እንሰት (ጉና-ጉና) – (ክፍል -፪-)

Views: 422
 • ያልተዘመረለት ኢትዮጵያዊ ሲሳይ

በዚህ ዠርጋጋ ቅጠል ባለው የእንሰት (ጉና-ጉና) ተክል ውስጥ፡- ለምግብነት የሚውለው ቆጮ አለ፤ ቡላ አለ፤ አሚቾ አለ፤ በአጠቃላይ የእንሰት ተክል ውስጥ ከፍተኛ ኃይልና ሙቀት ሰጪ ንጥረ ነገር አለ፡፡ በዚህ ላይ ለጤና እጅግ ጠቃሚና ተስማሚ ነው፡፡ ቆጮን የተመገበ፣ ቡላ የበላ እጅግ ተጠቀመ፡፡

(ለምግብነት የተዘጋጀ ቆጮ- ነብሴ)

መግቢያ

ስለ እንሰት (ጉና-ጉና) ተክል ልማት እና ጠቀሜታ በክፍል አንድ ላይ ገለፃ ተሰጥቶ ነበር፡፡ አሁን በዚህ በክፍል ሁለት ላይ ስለ ምግብ አሠራሩ ደግሞ እንቀጥላለን፡፡ የእንሰት ምርት ውጤት ለተለያየ የምግብ ዝግጅት ይውላል፡፡ ማንኛውንም ምግብ ለመሥራት ቀድሞውኑ በባሕላዊ አሠራር እንሰቱ ወደ ቡላ እና ቆጮ መለወጥ አለበት፡፡ ከዚያም በሚፈልጉት አሠራር ምግቡ ይዘጋጃል፡፡ ከዚህም ሌላ፣ እንሰት የቤት እንስሳት እና የዱር እንስሳት መኖ እና ለሰው መድኃኒት ጭምር ነው፡፡

 1. የቡላ እና የቆጮ ዝግጅት ሂደት

1.1 እንሰቱን መንቀል እና መፋቅ

ለምርት የደረሰው የእንሰት ተክል አሠራሩን በሚያውቁ ሙያተኞች ብዙ የአሠራር ሂደት አልፎ ወደ ቡላ እና ቆጮ ይቀየራል፡፡  በዕለቱም ቀድሞ የሚፋቅበት ቦታ ተደላድሎ በእንሰት ቅጠል ተሸፍኖ ይዘጋጃል፡፡ ሊፋቅ የደረሰው እንሰት ዙሪያው ተቆፋሮ ከነ  አሚቾው (ሥሩ) ይነቀላል፡፡ ከግንድ መሳዩ በላይ ወደ አናቱ ያለው ከነቅጠሉ ተቀርጦ ይቀራል፡፡ የአናቱ ክፍል ለእንስሳት መኖ እንጂ፣ ለቆጮ አይሆንም፡፡ ዋናው ግንድ መሳዩ ለቆጮ ዝግጅት የሚሆነው እስከ ሁለት ሜትር ከሆነ ሁለት ቦታ ይቆረጣል፡፡ ከዚህ ከግንዱ ላይ ያለው የደረቀው ሆፊቾ እና ወፋራም አረንጓዴው እየተላጠ ይነሣለታል፡፡

(ግንድ መሳዩ የእንሰት ክፍል)

የውስጡ ነጩ እየተላጠ ይደረደራል፡፡  ይህም ሁለት ሦስት ቦታ ይሸነሸናል፡፡ እያንዳንዱ በጣውላ መሳይ እንጨት ላይ ታስሮ በተሰነጠቀ ቀርከሃ እንጨት ይፋቃል፡፡ ቃጫው እስኪቀር ድረስ ይፋቃል፡፡ የተፋቀው ተሰብስቦ ይከማቻል፡፡ ቃጫው ለብቻ ለሌላ ሥራ ይቀመጣል፡፡

አሚቾው (ሥሩ) ከላዩ በቢለዋ ወይም በሌላ ብረት የማይፈለገው ይነሳነታል፡፡ ከዚያም ለዚሁ ሥራ ተብሎ በተዘጋጀ  የወይራ እንጨት ይከተከታል፡፡ የተፋቀው እና የተከተከተው ይደባለቃል፡፡

