የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሞሮኮ እግር ኳስ ፕሬዝዳንትን ከሠሠ

Views: 377

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሦስተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት ፋውዚ ሌክጃ፤ በፊፋ እውቅና የተሠጠውን በዓምላክ ተሰማ (ዳኛ) ላይ ድብደባ በመፈጸማቸው ክስ ተመሰረተባቸው፡፡

በሳለፍነው ሳምንት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን በግብፁ ዛማሌክ እና በሞሮኮው ቤርካኔ የእግር ኳስ ክለብ መካከል በተደረገው የፍፃሜ ዋንጫ ላይ በአምላክ ተሰማ የመሐል ዳኛ ሆነው በመሩበት ጨዋታ የግብፁ ዛማሌክ አሸናፊ ሆኖ ነበር፡፡

ሆኖም፣ በሜዳሊያ ሽልማት ሥነስርዓቱ ላይ ግን የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የትውልድ አካባቢቸውን የሚወክልላቸው እና የሚደግፉት ቤርካኔ መሸነፉን ተከትሎ የበአምላክን ጭንቅላት ጉልበት በተሞላበት ሁኔታ እንደመቷቸው እና በኋላም በፀጥታ ኃይሎች አማካይነት ዳኛው እንደተረፈ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉት ጥቂት ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ጨዋታ ዳኞች አንዱ የሆኑት ዳኛ በአምላክ የጨዋታን አጠቃላይ ጥንቅር ወይም ሪፖርት እንዳደረጉ ተገለጿል፡፡

ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በካፍ የስነ ምግባር (ዲሲፒሊን) መመሪያ ስር የሚገኘው አንቀፅ 146 ን በመጥቀስ ጉዳዩን በትኩረት እንዲከታተሉት አሳስቧል፡፡

እንደ መመሪያው ከሆነም ፕሬዝዳንቱ ላይ የአንድ ዓመት እገዳ ወይም 20 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡

ጉዳዩም በአሁን ሰዓት በካፍ ውስጥ አነጋጋሪ ከመሆን አልፎ ተርፎ፣ ፕሬዝዳንቱ በተቋሙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉት ውስጥ ተጠቃሽ በመሆናቸው ቅጣት ላይጣልባቸው ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሬሽን ነገሩን በሚገባ ማጤን እና አስፈላጊ እርምጃ እንዲወሰድ ያሳሰበው፡፡

በአምላክ ተሰማ (ዳኛ) ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ካፍን እና ፊፋን በዳኝነት እያገለገሉ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com