የኢንቨስትመንት ሕግ ሊሻሻል ነው

Views: 282

– ረቂቅ-ሕግ ለውይይት ቀረበ

በሀገራችን እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመንት ፍላጎት ለማሳደግ የሚረዳ፣ ረቂቅ-ሕግ ተዘጋጀ፡፡ ሕጉ እየተካሄደ ያለውን የኢኮኖሚ ለውጥ ታሳቢ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ረቂቅ ሕጉ ከግሉ ዘርፍ፣ ከልማት አጋሮች እና ከባለድርሻ አካላት በተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ረቂቁ፣ በዋነኛነት በተለያዩ ዘርፎች ለወጣቶች ሰፊ የሆነ የስራ ዕድል ለመፍጠር በሚያስችል ሁኔታ ግልጽና የተቀናጀ ሥርዓትን የሚገነባ ለማድረግ ታስቦ በአዲስ መልክ እንደተዘጋጀ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሆነ ለሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ምቹ ሆና የሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነትን ሊያረጋግጥ የሚችል የኢንቨስትመንት ሕግ ለማሻሻል ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በሕጉ ላይ በግልጽ የተከለከሉ ባለሀብቶች ካልሆኑ በስተቀር፣ የውጪ ባለሀብቶች በጥምረት ወይም ብቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጓቸውን አሰራር በአዲሱ ሕግ ተካቷል፡፡

የረቂቅ ሕግ ዝግጅቱ የተጀመረው ከጥር ወር ጀምሮ ሲሆን፣ 15 አባላት ያሉት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሲሰራ ነበር፤ ግብረ ኃይሉ ከመንግሥት ባለድርሻ አካላት፣ ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች እና የልማት አጋሮች ምክክር አድርገው ረቂቁን አዘጋጅተውታል ተብሏል፡፡

ረቂቅ ሕጉ ከባለድርሻ አካላት ግብዓት ከተወሰደ በኋላ፣ በሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ላይ በፓርላማ ቀርቦ የሚጸድቅ ይሆናል፡፡

የኢንቨስትመንት ሕግ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ አማካኝነት ማሻሻያ እየተደረገበት ለግማሽ ክፍለ-ዘመን (50) ዓመታት ማገልገሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com