ቁልቋል በለስ የሚበላ እና የሚጠጣ

Views: 212
 • ቁልቋል (በለስ) “የሚበላ ወይስ የሚጠጣ?!”

ቁልቋል (በለስ)፡- እነሆ በዚህ በክረምቱ ወራት፣ የበለስ ፍሬ በሚገባ በገበያ ላይ ይገኛልና፤ በለስ የቀናው የበለስ ፍሬ ይቅመስ ሳምንታዊ መልዕክቴ ነው፡፡ የጤና ጠቀሜታው እጅግ ብዙ ነውና!!!

 

ቁልቋል በለስ በበረሐ ምድር ሲበቅል

የበለስ (ቁልቋል) ፍራፍሬ

 1. የበለስ (ቁልቋል) ተክል፡-

በለስ (ቁልቋል) ቅጠል የለውም፡፡ እንዲሁ ወፍራም እሾሃማ ወይም እሾህ አልባ እንደ ሰፌድ የተዘረጉ ጠፍጣፋ ነገሮች አሉት፡፡ በአማርኛ ቁልቋል፣ በሳይንሳዊ መጠሪያው ኡፑንቲያ ፊከስ ኢንዲካ (Opuntia ficus indica) በኢንግሊዘኛ (Prickly pear  cactus)  በፈረንሳይኛ (Figuier d’inde)  በጀርመንኛ (Kaktusfeige)  ይባላል፡ማጣቀሻ አንድ

በየአካባቢውም ብዙ መጠሪያ ስሞች አሉት፤ በኦሮምኛ ሀዳሚ፣( Hadaammi)፣  በትግሪኛ በለስ፣ በሐረር አካባቢ ቲኒ፣ ባሌ አሾካ ይሉታል፡፡ ቁልቋል (በለስ) በረሐማነትን፣ ድርቀን፣ የአፈር ልምላሜ ማነስን ተቋቁሞ የሚለማ ተክል ነው፡፡ በበጋ ወራት ጠፍጣፋ አካሉን በመትከል ወይም አጋድሞ፣ በመሐሉ ላይ አፈር በመጨመር እንዲበቅል ማድረግ ይቻላል፡፡ በአገራችን አብዛኛው ዱር በቀል ነው፡፡ በብዛት የሚመረተው ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ በባሌ ዞን ሸነካ በሚባል አካባቢም በብዛት ይገኛል፡፡ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች በዱር ይበቅላል፡፡ በዚህ በሐምሌ ወራት አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ወጣቶች በእጅ በሚገፋ ጋሪ ላይ ሞልተው እያዞሩ ይሸጡታል፡፡ አሁን ወራቱ ስለሆነ፣ በሌሎችም ከተሞች ውስጥ ለገበያ ይቀርባል፡፡

 1. የሥነ ምግብ ጠቀሜታው ፡-

ቁልቋል (በለስ) ካሎሪው አነስተኛ እና ከኮልስትሮል ነፃ ነው፡፡ ጠቃሚ አሠር፣ ቫይታሚን ሲ፣ ካልስየም እና አንቲ ኦክሲደንት አለው፡፡ ለጤና ይረዳል፤ ብሎም ለብዙ ለበሽታ የመጋለጥን አደጋ ይቀንሳል፡፡  ሟሚ የሆነ አሠር (soluble fiber ) እና ሟሚ ያልሆነ (Insoluble fiber)  በውስጡ አለው፡፡ ሟሚ የሆነው አሠር የደም ኮልስትሮልን ለመቆጣጠር ይረዳል፤ እንዲሁም የዓይነት ሁለት የስኳር በሽታን ይቀንሳል፡፡ ሟሚ ያልሆነው አሠር የሥርዓተ ምግብ ስልቀጣን በማገዝ፣ ትልቁ አንጀት በቀላሉ ዓይነምድርን እንዲያስወግድ ይረዳል፡፡

የቁልቋል የጤና ጥቅሞች ብዙ ናቸው፣ ጥቂቶቹን ሜዴትራንያን ሔልዝ ላይፍ

እንደዚህ ይጠቅሳል፤ ማጣቀሻ ሁለት

 

 

 

 

 

 

 1. በጥሬው እንደዚሁ ይበላል፡-

ሲለቅሙትም ሆነ ሲመገቡት እሾሁን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለገበያ የቀረበውም ቢሆን፣ በዓይን የማይታዩ ደቃቅ እሾህ አሉት፡፡ ይህ ለዓይን፣ ለምላስ እና ለቆዳ ችግር ያስከትላል፡፡ እጅን በላስቲክ ሸፍኖ መያዝ ብልሐት ነው፡፡ ከዳር እና ዳር በቢለዋ ይቆረጣል፣ መሐሉ ይሰነጠቃል፣ የውስጡ ሙዳ-ዛላው አካል እንደዚህ ፍንትው ይላል፡፡

