ዜና

የተተከሉትን ችግኞች በቀጣይ በዚህ ዓይነት ዘዴ ተንከባከቡ፡፡

Views: 11
  • ተከታታይ ክብካቤ ያስፈልጋል!

የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብሎ፣ ለችግኝ ተከላው ሆ… ፣ ብሎ የወጣው ህዝብ፤ በጣም ያስደስታል፡፡ አዎን! ያስደስታል፡፡ ነገር ግን፣ ደስታው ቀጣይና ዘላቂ እንዲሆን ክብካቤውም ቀጣይ መሆን አለበት፡፡ ለተከላው የወጣው ህዝብ፣ በየ ግሉ፣ በየ ቡድኑ፣ በየ ማኅበረሰቡ፣ በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየሰፈሩ፣ እንደገና ሰብሰብ ብሎ “እንዴት በዘላቂነት እንንከባከብ፡” ብሎ መምከር አለበት፡፡ የክትትል ፕሮግራሞችን ለሳምንት፣ ለወራት እና በየሶስት ወራት ለይቶ ማውጣት እና መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ህዝባችን ህፃን ተወልዶ ያድግ ዘንድ፣ ችግኝ ተተክሎ ይጸድቅ ዘንድ እንክብካቤ ያስፈልጋል ሲል በየ ሕዝባዊ ሥነ-ቃሉ ውስጥ አካትቶ ጠቅሶታል፤ በየትኛውም ቋንቋ ይህን ኹነት ታገኛላችሁ፡፡

ስለዚህ፡-

ሀ) ተመላልሳችሁ ችግኙን ተመልከቱ

ህፃን የወለደ ሰው፣ ራሱን ከህፃኑ እንደማያርቀው ሁሉ፤ ችግኝ የተከለ ሰውም በአግባቡ ይጸድቅ ዘንድ ራሱን ከችግኙ ብዙ ማራቅ የለበትም፡፡ ስለዚህ፣ ችግኝ ተካዮቹ በምታወጡት ፕሮግራም መሠረት፣ በየሳምንቱ በየተራ ሄዳችሁ ተመልከቱት፡፡ በምልከታችሁ ውስጥ ለምልምው የሚገኙትን እና የተጎዱትን ለይታችሁ መዝግቡ፡፡ የተጎዱት ማለት የተነቀሉ፣ የደረቁ፣ አናታቸው የተበሉ፣ በሽታ ያጠቃቸው፡ እና የመሳሰሉትን የመርዳትና የማከም እድል ይኖረናል፡፡

ለ) በአካባቢው ላሉት ሰዎች አደራ ስጧቸው

ህፃን የወለደ ሰው፣ ከህፃኑ ራቅ ብሎ መሄድ ግድ ሲለው፤ የኔ ላለው ሰው እና ማኅበረሰብ ኃላፊነት በአደራ ይሰጣል፡፡ አደራ ተቀባዩ ችግኙን የመንከባከብ ኃላፊነት ልክ እንደ ባለቤቱ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ችግኞቹ በተተከሉበት አካባቢ የሚኖሩ ቤተሰቦችን፣ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችን ጭምር “አደራ፣ ጠብቁ ብሎ መስጠት ብልህነት ነው፡፡  

ሐ) ጠባቂ ሰው ቅጠሩ

አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ በአካባቢው የሚኖሩ አደራ የተሰጣቸውን ሰዎች የሚያግዙ ጠበቂ ሰዎች መቅጠር ወጪው ይህን ያህል ችግኞቹን ለተከለ ማኅበረሰብ የሚከብድ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ችግኞቹን መንከባከብ ሥራው የሆነ ሰው መኖሩ፣ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡

መ) የእሾህ እንጨት

ህፃን የወለደ ሰው፣ ህፃኑ እንዳይወድቅ፣ እናቱን ጨምሮ ካለማወቅ በአካላዊ ንክኪ እንዳይጎዳው ዙሪያውን ከለላ እንደሚደረገው ሁሉ፤ እንዲጸድቅ የሚፈለግ ችግኝም እንዲሁ እንክብካቤ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ፣ እነሆ ጎንበስ ቀና ብላችሁ የተከላችሁትን ችግኝ፣ ዝም ብላችሁ ትታችሁ ከተመለሳችሁ፤ የቤት እንስሳት ወይም የዱር እንስሳት አናት-አናቱን ይቀነጥቡታል፡፡ ስለዚህ፣ በችግኞቹ ዙሪያ የእሾህ እንጨት (ጭራሮ) ጣል-ጣል አድርጉ፤ ወይም በዙሪያው ትከሉ፡፡ ይህ የችግኞቹ ሥር መሬት ቆንጥጦ እንዲይዝ  ይረዳዋል፡፡

