ሕይወት ግዛቷ ሲጣስ

Views: 225

የሕይወት ግዛቷ የት ሆኖ ነው የሚጣሠው?! የሚል ቆፍጣና ጠርጣሪ ልቦና ያለው ሰው፣ ይቺን በመጠን አነስ ያለች መጽሐፍ እንዲያነብ ይመከራል:: ለማንበብ መነሸጥ እና መጽሐፉ ባነሳው ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የተወሰነ ሃሳብ ማንሳት ደግሞ፣ የዚህ ጽሑፍ ዐብይ ዓላማ ነው::

ማሳለፍ እንደ ሞት ነው፣

አንድም ሰው አይቀረው፤

ሕይወት ፣ ሞት እና ራስን ማጥፋት

ራስን ማጥፋት (Suicide) የሠው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ በሚባል መልኩ የቆየ እና የከረመ የኑሮው አንዱ መገለጫ ተደርጎ የሚቆጠር ጥንታዊ ድርጊት እንደሆነ፣ የታሪክ መዛግብት ይመሠክራሉ:: ራስን ማጥፋት በትርጓሜ ደረጃ ለመረዳት ያህል ከተረጎምነው አንድ ሠው የራሱን ሕይወት ሲያጠፋ ነው ማለት እንችላለን:: ይህ ትርጓሜ ግን ውስብስብ ከሆነው ራስን የማጥፋት ዝንባሌ እና ድርጊት አናጻር ካየነው ብዙም ገዢ ላይሆን ይችላል::

የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ንጉሡ አጥናፉ በግል፣ ማኅበረሰባዊ በሆነ ዕይታቸው እና ገጠመኞቻቸው ተነስተው ይህን መጽሐፍ ሊጽፉ እንደተነሱ የመጽሐፉ መግቢያ ላይ ይነግሩናል:: በዋነኝነትም ሠዎች ራሳቸውን ለምን እንደሚያጠፉ ከማየታችን በፊት ያ የሚጠፋው ሕይወት ምንድን ነው? ብለው ያጠይቃሉ:: (ገጽ 15)

ጥያቄው በራሱ ከባድ እና ውስብስብ መሆኑን የሚነግሩን ደራሲው፣ የበለጠ ጥያቄውን የሚያወሳስበው ደግሞ ሠዎች ይህን ጥያቄ ብዙ ግዜ የሚጠይቁት በሚጨነቁበት ወይም እሴቶቻቸው በሚጣሱበት የሕይወት አጋጣሚ ላይ በመሆኑ ነው:: የፍልስፍና ተማሪ እና ተመራማሪ ያልሆኑ ሠዎች እምብዛም እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው አለመጠየቃቸውን ያስተውሏል ይሉናል ደራሲው::

“ሕይወት እንደ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ነው:: ጥቂቶች ሜዳሊያ ለማግኘት ጡንቻቸውን የሚያጠነክሩበት፤ ሌሎች ለታዳሚው የተለያዩ ነገሮችን በመሸጥ ትርፍ የሚያገኙበት እና ብዙዎች ደግሞ እንዴት እንደሚከናወን ለማየት የሚመጡበት ነው:: ”

ፓይታጎረስ

የሕይወትን ትርጉም ለመረዳት፤ ትርጉምን ራሱ መረዳት አለብን የሚሉን ደራሲው ሄደን- ሄደን ህይወትን መተርጎም ላይ እንቸገራለን ይሉናል:: ይህ ደግሞ የሚሆነው በተለያየ ምክንያት ነው፤ አንደኛው ስለ አንድ ነገር ትርጉም (ምልክት፣ ቃል) ስንሰጥ፤ ያ ትርጓሜ ከራሱ አልፎ ወደ ሌላ ነገር ማመልከቱ ነው:: በዚህ ሃሳብ ከተስማማን ትርጉሙን እንደ አመላካች የመውሰድ ችግር ላይ እንወድቃለንና ጉዳዩን የመተርጎም አቅም አይኖረንም ወይም ያንሰናል::

ሠዎች ስለ ሕይወት ትርጉም ሲጠየቁ በአዕምሮአቸው ውስጥ ከነሱ ሕይወት ውጭ ወደ ሆነ ነገር ያመለክታሉ:: ይህም ጥያቄውን ከመመለስ ወደ ፊት ማስተላለፍ ላይ መውደቅን ያስከትላል፤ እንዲህ ካሉት በሕይወት ትርጓሜ ዙሪያ ከሚሰጡ ትርጓሜዎች ወይም መረዳቶች አራቱን ያህል መጥቀስ ተገቢ ነው ብለው ደራሲው እነዚህን ይጠቅሳሉ :-

