ዜና

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባልደረቦች፣  ጓደኞች እና ትዝታው

Views: 5096

– ወጥቶ-አደር፣ ንሥረ- ኢትዮጵያ!

በ196ዐዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከሐረር መድኃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቅቄ ነበር፡፡ ከዚያም፣ የኢትዮጵያ ቴሌኰሙኒኬሽን ቦርድ ተቋም የሚሰጠው የቴክኒክ ትምህርት ሙያ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ገባሁ፡፡ የሁለት ዓመታት ተኩል ሥልጠናውን አጠናቅቄ፣ ለተግባር ልምምድ አሥመራ በሚገኘው የኢትዮጵያ ራዲዮ ማሰራጫ ጣቢያ ተመደብኩ፡፡

ሐረር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትና ከዚያም በፊት የመጀመሪያ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት አብሮ አደግ ጓደኛዬ የነበረው ኰ/ል የሺጥላ መርሻ፣ አየር ኃይል በረራ ት/ቤት ገብቶ ሥልጠናውን አጠናቅቆ ስለነበር፤ በወቅቱ አሥመራ አየር ኃይል ተመድቦ ይሰራ ነበር፡፡

ይህ አጋጣሚ ከበርካታ የአየር ኃይል መኰንኖች ጋር ሊያስተዋውቀኝ ቻለ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ፣ እኔ የአንድ ዓመት የተግባር ትምህርቴን (ልምምድ) አጠናቅቄ ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ ቋሚ ምድብ ሥራዬ ላይ ተመድቤ በምሰራበት ወቅት፣ ጀግናው ኰሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ እና ጓደኞቹ ኰ/ል የሺጥላ መርሻ ደብረ ዘይት አየር ኃይል ተመድበው ስለነበር፤ የሳምንት እረፍታቸውን ማለትም ቅዳሜና እሁድን ከእኔ ዘንድ እያሳለፉ ነበር- ለሰኞ ሥራ ወደ ደብረዘይት የሚመለሱት፡፡

ይህ አጋጣሚ ከበርካታ የአየር ኃይል ተዋጊ መኰንኖች ጋር ሊያስተዋውቀኝ ቻለ፡፡ በመሆኑም፣ ዘመን እየገፋ በሄደ ቁጥር ግንኙነታችንም በጣም ተጠናክሮ ወደ ቤተሰባዊ ደረጃ ከፍ አለ፡፡

ኰ/ል በዛባህ ጴጥሮስ በውጊያ ላይ ያለው ብቃት፣ ወኔና ቆራጥነት እጅግ የተለየ ነበር፡፡ መላ የሥራ ባልደረቦችና የቅርብ ጓደኞቹ በአንድ ድምፅና ቃል የሚመሰክሩለት እልኸኛ ሀገር ወዳድ ቆራጥ ተዋጊ መኰንን ነበር፡፡

ወቅቱ የአብዮት ፍንዳታ ጊዜ ስለነበር፣ እኛ የ6ዐዎቹ ትውልድ አባላት ደግሞ አውቀናል ብለን ግራ ዘመም ፖለቲካን እናቀነቅን ነበር፡፡ ሁለት የማይጣጣሙ ጐራዎች አገር ወዳድነትና ዳር-ድንበር ጠባቂነት እና ዓለም አቀፋዊ ላብ-አደርና ዓለም የላብ አደሮች ትሆናለች ባይነት፡-

ሀገር ጐራ ለይቶ፤ በቀኝ እና በግራ ተከፋፍሎ ምድር ሲታመስ፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የሶማሊያው የዚያድ ባሬ ጦር ሲመኘው የነበረውን የታላቋን ሶማሊያ ድንበር ለማስፋፋት በምስራቁ የሀገራችን ድንበር በኩል ወረራ ይጀምራል፡፡

በዚህን ጊዜ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጀግኖች የፈፀሙት ገድልና ጀግንነት ወደር አልነበረውም፡፡ ከእነኚህ ጀግኖች መኰንኖች መካከል ኰ/ል በዛብህ ጴጥሮስ ላይ ብቻ- ለዛሬው አተኩራለሁ፡፡

በዛብህ ጴጥሮስ፣ እኔ ቤት የሳምንቱን መጨረሻ ቀናት የሚያሳልፍበት እንደበረ ገልጫለሁ፡፡ (ከጓደኛዬ ኰ/ል የሺጥላ መርሻ ጋር) በዚህን ጊዜ በተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መወያየትና መነጋገር ወቅቱ የሚጠይቀው አጀንዳ ስለነበረ፣ እኔም የእራሴን እምነትና የፖለቲካ መስመር አንፀባርቅ ነበር፡፡