ማሳሰቢያ፡- ይህ ገለፃ ሁኔታውን ለማስረዳት ያህል ነው፡፡ እንጂማ፡-

ሀ) እንደየባሕሉ በየአካባቢው ለእንሰት ሥራ መከወኛ የተለያዩ የእጅ መሣሪያዎ  አሉ፡፡ ማጣቀሻ አንድ

ለ) በዚህ ዘመን የተሻሻሉ የሴቶችን የሥራ ጫና የሚቀንሱ እና የምርቱን ብቃት የሚያሻሽሉ መከወኛ

መሣሪያዎች ይገኛሉ፡፡

1.2 ቡላ ማምረት፡-

ቡላ ለማምረት ከሁለቱም ድብልቅ በዕለቱ ይጨመቅና ወተት የመሰለ ፈሳሽ ምርት ይጠራቀማል፡፡ ወተት መሣዩ ፈሣሽ በወንፊት ተጠሎ፣ እንዲረጋ እና እንዲጠል ይቀመጣል፡፡ በማግስቱ የጥላዩ ውሃ ከላይ፣ ንፁህ ቡላ ከሥር ይሆናል፡፡ ውሃው ከላዩ ይፈሳል፡፡ ቀጥሎም ቡላው ለአንድ ሣምንት በሆፊቾ በጣም ተሸፍኖ ታስሮ በጉድጓድ ውስጥ ይቀበራል፡፡ ከዚያም ከወጣ በኋላ ቡላው እንዳይነፍስበት በመጠን፣ በመጠን ተደርጎ በእንሰት ቅጠል እና በሆፊቾ ይታሰራል፡፡ እንደ እንሰቱ ዝርያ ዓይነት ቡላ ብዙ የሚወጣው እና የማይወጣው አለ፡፡

ቡላው ከተዘጋጀ በኋላ ለቤት ፍጆታ ወይም ለገበያ ይቀርባል፡፡ ወደ ቤቱ ገዝቶ ያመጣው ሰው ጥሩ ግጣም ባለው ዕቃ ውስጥ ከላይ ውሃ ጨምሮ ማስቀመጥ እና በየጊዜው ውሃውን በመቀየር ማቆየት ይችላል፡፡

ቡላውን ለረዥም ጊዜ ለማቆየት እንዲቻል በፀሐይ ሙቀት ማድረቅ እና በኮረት መልክ ማስቀመጥ ወይም ማስፈጨት እና በዱቄት መልክ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

(ምስል፡- እርጥቡ ቡላ ከቅጠሉ እንደተፈታ)

መቸም ቢሆን፣ ቡላ በውድ ዋጋ የሚገዛ ምግብ ነው፡፡ በዚህ ዘመን በእንሰት ቅጠል የተጠቀለለ እርጥብ ቡላ በተለያየ መጠን በገበያ ላይ ይገኛል፡፡ አምራች ከሆኑበት አካባቢ ርቆ አንድ ኪሎ እርጥብ ቡላ ከ 6ዐ እስከ 1ዐዐ ብር ሊሆን ይችላል፡፡  ደርቆ የተፈጨ ቡላም በሱፐር ማርኬት እና በሱቁ ውስጥ ይገኛል፡፡ አንድ ኪሎ የቡላ ዱቄት ከ 8ዐ እስከ 12ዐ ብር ሊሆን ይችላል፡፡

(የደረቀ ቡላ በኮረት መልክ)

ሆኖም፣ በአንዳንድ አካባቢ ለምሳሌ አሰላ እና በዙሪያው ያሉት ብዙ ጊዜ “ቡላ የተጨመቀለት ቆጮ ጥራቱ ይቀንሳል” ይላሉ፡፡ የቆጮውን ጥራት ለማሻሻል ሲፈለግ ቡላው ሳይጨመቅ ዝም ተብሎ በአንድነት ቆጮ ይዘጋጃል፡፡

1.3 ቆጮ ማምረት

እንደየአካባቢው፣ እንደ ባሕሉ፣ እንደተፈለገበት ጉዳይ፣ ቆጮ ለማምረት ከጥቂት ሣምንታት እስከ ወራት ይፈጃል፡፡ የተፋቀው እንሰት እና የተከተከተው አሚቾ በዚያው ሥራው በተጀመረበት ቀን ተደባላልቆ እንዲብላላ በጉድጓድ ወይም በአንድ ቦታ ተሸፍኖ ለሣምንታት ይቆያል፡፡ በየጊዜው፣ በተደጋጋሚ እያገላበጡት ያሹታል፡፡

በዚህ ጊዜም የሽታውን ክብደት ለመቀነስ ከተለያየ ቅመም ጋር ይታሻል፡፡  በዚህ ሂደት ተብላልቶ፣ በስሎ ሊጥ ሲሆን እንደገና ከቃጫው እንዲለይ ይቀጠቀጣል፡፡ ይህ የበሰለው ሊጥ Ý ይባላል፡፡ ይህ ሥራ እንደየባሕሉ፣ እንደ እንሰቱ ዓይነት በአጭር ጊዜ በሦስት ሣምንት ይደርሣል፤  ወይም ከ 2 እስከ  4 ወራት ቆይቶ ይደርሣል፡፡ ማጣቀሻ አንድ