  • ልጆች
  • እግዚአብሔር
  • ከሕይወት በኋላ ያለው ሕይወትና
  • ሕይወት ትርጉም የለውም ብለው የሚደመድሙ ናችው

ይህ ማመልከት እንዳለ ሆኖ ለአንዳንዶች፡-

ሕይወት ጀብድ ነው

ሕይወት ተልዕኮ ነው

ሕይወት ታሪክ ነው

ሕይወት ጥበብ ነው

ሕይወት ፍላጎት ነው ወዘተ… (ገጽ 23)

ሕይወት ለሁላችን እያመለከተን እንዲሁም በራሱ ከነ ገደቡ እየተረጎምነው ስንሄድ ከላይ የጠቀስናቸውን ይመስላሉ እንደ ደራሲው አረዳድ::

ሞትስ ምንድን ነው?

ሕይወት ለሠው ልጅ ያለፈባቸው ነገሮች እንደሆኑና መጨረሻውም ቅርብ ይሁን እሩቅ በእርግጠኝነት ወደ ፍጻሜው እየተጠጋ መሆኑን የሚገነዘብበት ነው:: በዚህም ባለበት መቆም ወይም ወደ ኋላ መመለስ አለመቻሉና ወደ ፊት አንድ መዳረሻ ብቻ ሊኖረው የሚችል መሆኑን እሱም የራሱ የመኖር ሕልውና ማብቂያ እንደሆነ ይረዳል :: (ገጽ 24) ማብቂያው ነው ሞት እንደማለት::

ሠዎች ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ?

ጥፋት፣ ጥላቻና ጸብ

ሠዎች እንግዳ ለሆኑ ሠዎች የሚሠማቸው ያልተደበቀ ጥላቻ አብዛኛውን ግዜ በወዳጆች መካከል ሳይቀር እንኳ የሚቀሰቅሰው የጥላቻ ድርጊት፣ ለጥላቻ ዝግጁ መሆን፤ ሁሉም ምንጫቸው የማይታወቅ ነው:: እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችን ለመግለጽ የሚገፋፋ ባህሪ ጸብ ጫሪነት ነው:: (ገጽ 32) በተፈጠሮአችን ያሉ ዝንባሌዎቻችን ናቸው እንደማለት::

ተስፋ መቁረጥ

እንደ ሠው፣ ከተስፋ መቁረጥ የበለጠ በአንድ ላይ የሚያስተሳስረንና ለሁላችንም በአብላጫው የጋራ የሆነ ገጠመኝ የለም ማለት ይቻላል:: ተስፋ መቁረጥ ሳይነገር፣ ሳይጠበቅና ሳንዘጋጅ የሚደርስ በመሆኑ በኛ ላይ ሲከሰት ሁሉም ነገር ከኛ ወጥቶ የሄደ ያህል ይሰማናል:: ጉልበታችንን በቀስታ ይዞ የሚሄድ፣ እኛነታችንን በአንድ ላይ የያዘውን መንፈስ ቀስ በቀስ ሊያወጣ ወይም ሊያባርር የሚችል ነው:: በየትኛውም መንገድ ተስፋ የቆረጠ ሠው ወደፊት ጉዞ ለመቀጠል አዳጋች ይሆንበታል:: ደግሞም፣ በሕይወት ውስጥ ከምናሸንፍባቸው ይበልጥ የምንሸነፍባቸው ይበዛሉና ይህንን የማያገናዝቡ ሕይወታቸውን ለመራራነትና ለተስፋ መቁረጥ ብሎም ለባሰ ሁኔታ ይጋብዟታል:: (ገጽ 35)

ሠዎች ከላይ በጥቂቱ ደራሲው በጠቀሷቸውና እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ:: ሌላው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተነሱ ቁምነገሮች መጠቀስ ያለበት ራስን ለማጥፋት እንደ አንዱ ምክንያት የሚቆጠረው ሳናስብ የምናደርጋቸው ድርጊቶች ናቸው የሚለው ሥነ ልቡናዊ (Psychoanalysis) አስተሳሰብ ነው::

የተከለከሉና በማኅበረሰቡ የተወገዙ ግፊቶች በተደጋጋሚ ከ‹‹አንኮንሸስ›› ወደ ‹‹ኮንሸስ›› ለማለፍ በሚተጉ ጊዜ በራስ ያለ ዐመለካከት (ኤጎ) ይመልሳቸዋል:: ይህ ድርጊት ግጭቶችን ይፈጥራል:: ከዚያ ከከፋ ውጤቱ የአዕምሮ መቃወስን (neurosis) ያስከትላል:: የዚህ መጽሐፍ ጭብጥም ይህን ሃሳብ መግለጽ እንደሆነ ደራሲው ገጽ 45 ላይ አስቀምጠዋል::

