“ታሪካችን መንገዳችን ነው” ሳሚ- ኦባማ

Views: 143
  • “አውስትራሊያዊያንን ለማዝናናት አቅጃሁ”

በብዙ ኢትዮጵያዊያን፣ በተለይም በውጭ አገራት በሚኖሩ እና በዩቲዩብ ተጠቃሚዎች ዘንድ የሚታወቀው አዝናኙ ‹‹ሳሚ ኦባማ››፣ የራሱን ታሪክ እና አዝናኝ ፈጠራዎችን ለአውስትራሊያ ተመልካቶች  ለማቅረብ አቅዷል፡፡

በትግራይ ክልል ዛና አካባቢ የተወለደው ሳሚ ኦባማ በአፍሮ ጸጉር ወይም ጸጉሩን ሰብስቦ ወደ ኋላ በማስያዝ እና በተለያየ ስታይሎች ይታወቃል፡፡

በአውስትራሊያ መጠሪያ ስሙ ሳሙኤል ወልደአብዝጊ፣ የኢትዮጵያ ስሙ ደግሞ መብራቶም (መብራት) ሲሆን፣ የመድረክ ስሙ ደግሞ ሳሚ- ኦባማ ነው፤ ይህ ስያሜ የተሰጠውም ጆሮው ከቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ጆሮ ጋር ስለሚመሳሰል ነው ተብሏል፡፡

በተለያዩ መድረኮች ላይ ባህላዊ ውዝዋዜ በማቅረብ ሰዎችን የሚያስደምመው ወጣቱ አርቲስት፣ ገና የ10 ዓመት ታዳጊ እያለ ነበር ከኢትዮጵያ ወደ አውስትራሊያ የሄደው፡፡

‹‹በሰዓቱ የባህል ግጭት  አጋጥሞኝ ነበር፤ እኔ ያደጉበት አካባቢ መብራት የለም፤ እዚህ አውስትራሊያ ግን ሁሉም ቦታዎች እና እያንዳንዱ ህንፃ  በመብራት የደመቀ ነው›› የሚለው ሳሚ፤ ‹‹ይህን እና ሌሎችን ነገሮችን  ሳስብም፤ ከብዶኝ  ወደ ሀገሬ ለመመለስ ፈልጌም ነበር›› ብሏል፡፡

አውስትራሊያ ታላቅ አገር ልትሆን ትችላለች፤ ብዙ ሰዎችም እዚህ አገር ለመግባት ሞተዋል፡፡ ሆኖም በመጨረሻ የሚገለጽልህ ነገር ቢኖር ሀገርን የመሰለ ነገር እንደሌለ ነው ብሏል፡፡

በትንሽ መንደር ውስጥ ማደጌ፣ ከተፈጥሮ እና ከፍቅር ጋር ያለኝን ቁርኝት ከመጨመር አልፎ፤  የቴክኖሎጂ እጥረት ባለበት ቦታ ማደጌ ደግሞ በአንፃሩ የፈጠራ አቅሜን እንዲጨምር አድርጎታል በማለት ነበር ሳሚ ኦባማ የተናገረው፡፡

በተጨማሪም፣ በአንድ መንደር ውስጥ የነበሩት ሕፃናትንም  እንዴት ማዝናናት እንዳለብኝ ጠቅሞኛል ሲል አስረድቷል፡፡

የልጅነት ትውስታውን ማጋራት ሲቀጥል፣ በልጅነታችን ጨዋታዎችን እንፈጥራለን፤ ሲያሻን እንደባለ ሱቅ፣ ሲያሻን ደግሞ እንደ ቤተሰብ፣ ወይም እንደ ሃብታም ካስፈለገም ወታደር ምን ይህ ብቻ እንደ አያት እየሆንን መጫወታችን ወደ ጥበቡ ዓለም እንድገባ አድርጎኛል ሲል አስረድቷል፡፡

ምስጋና ለባህላዊ ተወዛዋዦቻችን የሚለው ሳሚ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ጭፈራዎች ለማዳበር የዕለት-ተዕለት ልምምዶችን በማድረግ ዘወትር ብቃቱን ለማሳደግ እንደሚጥር አስታውቋል፡፡

ብዙዎች ሳሚን በቴዲ አፍሮ ‹‹ብራናዬ›› የተሰኘው የሙዚቃ ቪዲዮ ከመለቀቁ በፊት በግሉ በሰራው ቪዲዮ ያስታውሱታል፡፡

ይህ ቪዲዮም በሥራዬ እንድቀጥልበት እና ብዙ አበረታች አስተያየቶችን አግኝቼ የራሴን ቀለም እንድይዝ እድርጎኛል ሲልም አክሏል፡፡

በነገራችን ላይ ሳሚ ኦባማ ተወዛዋዥ ብቻም ሳይሆን ሞዴል፣ ተዋናይ፣ ጸሐፊና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዩቱዩብ ተመልካች ያለው ሁለገብ አርቲስት ነው፡፡

በሀገረ አውስትራሊያ የተሰራው የሄለን ካሳ ‹‹Found in a dream›› የተሰኘው የፍቅር ፊልም ላይም ከተወነባቸው ፊልሞች አንዱ ነው፡፡

እንደ ማጠቃለያም እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ታሪክ ያለን ነን፤ ታሪካችንም መንገዳችን ነው፤ ሁልጊዜ ስለ ጎሳ ብቻ ማውራት የለብንም፡፡ ባህልና ታሪካችንም ለአውስትራሊያ ዜጎች ለማሳየት ጊዜው  አሁን ነው፡፡ ይህንን አጋጣሚ መጠቀም ይኖርብናል፤ እኔ ይህን ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ ሲል ገልጿል፤ ሁለገቡ አርቲስት ሳሚ ኦባማ፡፡

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com