ወቅቱ እጅግ አስፈሪ ስለነበር፣ በተለይ እኛ በህቡዕ ለምንቀሳቀሰው ብዙውን ነገር በይፋ አውጥቶ መነጋገር አስቸጋሪ ነበር፡፡ እናም፣ ዳር-ዳሩን ስንወያይ፣ አንድ ወቅት ላይ እጅግ ከረር ያለ ሁኔታ ተፈጥሮ እጁን እንደ ቡጢ ጨብጦ “I don’t want to be land locked” ብሎ ጠረጴዛውን ነረተው፡፡

ጓደኛሞች ስለነበርን፣ ለክፉ ነገር እንደ ማንሰጣጥ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በሀገር ጉዳይ ላይ ኰ/ል በዛብህ ጴጥሮስ ቀልድ አያውቅም ነበር፡፡ በሁሉም ወረዳ ዓውድ ላይ በተለይ በምስራቁ የሀገራችን ድንበር በኩል የዚያድ ባሬን አየር ኃይል ተዋጊዎች ድባቅ የመታ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበር፡፡

በተለያዩ ጊዜያት፣ ከዋላቸው የአየር ለአየር (dog fighting) ውጊያ ላይ በመትረየስና በቦምብ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የሶማሊያ ሚግ ጄቶችን አጋይቷል፤ ድባቅ መትቷል፡፡

ከዚያም፣ የሰሜኑ የእርስ በእርስ ጦርነት ሲፋፋም፣ ወደ ኤርትራ በመዛወር ከአስመራ አየር ኃይል ሠፈር በመነሳት፣ በኤርትራ ተገንጣይ ወንበዴዎች ላይ፣ ይህ ነው የማይባል ጉዳትንና ኪሳራ አድርሷል፡፡

ይሁንና፣ በጣም ዝቅ ብሎ ዒላማውን (ታርጌት) አነጣጥሮ እና ፈልጐ በጀግንነት ይመታ ስለነበር፣ በአየር መቃወሚያ መሳሪያ ተመትቶ በዣንጥላ ዘሎ በመውረዱ የኤርትራ ነፃ አውጭ ግንባር ሻአቢያ እጅ ወደቀ፡፡

ለሰባት ዓመታት በምርኰኝነት ከቆየ በኋላ፣ ወያኔና ሻዕቢያ ደርግን አሸንፈው ሀገሪቱን ከተቆጣጠሩና ለሁለት ከተቃረጧት በኋላ፣ የምርኰኛ ልውውጥ ተደርጎ ኰ/ል በዛብህ ጴጥሮስም ከሀገሩና ውድ ቤተሰቡ ጋር ዳግም ተቀላቀለ፡፡

ይሁን እንጂ፣ እንደገና የሻዕቢያና የወያኔ ግንኙነት ጠልሽቶ ተቃርኗቸው አገርሽቶ፣ ፍቅሩ ወደ ጸብ ተለውጦ ባድሜ ስትወረር፤ ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ ዳግመኛ ወደ አስመራ (ኤርትራ) ለግዳጅ እንዲዘምት ታዘዘ፡፡

ሀገር ወዳዱ ሰው፣ ቆራጡ ኢትዮጵያዊው ወታደር፣ የዓየር ኃይሉ አለቃ፣ ከፍ ብሎ የሚበረው ንሥር አሟራ፣ ንሥረ-ኢትዮጵያ ግዳጁን በሚገባ ተወጣ፡፡ ነገር ግን የእርሱን ሠልጣኞች ከማዘዝ ይልቅ ራሱ ዝቅ እያለ እየበረረ ሀገር ተደቅኖባት የነበረውን አደጋ ከምንጩ ሊያከስም በወጣበት አየር የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ይህን የሀገር አለኝታና ባለውለታ፤ ባለትዳርና የሦስት ወንዶችና የሁለት ሴቶች አባት ምን ላይ እንዳለ ታሪክ ትፈርዳለች፡፡ አሁን ግን ለጊዜው ቄሱም ዝም፤ መጽሐፉም ዝም፤ ዝም-ዝም ነው እንዲሉ፡፡ ሠላም ለሁሉም!!!

ፎቶ- መግለጫ፡- (በቀኝ በኩል ጥቁር ሌዘር የለበሰው የትውስታው ተራኪ አቶ ኩራባቸው ሸዋረጋ፤ መሐል ላይ ኮ/ል የሺጥላ መርሻ፤ በስተግራ በኩል ደግሞ የትውስታችን ዋና ባለ-ታሪክ፣ የሀገራችን ጀግና ተዋጊ ዓየር ኃይል- ኰ/ል በዛባህ ጴጥሮስ ነው፡፡)

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com