በአፋር እና በሶማሌ ክልል ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት ዘጠኝ ሰዎች ሞቱ

Views: 266

በአፋር እና በሶማሌ ክልል ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት፣ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የግጭቱ ሥር መሠረት የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ነው ተብሏል፡፡

‹‹ግጭቱ የተፈጠረው ደለህሌ እና ሀለሌ የተባሉ ሥፍራዎች ላይ ነው›› ያሉት በቦታው የሚገኙ የኢትዮ ኦንላይን የዜና ምንጮች፣ በአካባቢው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የመሬት ባለቤትነት ውዝግብ አለ ብለዋል፡፡

‹‹ግጭት ሲፈጠር አዲስ አይደለም›› የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የሰሞኑ ግጭት መንስዔም ይኸው የመሬት ይገባኛል ጉዳይ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ከሁለቱም ወገን በጥይት ተኩስ የተጎዱ ዜጎች በአካባቢው የጤና ተቋም ሕክምና እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡

ግጭት ከመፈጠሩ በፊት ላለፉት ስድስት ወራት መጠነኛ የተኩስ ልውውጥ በማድረግ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

ለአፋር ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ስለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም የስልክ ጥሪውን አልመለሱልንም፡፡

ከሶማሊያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራም እንዲሁ አልተሳካም፡፡

የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ሊቀ መንበሩ አቶ መሐመድ አሕመድ በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ግልፅ የሆነ እና የተጣራ መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com