በዝግጅት ሂደቱ እንደቆይታው ጊዜ ቃናው እና ጣዕሙ ይለያያል፡፡ ይህ እንደባለቤቱ፣ እንደባለሙያው ወይም ገበያ ላይ እንደሚፈለገው ዓይነት ይወሰናል፡፡ በሰለ ወይም ደረሰ ከተባለ በኋላ ቆጮው በሌላ ጉድጓድ ውስጥ በላስቲክ ወይም በእንሰት ሆፊቾ ተጠቅልሎ ይከተታል፡፡ ለወራት ወይም ለዓመታት ማቆየት ይቻላል፡፡

የቆጮ ሊጡ ከጉድጓድ ውጪም ቢሆን በላስቲክ ወይም በሆፊቾ ተሸፍኖ ታስሮ  እንዳይነፍስበት ታሽጐ ይቀመጣል፡፡ በደንብ በማስቀመጥ ሊጥ እንደሆነ ሣይበላሽ ለብዙ ወራት ማቆየት እና መጠቀም ይችላል፡፡ ለምሳሌ ቀጥሎ በምታዩት ምሥል ዓይነት፡-

(በሆፍቾ የታሰረ የቆጮ ሊጥ)

በሌላም ዘዴ፣ ተብላልቶ ከወጣለት በኋላ የቆጮ ሊጡ በፀሐይ እንዲደርቅ ይሰጣል፡፡  ኮረቱን (ዱቄቱን) በንጽህና ማስቀመጥ እና ለሚፈለገው የምግብ አሠራር ማዋል ይቻላል፡፡

 1. የቡላ እና የቆጮ ምግብ አሠራር (ጥቂት ምሳሌ)

       2.1 የቆጮ ቂጣ 

ከእንሰት ቆጮ የባሕል ምግቦች ውስጥ የቆጮ ቂጣ እጅግ ታዋቂ ነው፡፡ ከቤተሰብ ደረጃ አልፎ በብዙ ድግስ ላይ የምግብ አጃቢ ነው፡፡ እሱንም እነ አይብ እና ክትፎ ያጅቡታል፡፡ ቆጮ ቂጣው ብቻውን በወፍራሙ ወይም ትንሽ የገብስ ዱቄት ተደርጎበት ይጋገራል፡፡ ከበርበሬ ጋር አሽቶ በመጋገር ቀላ ብሎ ይበስላል፡፡ ከሥር ያለው ምስል ጥሩ ምሳሌ ነው፡-

(የቆጮ ቂጣ ተጋግሮ የተቆረሰ)

2.2 የቆጮ ፍርፍር

የቆጮ ሊጥ በብረት ምጣድ ላይ፣ በሸክላ ምጣድ ላይ ወይም በመጥበሻ ላይ በፍርፍር መልክ ይበስላል፡፡ በስሎ የተዘጋጀውን የቆጮ ፍርፍር በጨው፣ በርበሬ፣ በቅቤ፣ በኮረሪማ፣ በዘይት እና በመሳሰሉት ማጣፈጥ እና ከሚፈልጉት ማባያ ጋር ማቅረብ ይቻላል፡፡

(የቆጮ ፍርፍር)

2.3 የቡላ ምግቦች፡-

 • ከቡላ ብቻ ወይም ከሌላ ዱቄት ጋር መጥኖ በጣም ጥሩ አጥሚት ይዘጋጃል፡፡
 • በውሃ፣ ወይም በወተት በቡላ ጥሩ ገንፎ ይሠራበታል፡፡
 • ቀድሞ ከበሰለ ቅንጬ ጋር ቡላን በመሥራት ጥሩ ምግብ ይዘጋጃል፡፡
 • ቡላን እንደ አብሲት በማዘጋጀት ለእንጀራ ማዋል ይቻላል፡፡

2.4 ቆጮ  ዳቦ

እንሰት ዋና ምግብ በሆነባቸው አካባቢ ሁሉ፣ የቆጮ ዳቦ ይጋገራል፡፡ ብቻውን ወይም ከገብስ ወይም ከስንዴ ጋር፡፡

2.5 ቆጮ  ለእንጀራ

ቆጮ ከጤፍ ወይም ከሌሎች የእህል ዓይነት ጋር ተመጥኖ እንጀራ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከተዘጋጀው የጤፍ ዱቄት ላይ 2 ኪሎ ያህል ይቦካል፡፡ የሚጋገር ዕለት ከዱቄቱ ወይም ከቡኮው ላይ ተቀንሶ አብሲት ይጣላል፡፡ አብሲቱ ሲቀዘቅዝ ከ ግማሽ ኪሎ የቆጮ ሊጥ ጋር በአንድነት ከቡኮው ጋር ታሽቶ ይቀጥናል፡፡ ሊጡ በደንብ ኩፍ ሲል በማጥለያ ወይም በወንፊት ይጠለልና ቃጫ እና ጓጐላ ካለው ተለይቶ  ሊጡ እንጀራ ይጋገራል፡፡ ማጣቀሻ ሁለት

(ከዚህም ሌላ በተለያየ ዘዴ ደረቅ ቆጮን ከእህል ጋር መጥኖ በማደባለቅ እና በማስፈጨት እንጀራ መጋገር ይቻላል፡፡)

ቆጮ ለእንጀራ ልዩ ጠቀሜታው!