ሠ) ጊዜያዊ እና ቋሚ አጥር አብጁ

1ኛ/ ህፃን እንዳይጎዳ በልብስ፣ በፎጣ፣ በምን እንደምንከልለው ሁሉ፤ ለችግኝም ለጊዜው እስኪያድግ የሚረዳው አቅም በፈቀደ መጠን በእንጨት፣ በቅጠል፣ በብረት፣ በሽቦ፣ በቆርቆሮ ወዘተ አጥር ማጠር አስፈላጊ ነው፡፡

2ኛ/ እንደ አካባቢው ሁኔታ፣ ለምሳሌ ከተማ፣ ገጠር፣ መንገድ ዳርቻ፣ ወይም ደን፣ ተለይቶ ከአጥሩ

በውስጥ በኩል ወይም በውጪ በኩል  በቋሚነት አጥር የሚሆኑ ተክሎችን ትከሉ፡፡

ከዓመታት በኋላ አድጎ እራሱ ቋሚ አጥር ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ደን ውስጥ ቋሚ

የተክሎች አጥር ሊሆኑ የሚችሉት፣ ቆንጥር፣ ሰባንሳ፣ የፈረንጅ ኮሽም፣ ቁልቋል በለስ፣ ቁልቋል ባለወተት፣ ቅንጭብ፣ ቀጋ እና የመሳሳሰሉት ናቸው፡፡ በከተሞች ውስጥ እና መንገድ ዳርቻ ቋሚ አጥር የሚሆኑት ደግሞ በዚህ ዘመን በብዛት በግል ችግኝ ጣቢያ በብዛት ይገኛሉ፡፡

ረ) በጎደለ ሙሉ

አይበለውና ህፃን ከማደጉ በፊት ከተቀጨ፣ ወላጆች ሌላ ልጅ እንደሚወልዱት ሁሉ፤ በተጎዱቱ ችግኞች ጉድጓድ ውስጥ ሌላ ችግኝ ትከሉ፡፡ ሕይወት እንደዛ ነው፤ መተካካት የሕይወት መርህ ነው፡፡

በዚህ ላይ፡-

1ኛ/ ችግኝ ዘወትር ከችግኝ ጣቢያ ብቻ ይገኛል ብላችሁ አታስቡ፡፡

  • በየጓሮአችን፣
  • በየመንገዱ ዳርቻ፣
  • በየጥሻው፣
  • በየአጥር ጥጋጥግ፣
  • በሌሎች ዛፍ ጥላ ሥር እና
  • ወደፊት ሊያደጉ በማይችሉበት ቦታ ሁሉ

ችግኞቹ በቅለው ቀን ወይም እድል የሚጠብቁ አሉ፡፡ ይህ ቦታ ቋሚ ቦታ ሊሆናቸው አይችልም፡፡ ስለዚህ፣ ለእነዚህ ችግኞች እድል እንስጣቸው፡፡ ቢቻል ከነአፈሩ መንቀል እና ወደ ቦታው መውሰድ ነው፡፡ ከነአፈሩም ባይሆን በተነቀሉበት እለት ከተተከሉ ይይዛሉ፡፡ ወይም እንደተነቀሉ በከረጢት ላስቲክ ውስጥ ማድረግ እና አፈር መሙላት ነው፡፡ እስኪተከሉ ውሃ ማጠጣት እና መንከባከብ ነው፡፡

ለምሳሌ፡- አዲስ አበባን እንውሰድ፣ በብዙ ቦታ ላይ ችግኝ አለ፡፡ እስቲ በትኩረት ተመልከቱ፣ የግራዋ፣ ብርብራ፣ ብሳና፣ ዋንዛ፣ ድግጣ፣ ኮሽም፣ ጀሞ፣ ዘንባባ፣ አንፋር፣ ሸንበቆ፣ ሸውሸዌ፣ አመራሮ፣ ስንት እና ስንት ዓይነት አሉላችሁ መሰላችሁ፡፡ በሌሎች ከተሞች እና ገጠርም ብዙ ዓይንት ችግኝን ማሰባሰብ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አብሽር የአካባቢውን አረጋውያን ምክር ጠይቁ፡፡ ይነግሯችኋል፡፡

2ኛ) የግድ የደን ዛፍ ብለን የለመድነውን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም ዘሮች እና ችግኞች ወደ ዱር ወይም ደን ቦታ ወስደን እንትከል፡፡ ለምሳሌ የፍራፍሬ ዛፎችን እንውሰድ፣ የዘይቱን፣ ካዛሚሮ፣ አምበሾክ፣ አቡካዶ፣ ማንጎ፣ ጊሽጣ፣ ወሽመላ እና የመሳሰሉትን፡፡ በሌላ በኩል ጌሾን ደግሞ አስቡት፡፡ ጌሾ በቀላሉ ደን ውስጥ ሊበቅል ይችላል፡፡ እንዲያውም በቀላሉ በዱር እንስሳት አይበላም፡፡