በጥሬ ለመብላት የተዘጋጀው ቁልቋለ (በለስ)

የውጪውን ወፍራም ልጣጭ ትቶ የውስጡን ሙዳ-ዛላ ከነ ደቃቅ የውስጡ ፍሬ መብላት ነው፡፡ እስካልበዛ ድረስ የውስጡ ደቃቅ ፍሬ አብሮ ቢበላም ችግር የለውም፡፡

 1. ‹‹በለስ ቀንቶን›› በቀን ምን ያህል መጠን በለስ እንብላ ወይም እንጠጣ?

ተለቅ ያሉት ፍሬዎች አንዱ እስከ 1ዐዐ ግራም ይመዝናል፡፡ የውስጡ ደቃቅ ፍሬ ያልወጣለት በቀን እስከ 1ዐ የበለስ ፍራፍሬ በተለያየ ሰዓት መብላት ይቻላል፡፡ በወቅቱ በገበያ ላይ በሚቀርብበት ወራት አንዳንድ ወጣቶች በአንድ ጊዜ 1ዐ (አንድ ኪሎ ያህል) እና ከዚያም በላይ ከነ ደቃቅ ፍሬው ይመገባሉ፡፡ ይህንን ያህል በአንድ ጊዜ ከነፍሬው ከተመገቡ ለአንጀት ጥሩ አይሆንም፡፡ ነገር ግን ይህንኑ ያህል ፍሬው ተለይቶ በጁስ መልክ በአንድ ጊዜም ቢጠጡት እንዲያውም እጅግ መልካም ነው፡፡

 1. ፍሬውን መለየት

ደቃቅ ፍሬውን በቀላሉ ለማስለቀቅ እና ለመለየት በጁስ መፍጫ የቤት ማሽን መጠቀም ነው፡፡ በማሽን ለመምታት ንፁህ ውሃ መጨመር ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ማጥለል፡፡

የተጠለለው የበለስ ፍሬ (ዘር)

 1. ወፈር ያለ ጁስ ለመሥራት

ከማጥለያው ውስጥ አልፎ የወረዳው ጁስ መሳይ ፈሳሽ ላይ፣ የሚፈልጉትን ማጣፋጫ ሊያደርጉበት ይችላሉ፡፡ ስኳር ወይም ማር፡፡ አለዚያም በራሱ ጣዕም መጠጣት ይቻላል፡፡ የተጣራው የበለስ ጁስ እንደዚህ ደስ የሚል መልክ አለው፡፡ ሲጠጡት አርኪ ነው፡፡

የበለስ ጁስ

ከላይ ያለው አንድ የውሃ ብርጭቆ ጁስ ከ ሁለት የበለስ ፍሬ የተጨመቀ ወፍራም ጁስ ነው፡፡ ከአንድ ኪሎ የበለስ ፍሬ አምስት ብርጭቆ ጁስ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ከቻላችሁ በየቤታችሁ እንደዚህ አዘጋጅታችሁ ጠጡ፡፡ ለጤና ጠቃሚነውና!

7. የበለስ ወጥ፡-

የበለስ ፍሬ- ወጥ

የበለስን ፍሬ ጨምቆ ደቃቁን ዘር ለይቶ በመጠባበስ ዓይነት አብስሎ፣ ለእንጀራ ወይም ለዳቦ ማባያ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ከላይ በምስሉ የሚታየው በነጭ ሸንኩርት፣ ቃርያ፣ ጨው፣ ወዘተ የተጠባበሰ ነው፡፡ በቀላሉ በ1ዐ ደቂቃ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ከሌላም ከሚፈልጉት አትክልት ጋር ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ እንዲያውም ለወጥ ቅጠሉ ተመራጭ ነው፡፡ ሆኖም ለጊዜው ቅጠሉን በገበያ ላይ ማግኘት አይቻልም፡፡

 1. የበለስ ሻይ፡-

ከላይ በተነገረው መሠረት በጁስ መምቻ ይመታል፡፡ የውሃው መጠን ከጁሱ እጥፍ ይሆናል፡፡ ይጣድ እና ይፈላል፡፡ በውጤቱ ይህን የመሰለ የበለስ ሻይ ይገኛል፡፡

የበለስ ሻይ

በዚህ ዓይነት ከአንድ ኪሎ የበለስ ፍራፍሬ፣ 2ዐ የሻይ ስኒ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ሻይው ላይ ስኳር ወይም ማር ማከል ይችላሉ፡፡