 • እንጀራው ይለሰልሳል፣
 • ሊጡ አብሲት ያነሳል፤ ውሃም ያነሳል፤
 • ዐይኑ በጣም ይፈካል፣ ሰበከቱ ያምራል፣
 • ቶሎ አይሻግትም፤
 • እንጀራው ሲጋገር ያስቸገረ እህል ቆጮ ሲደረግበት ያምራል፤
 • ከምጣድ ጋር ተስማሚ ነው፤

2.6 የእንሰት ንጥረ ምግብ ይዘት  ማጣቀሻ ሶስት

በመቶ ግራም የእንሰት ውጤት እና ጤፍ ውስጥ ያለ የንጥረ ምግብ ይዘት

እንሰት የንጥረ ምግብ ጉድለቱ ኘሮቲን እና ብረት ነው፡፡ ስለዚህ ከሌላ እህል ወይም አትክልት ጋር መመገብ የተሻለ ይሆናል፡፡ እንዲያውም እንሰት ቃጫ ያለው ስለሆነ ይህ ደግሞ ለምግብ ስልቀጣ ይረዳል፡፡

 1. እንሰት ለእንስሳት መኖ

የእንሰት ተክል ከሁለት ዓመት ጀምሮ በተለያየ መንገድ ለእንስሳት መኖ ይውላል፡፡ ዘንግ መሳይ አካሉ (ከታች ባለው ምስል እንደተመለከተው)፣ አሚቾው፣ ቆጮ ሲፋቅ ተረፈ ምርቱ እና የመሳሰሉት፡፡ ጭሮ አደግ ዶሮዎች ማንም ውሃ ባይሰጣቸው ግንዱን እየከተከቱ ውሃ ያገኛሉ፡፡

እንሰት ሌላው ቀርቶ ለዱር እንስሳት የምግብ ምንጭ ነው፡፡

(ለመኖ የተዘጋጀው  የእንሰት ዘንግ)

 እንሰት ለሰው መድኃኒት ማጣቀሻ አንድ

አንዳንዱ ዓይነት እንሰት ለሰው መድኃኒት ነው፡፡ ለምሳሌ፡-

 • ቅብናር የተባለውን አሚቾውን ሲመገቡት፣ ለታመመ አካል አለስላሽ እና በእጅጉም መግል ሠሪ ነው፡፡ ሆኖም፣ በመጠኑ መመገብ ያስፈልጋል፡፡ መምገሉ እንዳቋረጠም አስታራን ይበሏል፡፡
 • አስታራ አረጋግቶ አክሞ ያዳነውን፣ ቁስሉን ለማድረቅ ጓርየ ይበሉበታል፡፡
 • ጓርየ ስብራትን ይጠግናል፤ ለውልቃት ግን አይፈለግም፤
 • ቡላ ለጨጓራ ታማሚ ጥሩ ምግብ ነው፡፡

ማጠቃለያ

እንሰት  የምግብ አሠራሩ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ እንደየባሕሉ ማጥናት የጠቅማል፡፡ ለማንኛውም ስለ እንሰት በአቶ ዓለማየሁ ነሪ ውርጋሶ የተዘጋጀው፣ ኧሰት ፫ኛ መጽሐፍ፣ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ መጽሐፉን ማንበብ ስለ እንሰት ማወቅ ብቻ ሣይሆን ሌሎችንም ለማስተማር የሚተርፍ እውቀት ያስገኛል! ለምርምርም ሆነ  ለስርፀት በእንሰት ላይ ሥራ የሚጀምሩቱ ይህንን መጽሐፍ ማንበብ ይበጃቸዋል፡፡

                                                                                                                       

የመረጃ ምንጭ፡

 1. ዓለማየሁ ነሪ ውርጋሶ፣ 1998 ዓ፣ም፤ ኢትዮጵያዊ ሲሳይ፣ ኧሰት  ፫ኛ መጽሐፍ፣አዲስ አበባ
 2. በቀለች ቶላ፣ 2ዐዐ4 ዓ.ም በዐይነት እንጀራ፣ ለምለም እንጀራ ከብዝሀ ሰብሎች፤

ፋልከን ማተሚያ ድርጅት፣ አዲስ አበባ፡

 1. የኢትዮጵያ የጤናና ስነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት፡

       EHNRI– FOOD COMPOSITION TABLE FOR USE IN ETHIOPIA:  PART III, 1997  PART IV, 1998

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com