በዐማርኛ አፍ ያልፈቱ አንጋፋ ደራስያን ሲታወሱ

Views: 893

ዘመናዊ የዐማርኛ ስነ ጽሑፍን ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ ካደረሱት ጎምቱ ጸሐፍት መካከል ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባሉት አፋቸውን የፈቱት በሌላ ቋንቋ ነዉ ።

ያለ በዐሉ ግርማ እና ሥብሐት ገ/እግዚአብሔር የዐማርኛን ሥነ-ጽሑፍ ማሰብ ከባድ ነዉ ። ጸጋዬ
ገ/መድህንን ደግሞ ከተዉኔቱ እና ሥነ ግጥም አንጻር አለማንሳት አይሞከርም ፤ ግጥምንስ እንደ ሠለሞን ደሬሳ ማን አዘመናት ?

በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን በበኩላቸዉ የዐማርኛን ትርጉም ከሣህለ ሥላሴ ብርሀነማርያም ዉጪ አይታሰብም በማለት ዘመናዊ የዐማርኛን ሥነ ጽሑፍ ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች የመጡ ሠዎች እንዳፋፉት እና አሁን ያለዉን ቅርጽ እንደሠጡት በመናገር ” የዐማርኛን ሥነ-ጽሑፍ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ነዉ ” ይላሉ ።

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የዉጪ ቋንቋዎች እና ሥነ-ጽሑፍ ክፍል ረ/ፕሮፌሰር የሆነችው ጸደይ ወንድሙ ” እነዚህ ደራስያን በሌሎች የዓለም ቋንቋዎች የመጻፍ ዕድል እያላቸዉ በዐማርኛ የጻፉ ፣ የራሳቸውን የሥነ -ጽሑፍ ዘይቤ የገነቡ ናቸዉ ” ትላለች ።

የኮተቤው መምህር የሻዉ ተሠማ በበኩሉ ” እርግጥ ዘመናዊ የዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ዘር ልቁጠር ካለች እርቃኗን ቀሪ ” እንደሆነች ይናገራል ። ለዚህም በዐሉ ግርማ ፣ ጸጋዬ ገ/መድህን ፣ ሠለሞን ደሬሳ ፣ ገበየሁ ዐየለ ፣ አማረ ማሞ፣ ሙሉጌታ ሉሌ ፣ ታቦር ዋሚ እያለ በመጥቀስ ዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ በነማን ጫንቃ ላይ ወድቆ እንደነበር ለመረዳት ይቻለናል ሲል መምህር የሻዉ ያክላል።

በየሻዉ ሀሳብ የሚስማማው ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ” ዐማርኛ ከግራም ከቀኝም የተወጠረበት ካስማ አለዉ” በማለት ሀሳቡን ያጸናል ። የመጀመሪያዎቹን የዐማርኛ ደራስያንን በተመለከተ ” እዉነት ነዉ አፋቸውን በዐማርኛ የፈቱ ሠዎችን እናገኛለን ” ብሎ እነ መኮንን እንዳልካቸው ፣ ዮፍታሔ ንጉሴ ፣ ግርማቸው ተ/ሀዋርያትን የሚጠቅሰው ዓለማየሁ ገላጋይ ፤ በተጨማሪ ግን የዐማርኛ ልብ ወለድ ሥጋ እና ደም ነስቶ እስትንፋስ የዘራዉ አፋቸዉን በዐማርኛ በፈቱ ደራስያን እንዳልሆነ ይጠቅሳል ።

ለዐማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ሁለተኛው ረድፍ ላይ ተሠልፈው የሚገኙት ከጣልያን ወረራ በኋላ የተወለዱት ፤ በተለይ ከ1928 ወዲህ ፣ ከመሠረተ ልማት መስፋፋት በኋላ የመጡት ደራስያን መሆናቸውን ዓለማየሁ ያስታዉሳል ።

ከትግራይ ስብሀት ፣ ከአምቦ ጸጋዬ ፣ ሠለሞን ከወለጋ ፣ አሠፋ ጫቦ ከጨንቻ በድርሰቱም ሆነ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ዉስጥ በመሳተፍ ዐማርኛ ለሥነ-ጽሑፍ ምቹ ቋንቋ እንዲሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ ሊሠመርበት እንደሚገባ ያስገነዝባል ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ።

Via – BBC ዐማርኛ

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com