 1. ለነገሩ፡-

ለነገሩ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋውን አውቀን ዋጋ አልሰጠነውም፡፡ ህንድ፣ ሞሮኮ፣ ዩ.ኤስ አሜሪካ፣ ቱንዚያ፣ እና ስፔን በከፍተኛ መጠን ለዓለም ገበያ ከአቅራቢዎች ተርታ ናቸው፡፡ በዓለም ገበያ የበለስ (ቁልቋል) ፍሬ አንድ ኪሎ የችርቻሮ ዋጋው ከ 15 እስከ 25 ዶላር ነው፡፡ እኛ አገር በነፃ ለቅሞ ከመብላት እስከ 2ዐ ብር በኪሎ ነው፡፡ ሌላው ቀረቶ በዓለም ገበያ ፍራፍሬውን በዱቄት መልክ አዘጋጅተው የሚያቀርቡ ከ አንድ ሺ በላይ ካምፓኒዎች አሉ፡፡ የዱቄቱም የአንድ ኪሎ ዋጋ በአማካይ ከ 3ዐ እስከ 6ዐ ዶላር ይሆናል፡፡

በእርግጥ በብዙ ሺ ኪሎ የሚገዙት በጅምላ ዋጋ ኪሎው እስከ አንድ ዶላር ዝቅ ባለ ዋጋ እና በጥቂቱ በችርቻሮ ዋጋ ለምሳሌ አንድ ኪሎ ብቻ የሚገዙት ደግሞ እስከ መቶ ዶላር ከፍ ያለ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ እንግዲያውስ፣ ይህን ያህል ዋጋ የሚከፈልበት ስንት ጥቅም ቢኖረው ነው?! ብላችሁ አስቡ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በበረሐው፣ በቆላ፣ በወይናደጋው እና በደጋው መትከል እና ማምረት ይቻላል፡፡ ከዚያም በፋብሪካ ማቀናበር፣ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ገበያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይህም ባይቻል በጥሩ ሁኔታ ፍሬውን አድርቆ፣ ማሸግ እና ከፍ ባለ ዋጋ ወደ ውጪ መላክ ይቻላል፡፡

1ዐ. የተነገሩበትን ሐሜት መመከት

 • “ሆድ ድርቀት ያመጣል” የሚሉት ሐሜት የበዛ ስህተት ነው፡፡ እንዲያውም የሆድ ድርቀትን ይከላከላል፡፡ ዋናው ነገር ፍሬውን ማጣራት ነው፡፡ ከነፍሬው እንኳን ቢበሉት አለማብዛት ነው፡፡ እናም በሰል ያለውን መመገብ፡፡
 • “የደሃ ምግብ ነው”  በእኛ አገር በሞኝነት “የደሃ ምግብ” የሚል ሐሜት ተነገረበት እንጂ፣ በዓለም ላይ በውድ ዋጋ የሚሸጥ የተፈጥሮ ምግብ የሚመርጡት ሰዎች ተመራጭ ምግብ ነው፡፡

ለማጠቃለል፡-

በዚህ አጭር መልዕክት ለማስተላለፍ የተፈለገው፣ የቁልቋል (በለስ) ፍራፍሬ ተመገቡ፣ የጤና በረከቱ ብዙ ነው ለማለት ነው፡፡ በሰፊው ስናስበው ዳግሞ በለስ ቅጠሉ ለእንስሳት መኖ ይሆናል፤ ቅጠሉ ለሰው ምግብም፣ መድኃኒትም ጭምር ነው፡፡ አበባው በፋብሪካ የሚፈለግ ምርት ነው፡፡ ሥሩ ለበሽታ መድኃኒት ነው፡፡ ተክሉ የአፈር መሸርሸርን ይከላል፡፡ የበለስ ቅጠል ፀረ-ፈንገስ ሲሆን፣ በዚሁ መረጃ መረብ ላይ “ፀጉርን እንዲህ ተንከባከቡ” የሚለው ርዕስ ሥር  የበለጠ አንብቡ፡፡

ማጣቀሻ፡-

 1. በቀለች ቶላ፣ ሐምሌ 2ዐዐ9 ዓ.ም Glossary of Plant’s Name In Scientific, Amharic and Others, የዕፀዋት መጠሪያ በሳይንሳዊ፣ አማርኛ እና ሌሎች፤ አልፋ አታሚዎች፡ አዲስ አበባ፤
 2. https://mediterraneanlife.trustpass.alibaba.com/product/
Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com