ምን ጠላት መጣና በለሊት ጠራው፣

ለመሬት እንደሆን ቀድሞም የጁ ነው፤

በዚህ መጽሐፍ ደራሲ እምብዛም ትኩረት ያላገኘውን (በጥናትም፣ በሣይንስም፣ በሃይማኖትም) ርዕሠ-ጉዳይ አንስተው አከራካሪ፣ አሳሳቢ፣ ዐይን ገላጭ፣ ሸንቋጭ እና ታዛቢ ሃሳቦችን አነስተው ይሟገታሉ:: ራስን የማጥፋት ውስጣዊ ምክንያት (ለመግደል መፈለግ፣ ለመገደል መፈለግ እንዲሁም ለመሞት መፈለግ) እና ውጫዊ ምክንያት (የማኅበረሰብ አመለካከት፣ የቤተሰብ ሁኔታዎች፣ የአካባቢው ወግና ልማድ እና ያልተሟላ ስብዕና ዕድገት የሚያመጣው የመዛባት ሁኔታ) ብሎም ራስን ለማጥፋ የሚያበቁ ድንገተኛ ሁኔታዎችን፣ አዝማሚያ እና ዝንባሌዎችን ባጠቃላይ ራስን ስለማጥፋት በጥናት የተዳሰሱ ሃሳቦችን እና የግል ምልከታቸውን ከተለያዩ ገጠመኞቻቸው ጋር በአገራዊ ግጥም እያዋዙ ከባዱን እና የማይስበውን ርዕሠ-ጉዳይ ተነባቢ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል::

ምናኔ (በዝግታ ራስን መግደል)፣ ሰማዕትነት (በምክንያት /ከፍ ላለ ሃሳብ/ መሞት)፣ የአልኮል ሱሰኛነት (በዝግታ የመሞት አዝማሚያ)፣ የራስን ዐካል ማስወገድ (ራስን የመጉዳት ዝንባሌ እና ራስን ወደ ማጥፋት ሊያደርስ የሚችል ጠቋሚ ምልክት)፣ ጦርነት (ሠዎች በፍቃድ ወደ ሞት የሚሄዱበት በምክንያት የተደገፈ ወይም ያልተደገፈ ምርጫ መውሰድ) እንዲሁም መሠልና ከራስ ማጥፋት ጋር ተያያዥ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስተው አጠር አጠር ያሉ ማብራራያ እና ትንታኔዎችን በዚህ መጽሐፋቸው ሠጥተዋል::

ማጠቃለያ

ሞት ይቅር ይላሉ ሞት ቢቀር አልወድም፣

                ድንጋዩም ዐፈሩም ከሠው ፊት አይከብድም፤

ራስን ለማጥፋት ቢያንስ ውጫዊ እና ውስጣዊ ምክንያቶች እንዳሉ ለመረዳት ይቻላል:: ጉዳዩም ውስብስብ እና ብዙዎቻችን ሠዎች ራሳቸውን ካጠፉ በኋላ፣ በተለመደ መልኩ የምንደርስባቸው ድምዳሜዎች ከእውነታው እጅግ የራቁ እና ጉዳዩን እንዳንረዳ ሲያደርጉን እንደዘለቁ ደራሲው ያምናሉ:: እናም፣ በሠከነ መንገድ ይህ ጉዳይ ውይይት እና ምርምር እንዲደረግበት ይጋብዛሉ፡፡ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል:: ተደጋግሞ የታየው ራስን የማጥፋት ጉዳይ የግለሰቡ ጉዳይ ተደርጎ ተትቷል፡፡ ይህ ግን፣ መቅረት እንዳለበት እና ማኅበራዊ እንዲሁም ሳይንሳዊ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ አጽንዖት ሠጥተዋል:: (ገጽ 99)

እንደሚባለው ነው፤ ሁሉንም የራስ ማጥፋት ዝንባሌ እና ድርጊት ከሠው ልጅ ሕይወት ማጥፋት ባይቻልም እንኳ፣ በዳበረ ውይይት እና በተጠናከረ ጥናት እንዲሁም በሠው ልጅ ቁርጠኝነት አደጋውን መቀነስ ይቻላል:: የአንድንም ሠው የሕይወቱን ግዛት ከመጣስ ማዳን ከተቻለ እንደ ትልቅ ቁምነገር ይቆጠራል ብለው ያምናሉ- ደራሲው ንጉሡ አጥናፉ::

የህይወት ግዛቷ ደግሞ በተፈጥሮአዊ መንገድ እንደተሠመረላት ሁሉ ቢቻል በተፈጥሮአዊ መንገድ ካልሆነ ደግሞ ያለ ራስ ጣልቃ ገብነት ቢጣስ ምርጫቸው እንደሆነ ያስቀመጡ ይመስለኛል ደራሲው:: ያው ይመስለኛል ነው እንግዲህ::

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com