400 አውሮፕላን ነው›› ብለዋል፡፡

ከተመሰረተ 73ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በመላው ዓለም በአምስቱም አኅጉር ከ120 የሚበልጡ መዳረሻዎች ያሉት ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ መሆኑ ይታወቃል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com