3ኛ)  በበጋ ወራት ቁርጥራጫቸው የሚተከሉ ብዙ የዛፍ እና የቁጥቋጦ ዓይነታት አሉላችሁ፡፡ እነዚህ ተክሎች ክረምት ሲተከሉ አይወዱም፡፡ በጋ ነው የሚወዱት፤ እንጨቱ ተቆርጦ ከተተከለ በኋላ አፈር ውስጥ ሥር ማበጀት ይጀምራሉ፡፡ ቀስ ብለው ቅጠል ያቆጠቁጣሉ፡፡ ይህ ዘዴ ቀላል እና ጊዜ ቆጣቢ ነው፡፡ ከህዳር እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ቁርጥራጭ ይዛችሁ ወደ ተከላ ሂዱ፡፡ ለምሳሌ፡-

የተክሉ ስም የሚተከለው ክፍል የሚቆረጥበት መጠን
እንጆሪ ጠንካራ ዘንግ እንጨቱን አንድ ሜትር ያህል
ኮርች ጠንካራ ዘንግ እንጨቱን አንድ ሜትር ያህል
ችብሃ ጠንካራ ዘንግ እንጨቱን አንድ ሜትር ያህል
የጎማ ዛፍ የአናቱን ዝንጣፊ ግማሽ ሜትር ያህል
ወይን (ወይን ሐረግ) ጠንካራ ሐረግ እንጨት ግማሽ ሜትር ያህል
ነጭ አሃይ ለጋ ወይንም ጠንካራ ዘንግ ግማሽ ሜትር ያህል
ዕፀ ጳጦስ በጎን ያቆጠቆጡ ብቃዮችን ከግማሽ እስከ አንድ ሜትር
ቁልቋል በለስ ወፍራም ቅጠል መሳዩ እያንዳንዱ ቅጠል መሳይ
ቁልቋል ባለወተት ግንድ መሳይ እንጨቱ ከግማሽ እስከ አንድ ሜትር
ቅንጭብ ያሉት ዘንጎች በማንኛውም መጠን
ሰንሰል (ስሚዛ) ዘንግ እንጨቱ በማንኛውም መጠን
ምስርች ዘንግ እንጨቱን ከግማሽ እስከ አንድ ሜትር
አዛምር የሥሩ ቁርጥራጭ እስከ ግማሽ ሜትር
ኦሌንደር ዘንግ እንጨቱ ተቆርጦ እስከ ግማሽ ሜትር
በተለይ በቆላና ወይናደጋ
ቻያ (ጎመን ዛፍ) የእንጨት ቁርጥራጭ ከግማሽ እስከ አንድ ሜትር
ከርቤ፣አንቋ፣አበከድ የእንጨት ቁርጥራጭ እስከ አንድ ሜትር
ካሳቫ (እንጨት ቦዬ) የእንጨት ቁርጥራጭ ከአንድ ሜትር በላይ

 

አላል ያክል (ትንሽ ጭማሪ)፡-

የተለመደ ጥያቄ አለ፡፡ “ይሄ አይታወቅም” ይሉት ነገር፡፡ ካለመጠየቅ እንጂ፣ የማይታወቅ ዛፍ የለም፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ችብሃ ከሜክሲኮ ወደ ተክለሃይማኖት ስትሄዱ፣ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ (በምዕራቡ በኩል) ከመንገድ ዳር ያሉት ዛፎች ናቸው፡፡ ኮርች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አራት ኪሎ በር፤ ከውጪ አጥር ያሉት እሾሃም ዛፎች ናቸው፡፡ ዕፀ ጳጦስ ኢኖቬሽን ሚ/ር በር ላይ ተዥርጎ ይገኛል፡፡

ማጠቃለያ ለመንገር፡-

ዛፍ ተከላው እና ክብካቤው ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት፡፡ ሰዉ በየጊዜው፣ በየዕረፍት ቀኑ፣ ወዘተ ወደ ደን ቦታ፣ ወደ ተከለበት ዛፎች ቦታ ቢሄድ እጅግ መልካም ነው፡፡  ህፃናቱ በአግባቡ ይደጉ፤ ችግኙም ይጸደቅ ይብቀል፤ ሕይወት ለምለም አረንጓዴ ሆና ትቀጥል፡፡ ለመጪዎቹ ትውልዶች ለም-ለሙን ምድር እናስረክብ!!!

ቸር ሰንብቱ፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com