ዜና

የተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ዓዋጆችን እና የውሳኔ ሃሳብ አጸደቀ

Views: 371

የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ዛሬ ሐምሌ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው፤ የተለያዩ ዓዋጆች እና የውሳኔ ሃሳቦች ማፅደቁ ተነግሯል፡፡

ምክር ቤቱ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታቸውን ለሚለቁ የሚከፈል የካሳ ሁኔታን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል፡፡

በመሆኑም፣ የከተማ ልማት እና ኮንሰትራክሽን ሚኒስቴር በከተማም ሆነ በገጠር ባለይዞታዎች ለህዝብ ጥቅም መሬት እንዲለቁ ሲደረግ፣ የተነሺዎችን በሕገ መንግስቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ባከበረና በመሬት ዘርፍ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ርብርብ ለመደገፍና የመንግሥትን ልማታዊነት ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ እንዲሆን ዓዋጁ ተሻሽሎ እንደቀረበ ምክር ቤቱ አስታወቋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ምክር ቤቱ የጉምሩክ ዓዋጅን ለማሻሻል ተዘጋጅቶ የቀረበውን ረቂቅ ዓዋጅ ማጽደቁ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪ፣ ምክር ቤቱ ካጸደቃቸው ጉዳዮች መካከልም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤቶች ተወካዮች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫ ከቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንዲካሄድ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ማጽደቁ ነው የተነገረው፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት በ 2011 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ የነበረውን የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ እና የአካባቢ ምርጫ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ ባለመቻሉ፤ ከቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ ጋር እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ማጽደቁ ታውቋል፡፡

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሐምሌ 4 ቀን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፃፈው ድብዳቤ፤ የሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤት ምርጫን በተቀመጠው ጊዜ ሠሌዳ፣ ዘንድሮም ማካሄድ አይቻልም ማለቱን እና በቀረው አጭር የዓመቱ ጊዜ ምርጫ አስፍፈፃሚዎችን መመልመል፣ ማደራጀት እና ሥልጠና ለመስጠት በቂ ጊዜ አለመኖሩን ቦርዱ በምክንያትነት አቅርቧል ነው የተባለው።

ስለሆነም፣  አሁን በስራ ላይ ያሉት የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች በሥራቸው ይቀጥላሉ ተብሏል።

ምክር ቤቱ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ ምክር ቤቶች የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በተጨማሪም፣ ምክር ቤቱ የባንክ ሥራ ዓዋጅን ለማሻሻል የወጣውን ረቂቅ ዓዋጅ ከመረመረ በኋላ፣ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዘርፉ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችለውን ረቂቅ ዓዋጅ አፅድቋል፡፡

አዲሱ ዓዋጅ፣ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንክ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዳይሳተፉ ተጥሎ የነበረውን የሕግ እገዳ ከማንሳቱም ባሻገር ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን የፈቀደ መሆኑን ታውቋል፡፡

ከነዚህ ውሳኔዎች በተጨማሪ የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባንክ ሥራ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ረቂቅ ዓዋጁ ተመልክቷል፡፡

በተመሳሳይ የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጉምሩክ ዓዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ በመርመር ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎም እየተጠበቀ ነው፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com